ፍትህ ሚኒስቴር በአሸባሪው አመራሮች ላይ የተከፈተው ክስ የሚቀጥል መሆኑን አስታወቀ፤ እነ ስብሃት በእርጅናና በርህራሄ ነው የተፈቱት

መንግስት የተወሰኑ እስረኞችን ክስ በማቋረጥ ከእስር መፍታቱ የአገራዊ ምክክሩን አካታችነት እና ሰብአዊነትና ርህራሄን ታሳቢ ያደረገ ውሳኔ መሆኑን የፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ። ወታደራዊ አመራር በሰጡና የአሸባሪው አመራሮች ላይ የተከፈተው ክስ እንደሚቀጥል ተገለጸ። ሰባቱ የተፈቱት በድሜ፣ በህምመና በርህራሄ እንደሆነ ተመልክቷል።

ከፖለቲካ ልሂቃን አልፈው ወደ ማህበረሰቡ እየተንጸባረቁ ያሉ ያለመግባባት ችግሮችን በአገራዊ ምክክር ከስር መሰረቱ ለመመፍታት በመደበኛ ፍትህ ብቻ ሳይሆን በተሃድሶ የሽግግር ማዕቀፍ እልባት መስጠት ያስፈልጋል ተብሏል።

የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ መንግስት በትናንትናው እለት የተወሰኑ እስረኞችን መፍታቱን በተመለከተ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው የተያዙ እስረኞችን በመፍታት ሂደት ‘ምህረት’ የሚደረገው በሕግ አውጭ አካል ሲሆን ይቅርታ ደግሞ በይቅርታ ቦርድ ጥያቄ መሰረት በአገሪቷ ፕሬዝዳንት በኩል የሚፈፀም መሆኑን አስረድተዋል።በመሆኑም በትናንትናው እለት መንግስት ይፋ ያደረገው እስረኞችን የመፍታት እርምጃ ምህረትም ሆነ ይቅርታ ሳይሆን በፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ላይ ያለን ጉዳይ ክስ የማቋረጥ ውሳኔ መሆኑን ገልጸዋል።

የክስ ማቋረጥ ውሳኔው የተወሰነው በሶስት መዝገቦች ሲሆን ሁሉቱ መዝገቦች በአቶ ጃዋር መሃመድና በአቶ እስክንድር ነጋ ስም ያሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በሁለቱ መዝገቦችን ክስ የማቋረጥ ውሳኔ ሁለቱ ግለሰቦች በርካታ ተከታይ ያላቸው የፖለቲካ አመራሮች በመሆናቸው ለአገራዊ ምክክር መድረኩ አካታችነትና አሳታፊነት የሚኖረውን ፋይዳ ታሳቢ ማድረጉን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።

‘አገራዊ ምክክር በአንድ አገር ከብዙ ዘማናት አንድ ጊዜ የሚደረግ ነው’ ያሉት ሚኒስትሩ በኢትዮጵያም እስካሁን ሁሉን አካታች አገራዊ ምክክር ተካሂዶ እንደማያውቅ ገልጸዋል።

በዚህም እስረኞችን የመፍታት ውሳኔው ‘ሁሉም ህብረተሰብ ተሳትፌበታለሁ’ የሚለው አሳታፊና አካታችና ቅቡልነት ያለው የምክክር መድረክ እንዲሆን ለማስቻል መንግስት የሄደበት እርቀት ስለመሆኑ አንስተዋል።

በሶስተኛ የክስ መዝገብ ደግሞ በእነ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ስም የተካተቱ ስድስት ግለሰቦች ከጤና ችግርና ከዕድሜ መግፋት አንጻር ጉዳያቸው ታይቶ ለሰብዓዊነትና ለርህራሄ ሲባል ከእስር እንዲፈቱ መደረጉን አብራርተዋል።

በመዝገቡ የተካተቱ ተከሳሾች ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራር የሰጡ ግለሰቦቦች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ከእስር እንዲፈቱ የተወሰነላቸው ስድስት ግለሰቦች የአሸባሪው ቡድን ስራ አስፈጻሚ አባል ያልነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። በክስ መዝገቡ የተካተቱ ሌሎች ተከሳሾች የክስ ሂደቱ ግን ይቀጥላል ብለዋል።

አገር መልከ ብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ስትገባ ችግሮቹን ለመፍታት በመደበኛ የፍትሕ ስርዓቱ መሰረት መፍትሄ ስለማያገኙ የሽግግርና የተሃድሶ ፍትህ ተመራጭ የሚደረግበት አውድ እንዳለ ጠቅሰዋል።
በዚህም በኢትዮጵያ ባለው ነባራዊ ሁኔታ የአገር ህልውና ለማስጠበቅ በኢትዮጵያ ከመደበኛው ፍትህ ስርዓት ይልቅ በተሃድሶ የሽግግር ማዕቀፍ እልባት መስጠት ተገቢነት እንደለው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ አገራዊ መግባባትና መስማማት የሚያስፈልጋቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ ለመነጋገር እስካሁን የተደረገ ሁሉን አቀፍ አገራዊ ምክክር አለመኖሩን ያስታወሱት ሚኒስትሩ ይህ በታሪካችን የመጀመሪያ መሆኑን ተናግረዋል።

አገራዊ ችግሮች ከፖለቲካ ልሂቃኑ አልፈው በማህበረሰቡ ዘንድ እየተንጸባረቁ በመሆኑ አገራዊ ቀውሱ ወደ ትውልድ እንዳይሻገር በበቀል ፍትህ ሳይሆን በምክክርና በውይይት መፈጸም የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ባለፉት ሶሰት ዓመታትም ሆነ ቀደም ሲል ባጋጠሙ የመብት ጥሰቶች የአገር ህልውና ታሳቢ ባደረገ መልኩ በተሃድሶ የሽግግር ማዕቀፍ መፈትሄ መስጠት እንደሚገባ ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል ነው ያሉት።

በፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ላይ ክሳቸው እንዲቋረጥ የተደረገው አቶ ስብሐት ነጋ፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አቶ ዓባይ ወልዱ፣ አቶ አባዲ ዘሙ፣ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ አቶ ኪሮስ ሐጎስ፣ አቶ ጃዋር መሐመድና በእርሳቸው መዝገብ የተከሰሱ እንዲሁም አቶ እስክንድር ነጋና በእርሳቸው መዝገብ የተከሰሱ መሆኑ ይታወቃል።
ኢዜአ

Leave a Reply