ትህነግ ወደ”መቆላመጥ ፖለቲካ” አደገ፤ “መልካም ጎረቤት ያስፈልገናል” ደብረጽዮን

ላለፉት ሶስት ዓመታት ራሳቸውን ” መንግስት” የሚሉት፣ በድርጅት ደግሞ ላለፉት ሃምሳ ዓመታት የትግራይ ሕዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ሲል ራሱን የሚጠራውን ትህነግን የሚመሩት ዶክተር ደብረጽዮን ” መልካም ጎረቤት ያስፈልገናል” ማለታቸው ተሰማ። መልካም ጎረቤት እንደሚፈልጉ በጠቀሱበት የመጀመሪያው አንቀጽ “… አምባገነኑ ኢሳያስ ላይ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ ከጨዋታ ውጭ መሆን አለበት” የሚል ሃሳብም አስፍረዋል። በአፋር ህዝብ ላይ ጥቃት፣ በምድሩ ላይ የጀመሩትን ዳግም ወረራ ማጠናከራቸው ተስምቷል።

“የትግራይ መንግስት ፕሬዝዳንት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለዓለም ኣቀፍ ማህበረሰብ የፃፉት መልእክት ” ሲል የክልሉ የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በፌስ ቡኩ ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ እንዳለው በኢትዮጵያ ሰላም እንዲመጣ የተጀመረው “ድርድር” እንዲቋጭ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በቅድሚያ ጠንካራ እርምጃ ተወስዶባቸው ከጨዋታው ሊወገዱ እንደሚገባ ተመልክቷል።

ከትግራይ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ ሃይል አሰልፎ መገስገስ በወታደራዊ ዕውቀት “ድንቁርና” መሆኑንን በመግለጽ የተቹት ኢሳያስ አፉወርቂ፣ ትህነግ የተጠቀመበት ስልት ስለውትድርና እናውቃለን ከሚሉ የማይጠበቅ ፍጹም ኋላ ቀር አመለካከት እንደሆነ በአገራቸው ቴሌቪዥን ማስታወቃቸውና መተቸታቸው ይታወሳል። የትህነግን ሽንፈትም “የአእምሮ መድረቅ” ውጤት እንደሆነ ማመልከታቸው አይዘነጋም።

“ሁሉም ሰው መልካም ጎረቤት ይፈልጋል” በሚል ርእስ ደብርፅዮን ያዘገጁትን ጽሁፍ ያተመውን ዘ አፍሪካን ሪፖርት ድረ ገፅ ጠቅሶ የክልሉ ኮሙኒከሽን ጽህፈት ቤት ያሰራጨው ጽሁፍ “ኢሳያስን አስወግዱልን” የሚል ተማጽንዖ ያቀረበው አንድ የቀረራቸውን ጎረቤታቸው አፋርን ሙሉ በሙሉ ማጣታቸውን ተከትሎ ነው።

“አሁን በኢትዮጵያ ወስጥ ያለውን ጦርነት በሰላማዊ ድርድር ለመቋጨት እና ሰላም ለማምጣት ከተፈለገ ጣልቃ እየገባ ያለውን አምባገነኑ ኢሳያስ ላይ ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ ከጨዋታ ውጭ መሆን አለበት” ሲል ጽሁፉ የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብን ይለምናል። በዚህም ትህነግ በራሱ ምንም ነገር የማድረግ አቅሙ መዳከሙን እንዳመነ እንደሚቆጠር ነው በርካቶች ያመለከቱት።

“አምባገነኑ ኢሳያስ ባለፉት አስራ አራት ወራት በትግራይ ህዝብ ላይ ያካሄደውና እያካሄደ ያለውን ጭፍጨፋ ፋሽስት አብይና ተስፋፊው የአማራ ሃይል እንደቡራኬ ተቀብለውታል” የሚለው ደብረጽዮን “ዋና አላማ” በማለት ኢሳያስን ለዓለም አቀፍ ህበረተሰብ ሲከስ “ህወሓትን ለማጥፋት ብሎም በኢትዮጵያ ማህበረሰብ የተገለለ የትግራይ ህዝብ ለመፍጠር ነው” በማለት ነው። ይህን ያዩ ” ትህነግ ተሞላቀቀ” ሲሉ የፖለቲካ እድገቱን ጎረቤቶቹ እንዳሞላቀቁት ልጅ ዓይነት ማድረጉን ገልጸዋል።

