ትህነግ በ”ዝርፊያ ፖለቲካ” ችጋር እያመረተ ነው

ከትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር በኩል የሚሰማው በጋው በደንብ ሳይገባ አንድ ሁነኛ ድል መጨበጥ፣ አለያም መደራደሪያ የሚሆን ሃይል መያዝ የሚለው አጀንዳ ነው። በመንግስት በኩል ደግሞ መስከረም ከጠባ በሁዋላ መሬቱ ሲተግ፣ ሰማዩ ሲበራ የትህነግን ግብአት ለመፈጸም በድል የታጀበ ቅድመ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ነው። ከየአቅጣጫው ውጤት የሚጠብቁ እንዳሉ ሁሉ የዕለት ጉርስ ያረረባቸው ዜጎች ድምጽ እየተሰማ ነው። ችጋር እየተስፋፋ ነው።

ትህነግ ” የሰው ማዕበል” በማንቀሳቀስ ሰፊ የሆነ አካባቢን ከአማራ ክልል በመውረሩ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ተፈናቅለዋል። አርሶ አደርና ሰለባ የሆኑ ሲመሰክሩ እንደተሰማው ትህነግ ኮቴው ባለፈባቸው ስፋራዎች ሁሉ ዘርፏል። ገሏል። አቃጥሏል። አውድሟል። ይህን ሁሉ ሲያደርግ እድሜ፣ ጾታ አለመረጠም። እንስሳና ሰው አልለየም። ደሃና ያለውን አልመዘነም። የዕምነት ተቋማትን፣ የህክምናና የትምህርት መሰረተ ልማቶችን ሳይለይ አዳሽቋል። ዱቄትና ሊጥ ሳይቀር ዘርፎ ጠኔውን አራግፏል። ምንም ያላደረጉትን ምስኪኖች ክረምቱን አርሰው አንዳይበሉ ከልክሏቸዋል። ችጋር እንዲወራቸው አድርጓቸዋል። ችጋር አምርቶ፣ ነስንሶባቸዋል። በሃይል ተገፍቶ ከወጣባቸው ስፍራዎች ሁሉ የሚሰማው ምስክርነትና በስዕል የተደገፈ ማስረጃ የሚያረጋግጠው ሂሳብ ማወራረዱ አማራ ክልልን ማውደም ስለመሆኑ ማስረጃ ነው።

ዛሬ ከሰሜን ወሎ የሚሰማው ድምጽ ይህ ነው። ቀድሞም አስታዋሽ ያልነበረውና በአማራነቱ ተገፍቶ ሲኖር የነበረው የወሎ ህዝብ ዛሬ እህል እንዳያገኝ፣ መድሃኒት እንዳይገባለት፣ እርድታ የሚባል ነገር እንዳይላክለት ይህ ” የችጋር ነጋዴ” ይህ ” የችጋር ፖለቲካ” አራማጅ፣ ይህ ” የችጋር አትራፊ” ቡድን እንቅፋት ሆኗል። “ለምን?” ይህን ያደርጋል? ምስኪኖች እህል እንዳይደርስላቸው የሰው ጎርፍ እያጎረፈ ስለምን በር ይዘጋል? ምንድንስ ነው ፍላጎቱ? ሕዝብ በረሃብ እንዲረግፍ ሲያደርግ ስለምን ዝም ተባለ? ኢትዮጵያዊያን በርጋታ ልንጠይቀው የሚገባ ጥያቄ ነው።

የወሎ ልጅ ልደቱ አስር ገጽ ጽፎ መንግስትን ሲዘለዝል አንድም ያልተነፈሰበት የችጋር ጉዳይ ማንን ስለሚመለከት ይሆን? ልደቱ ስለ ችጋር ዝምታን የመረጠው ማን ስለሚነካበትና ለማን ስም ተጠንቅቆ እንደሆነ ያልገባው አለ? ” አማራው ላይ የተፈጸመ የህልውና አደጋ የለም” ሲል የህሊናውን ውርዴ እንዲያሳይ የድፈረበት ምክንያት ያልተገለጸለት ሰው ይኖር ይሆን? ይህ ሁሉ አማራው ላይ የደረሰ ሰቆቃ ለልደቱና ለመሰሎቹ እንግዴዎች ቁብ ያልሰጣቸው ዋና መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ ምርምርና አዋቂ አያስፈልግምና ለተወው።

See also  የኦብነግ ማዕከላዊ ኮሚቴ በአስቸኳይ ስብሰባ ውሣኔዎች በሙሉ ተቀባይነት እንደሌላቸው ምርጫ ቦርድ አስታወቀ

የትህነግ ኮቴ በደረሰበት ሁሉ ችጋሩን እየረጨ ከፖለቲካው ጋር አንዳች ግንኙነት የሌላቸው ወገኖችን እያወደማቸው ነው። አይሳካም እንጂ ኦሮሚያ ቢዘልቅም ፋብሪካ፣ የኢንዱስትሪ መንደር፣ ባለሃብቶችን ወዘተ ከመዝረፍ የሚያግደው አንዳች ምክንያት የለም። አሽከሮችን ቀጥሮ ” ኦሮሞን ነጻ አወጣለሁ” ሲል፣ ይህንኑ ተከትሎ በከርስ በመደራደር ነጻ የወጣውንና የአገር ሃላፊነት ተረክቦ እየመራ ያለን ሕዝብ እንወክላለን የሚሉ ” ትግሬ ነጻ ያወጣናል” በሚል ታላቁን የኦሮሞ ሕዝብ እያዋረዱት ነው።

ኦሮሞን ” ጅኒ” ሲል በአጋንንት የወከለው ትህነግ ” ጅኒዎቹ እንደዚህ እንዲሆኑ የፈቀድነው እኛ ነን፤ ዋጋቸውን እንሰጣቸዋለን” በሚል በአደባባይ ምሎ ኦሮሞን አናት አናቱን እያለ በስናይፐር ሲደፋው ለነበረ ደም ቀለቡ ትህነግ ያደሩ “ሸቃዮች” ዝርፊያ አመሉ የሆነውን ወንበዴ ወደ ኦሮሚያ ጎትቶ ለማስገባት የሚያደርጉት ሙከራ የሚሳካ አይሆንም። የሃሳቤ ዋና መነሻ ለዛሬው ይህ በለመሆኑ አልፈዋለሁ።

ሕወሓት በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ እየፈፀመ ባለው ግፍ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች በረሃብ ምክንያት ከሞት ጋር መጋፈጣቸው ሲሰማ ፣ ይህ ተባይ የሆነ ቡድኑ በከፈተው ወረራና ጦርነት የተፈናቀሉ እናቶች፣ ህፃናትና አዛውንቶች ለሞት ሳይዳረጉ ምን መደረግ አለበት? በሚል አስቸኳይ ንቅናቄ ያስፈልጋል።

አልጀዚራ፣ ሮይተርስ፣ አጃንስፍራንስ ፕሬስ፣ ቢቢሲ፣ ፎክስ ኒውስና አሶሼትድ ፕሬስ ሚሊዮኖች ለህይወታቸው በሚያሰጋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እየተሰቃዩ መሆኑን ያፋ አድርገዋል።ችጋር የሚጋባ እንደሆነ አልዘገቡም እንጂ ችግሩን ይፋ አድርገዋል። የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ አቋሙን እንዲያስተካክል በይፋ አልተቹም እንጂ ዜናውን ዓለም እንዲሰማው አድረገዋል። አንዳንድ የቀድሞ ሴናተሮች ” በቃ” በሚል ዓይነት አሜሪካ ትህነግ እንዲጠፋ አዲስ ፖሊሲ ልትከተል እንደሚገባም ያመለከቱ አሉ። ሁሉም ሆኖ ግን ወገን ነጮቹ እየታቸውን ያስተካክሉ ዘንዳ፣ የረድኤት ተቋማት በሰብኣዊ አቅርቦት መንግሥትን እንዲያግዙ የሚጠይቁ የቲውተር ዘመቻዎች በስፋት እየተካሄዱ ነው።

ከስፍራው የሚወጣው መረጃ ትህነግ ከአካባቢው ህዝብ ላይ እየነጠቀ ጭፍራውን ስለሚቀልብ ከብቶቻቸው አለቀዋል። የቆጠቧት እህልም ተረግፋ የጭፍራው ምግብ ሆኗል። ቀኑ ሲደርስ ይፋ የሚሆነው ግፍ የወደፊቱን መጠፋፋት የሚያመላክት እንደሆነ ይሰማኛል። የተፈጸመው፣ እየተፈጸመ ያለውና ለመፈጸም ታቅዶ እየተሰራ ያለው ሁሉ የሰላም መንገድን አጨልሟል። እንደ ልደቱ አይነት ህሊናው የሞተ ” አማራው ላይ የተፈጸመ ወረራ የለም” በሚል በአደባባይ የቁም ሞት ኑዛዜ ሳይሆን አማራው ላይ ቀበሌ፣ ወረዳ፣ ዞን፣ አካባቢና ዘዬ ሳይለይ የከፋ ወንጀል ተፈጽሟል።