ጽሁፉ “ተሳፋፊው” የሚለውን አማራ፣ ” ፋሽስት” ሲል የሚጠራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የእንግሊዘኛውን ጽሁፍ በአማርኛ ቋንቋ ተርጉሞ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ሊያማና ሊያሳጣ ይሞክራል። ከነሱም በላይ ለኢትዮጵያና ለአማራ ህዝብ ቅርብ፣ ተወዳጅ እንደሆነ አድርጎ ትህንግን ያቀረቡት ጸሃፊው ትናንት ” ዋጋ የለህም፣ እጅህን ስጥ” እያሉ መፎከራቸውንና ጭፍራቸው በወረራቸው የፋርና የአማራ አካባቢዎች የፈጸመውን ጉድ በድርቅና የሸመጠጠ ሆኖ ተወስዷል። መሳቂያም አድርጓቸዋል። ትህነግ ስለ ኢትዮጵያም ሆነ ስለህዝቧ የመናገር ሞራሉ ከምድር በታች እንደሆነ የመረዳት አቅሙ የነተበ እንደሆነም ያሳየ እንደሆነ ተመልክቷል።

“የተስፋፊው የአማራ ሃይል ዓላማ የትግራይ ህዝብን በማዳከም አማራ ብቻ የሚቆጣጠረው የድሮ ዘመን ስርዓት ለመመለስ ያለመ መሆኑን ጽሑፉ አመላክቷል” ሲል ቢሮው በትርጉም ጽሁፉ ገልጿል። በማኒፌስቶ አማራን “ጠላት” ብሎ በመፈረጅ፣ በትምህርት ቤት ሳይቀር አማራ ላይ ጥላቻ ሲያስተምር የኖረው ትህነግ ለምን የበላይነትና የበታችነት አስተሳሰብን በተደጋጋሚ እንደሚያነሳ በርካቶች እንደማይገባቸው በተደጋጋሚ የሚያነሱት ጉዳይ ነው። የአማራን ክልል ወሮ አውድሞ፣ ዘርፎና ንጹሃንን ጭፍጭፎ በሽንፈት ክልሉን የለቀቀው ትህነግ፣ ስለ መልካም ጉርብትና በእንግሊዘኛ ያሰራጨው ጽሁፍ ይህን ባደረገ በአጭር ጊዜ ውስጥ መሆኑና አሁንም አፋር ላይ ዳግም ወረራ እያካሄደ ባለበት ወቅት መሆኑ አስገራሚ መሆኑንን በጽሁፉ ግርጌ የተሰጡ አስተያየቶች ያመልክታሉ።
“አምባገነኑ ኢሳያስ ከፋሽስት ቡደኑና ከተስፋፊው የአማራ ሃይል በመተባበር በትግራይ ህዝብ የጀኖሳይድ ጦርነት የከፈተበት ሌላኛው ምክንያት የትግራይ ህዝብ መሰዋእትነት ከፍሎ ያረጋገጠውን ለ30 አመታት የተገነባው የኢትዮጵያ የፌዴራል ስርአት በመበታተን በአፍሪካ ቀንድ በወታደራዊና በፖለቲካ ፈላጭ ቆራጭ ሆኖ ለመውጣት የነበረው ህልም ለማሳከት ነው” ሲል ጎረቤቶቹን እየወረረና ለትግራይ ሕዝብ ጠላት እያመረተ ለምስራቅ አፍሪቃ ተቆርቋሪ እንደሆነ ያትታል።

“መንግስታቸው” ሲል የዶክተር ደብረጽዮንን ክልል የጠራው ጽሁፍ “ለሰላም ዝግጁ መሆኑንና የሚታሰበው ሰላም ለማሰፈን ደግሞ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ የገባው አምባገነኑ ኢሳያስ ከጨዋታ ወጭ መሆን እንዳለበት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ ነው” በሚል እንዳዘጋጁ ተመልክቷል። ቀደም ሲል የትህነግ አመራሮችና ጽንፈኛ ደጋፊዎች ” ኢሳያስን አሽቀንጥረን በመጣል ታላቋን ተጋሩ እስከ ደጋማው የኤርትራ ክልል በመዝለቅ እንመሰርታለን” በሚል ይህን ለማድረግ ፍጹም እንደማይቸገሩ ሲያስታውቁ ነበር። ይህ ቀርቶ አሁን ” ኢሳያስን ከጨዋታ አስወጡልንና ሰላም ይወርዳል” በሚለው ልመና መተካቱ አብዛኞችን አስገርሟል። ይህን ልመና ለማን ለማሳወቅ በአማርኛ መተርጎም እንዳስፈለገና ራስን ዝቅ የሚያደርገው የልመና ጽሁፍ የመሰራጨቱ ጠቀሜታ እንዳስገረማቸው አሁንም አስተያየት ሰጪዎች አክለው ገልጸዋል።

“የዓለም ማህበረሰብ የዘነጋው ጉዳይ ቢኖር ይላል” ጽሁፉ፣ “አብይና ኢሳያስ በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል እርቅ አውርደናል ብለው የተፈራረሙት የጋራ ስምምነት በሁለቱም ሀገራትና ህዝቦች ሰላም ለማውረድ ሳይሆን ተባብረው በትግራይ ህዝብ ላይ ጀኖሳይድ ለመጸፈም ነበር” ሲል ይከሳል። ነገር ግን ጽሁፉ ጦርነቱ እንዴትና በማን፣ ለምን እንደተጀመረ አቶ ሴኮ ቱሬና ጻድቃን ገብረትንሳኤ በግልጽ በአማርኛ ቋንቋ ጀግና መሆናቸውን ለማሳየት የሰጡትን ምስክርነት የማስተባበል አቅም የለውም።