See also  TPLF General celebrates Oromo-Amhara division after Wolega massacres

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ባለፈው ሐሙስ ጳጉሜ 4/2013 በሰጠው መግለጫ በአካባቢው በሽብር ቡድኑ ምክንያት ለተፈናቀሉ ዜጎች የሰብኣዊ አቅርቦትን ከተባባሪ የረድኤት ተቋማት ጋር ለማድረስ እየተሰራ ቢሆንም በዚህ ” ነቀርሳ” ድርጅት ምክንያት ሰንካ እንደገጠመው አስታውቆ ነበር።ለሽብር ቡድኑ ሕወሓት ወገንተኛ ዘገባን የሚዘግቡ ተቋማትና በሰብኣዊ አቅርቦት ሽፋን የሽብር ቡድኑን ለመደገፍ የሚሰሩ አካላት ሰብኣዊነት ካሳሰባቸው በሁሉም አካባቢ ላሉና በሽብር ቡድኑ ምክንያት ችግር ውስጥ ለገቡ ድምፅ ሊሆኑ እንደሚገባ በመግለፅ ከኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ በተደጋጋሚ እያሰሙ ነው።

በየዘርፉ ዜጎች የሚያካሂዱት እንቅስቃሴ፣ መንግስት ይህን ነቀርሳ ለመንቀል እየዘረጋ ያለው ሰፊ ወጥመድ፣ በየሰፈሩ ህዝብ እያሳየ ያለው ወታደርነት፣ የደጀኑ ድጋፍ ታላቅ አክብሮት የሚሰጠው ነው። በሌላ በኩል ያለምንም በቂ ምክንያት ምስኪኖችን እየወረረ ግፍ ለሚፈጽመው ከሃጂና ጀሌዎች ባፍርም አነባላቸዋለሁ። ለምን?

መንግስት ትህነግን በሰማይና በምድር አረር ያወረደበት መከላከያን በማረዱና ክህደት በመፈጸሙ ነው። ሴኮና ጻድቃን በገሃድ ያመኑት ሃቅ በመሆኑ እዚህ ላይ ክርከር የለም። ስለዚህ ምንም ይሁን ምን የኢትዮጵያ መንግስት ጦር ለማዝመቱና ይቅርታ የሌለው ቅጣት ለመሰንዘሩ መነሻ ምክንያት አለው። ትህነግ ዛሬ ላይ አፋርን ወሮ ህዝቡን ለመጨፍጨፉ ምንም ምክንያት የለውም። ሰሜን ወሎ ወሮ ለማስራብ፣ንጽሃንን ለመግደልና ለመዝረፍ፣ ደቡብ ጎንደርንና ሰሜን ጎንደርን ወሮ ምስኪን አርሶ አደሮች ላይ ጥቃት፣ ንብረታቸው ላይ ዝርፊያ … ለመፈጸም፣ እነሱን ለመግደል እስከወዲያኛው ምክንያት ማቅረብ አይችልም። ታዲያ የዚህ ሁሉ ምላሽ የሚሰጥበት ቀን ሲመጣ ምን ሊሆን ይችላል? ይህን ሁሉ ያየ ከአሁን በሁዋላ እንዴት ከትህነግ ጋር አንድ ገበታ ይቀመጣል? እንዴት አንድ ኢትዮጵያዊ ከትህነግ አጫፋሪ ጋር … ነገሩ አያድርስ ነው። አምላክ ይርዳን እንጂ ነገሩ ሁሉ አያምርም። “ተው” የሚል ጠፍቷል። የ”ዲቃላ ፖለቲካ” በርካታ አክራሪዎችን አከሰመ። “የዝርፊያ ፖለቲካ” ትህነግን ማክሰሙ አይቀርም። ይህን ተረድቶ ከትህነግ መለየት መከራውን ያቀለው ካልሆነ በቀር ሌላ ጉዳት የለውም።

ትህነግ ዛሬ ላይ ከዝርፊያ ፖለቲካ ውጭ ማሰብ ያልቻለው ከተስፋ መቁረጥ በመነሳት “ከሄድኩ አይቀር ሁሉን አደህይቼ” በሚል ” የሂሳብ አወራርዳለሁ” ጨዋታ ነው። ሌሎችም ሂሳብ ሊያወራርዱ እንደሚችሉ ማሰብ የሌሎች ፈንታ ይሆናል። ትግራይ ወገኖቻን ሰፊ ችግር አሳልፈዋል። አሁንም በችግር ውስጥ እንደሆኑ እሙን ነው። ቸላማ ውስጥ ናቸው። ትህነግ ከኤርትራ፣ ከአማራ፣ ከአፋር ጋር ደም አቃብቶ ብቸኛ አድርጓቸዋል። በዚህ ከተቀጠለ ወደፊት ምን ይሆናል? ችጋር እየሰፋ፣ ልዩነት እየገነገነ፣ የዝርፊያ ፖለቲካ እያደገ … መቀጠል አይቻልም። መጨረጫው ሲጀመር ካሁን ይብሳልና ልብ እንበል።

See also  "በትግራይ ክልል ከኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ውጭ በግዳጅ ላይ ያለ ሌላ የፀጥታ ሀይል የለም"

በአያሌው ነመራ – አስተያየቱ የጸሃፊው አቋም ብቻ ነው

Leave a Reply