ለውጡን ተከትሎ “ሂድ” ሳይባል ወደ መቀለ የሸሸው ቡድን ዳግም ወደ ስልጣን ለመመልሰ በክህደት ከጀርባቸው የወጋቸውን ድርጅት የሚመሩት ደብረጽዮን ያዘጋጁት ጽሁፍ ትርጉም መሰራጨቱ፣ በክህደት የታረዱትን የኢትዮጵያ ልጆች ደምና አጥንት ያስታወሰ ሆኗል። ኤርትራ ሸሽተው የገቡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ የተፈጸመንና የጦርነቱ ዋና መነሻ ምክንያት መደበቅ የማይችለው ይህ ጽሁፍ፣ በወገን ላይ የደረሰውን ግፍ ከማስታወሱ በላይ የድርጅቱን አመራሮች ይሉኝታ ቢስነት፣ ህሊና አልባነትና የማስተዋል ልዕላናቸው መንተፉን የሚያሳይ ሆኗል። ጽሁፉ ድርጅቱ “የተጠራቀመ የአዕምሮ ንቅዘት ውጤት ነው” በሚል ቀደም ሲል ምግባሩን አይተው ያወገዙት የተናገሩትን የሚያስታውስ ሆኖ ተገኝቷል።

ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለአለም ማህበረሰብ ያስተላለፉት መልዕክትም በትግራይ ጦርነት ብሎም በኢትዮጵያ ጉዳይ ዋና ተዋናዩ ኢሳያስ መሆኑናቸውን፣ ሰለማዊ ድርድር ውጤታማ እንዲሆንና የሚታሰብው ሰላም እውን ለማድረግ ከተፈለገ በአምባገነኑ ላይ ጠንካራና ተስፋ የሚያስቆረጥ እርምጃ በመውሰድ ከጨዋታው ውጭ ማድረግ እንደሚገባ ትህነግ ደጋግሞ ለምኗል። ለጦርነቱ መነሳት ሌላ ስዕል በመስጠት ዓለም እንዲያግዛቸው የለመኑት የትህነግ መሪ ” ይህ ካልሆነ ግን የሚታሰበው ሰላም ሊመጣ አይችልም” ማለታቸው ተመልክቷል። ጻድቃንም “ውጊያው አልቋል። ከማን ጋር እንደራደራለን” ባሉበት አንደበታቸው ” ኢሳያስን አስወግዱልን” ሲሉ ለደብረጽዮን ከተዘጋጀላቸው ጽሁፍ በፊት የገል ሃሳባቸው መሆኑንን ጠቅሰው ጽሁፍ መበተናቸው አይዘነጋም።
“በኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት ከተፈለገ አምባገነኑ ኢሳያስ ኣፈወርቂ ከጨዋታ ውጭ መሆን አለበት” ሲሉ በጽሁፋቸው ደጋግመው ለዓለም መንግስታት የተማጸኑት የትህነግ መሪ፣ ይህን ባሉ በሁለተኛው ቀን አፋር ላይ እያካሄዱ ያሉት የከባድ መሳሪያ ድብደባ ሰላሙን የሚያፋጥን፣ ለትግራይም መልካም ጎረቤት የሚፈጠርበት ዘዴ ስለመሆኑ ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።

“የትህነግ አመራሮች የዕርዳታ አልሚ ብስኩት እየተመገቡ፣ የሚወጓት አገር ነዳጅና መድሃኒት እያቀረበችላቸው፣ ዓለም ከነሱ ጋር ሆኖ ሲጮህ ስለቆየ ‘ቁልምጥ’ ፖለቲካ ጀመረዋል። የፖለቲካው ጨዋታ መቀየር አልገባቸውም። የሱዳን የፈጥኖ ደራሽ አዛዥ ጀነራል አዲስ አበባ መጥተው መማማላቸውም አላነቃቸውም።የዓለም አውራ አገሮች ለራሳቸው ፍልጎት ሲል አቆላምጠዋቸው ስለነበር፣ እዛው ላይ ተቸክለዋል። በዛው ቁልምጥናቸው ሊቀጥሉ ይመኛሉ። ፖለቲካ በቆሞ ቀር አስተሳሰብ አይመራም። ከድንፋታና ከትምክህት ወጥተው ለቅሶ ላይ መሆናቸውን በቁልምጥና ፖለቲካና ሊሸፍኑት ይወዳሉ። ይህ ክስረታቸው ነው” ሲሉ በርካቶች አዲስ የፖለቲካ ፖለቲካ መጀመሩን እሱም ” የመቆላመጥ ፖለቲካ” እንደሚባል ገልጸዋል።

Leave a Reply