የአሶሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሃሰተኛ የብር ኖት ከነማባዣ ማሽን እና ተጠርጣሪው ጋር ዛሬ በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ፡፡

የፖሊስ መምሪያው ሃላፊ ኮማንደር ቡሽራ አልቀሪብ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪው በከተማው ወረዳ ሁለት ቀጠና አንድ በተለምዶ የማረሚያ ሠፈር ነዋሪ ነው፡፡

ፖሊስ የህብረተሰቡን ጥቆማ መሠረት በማድረግ በተጠርጣሪው ቤት ባደረገው ፍተሻ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጋ ሃሰተኛ ባለ 200 አዲሱን የብር ኖት አግኝቷል ብለዋል፡፡

ከሃሰተኛ ብሮች በተጨማሪ በ”ኤፎር ሳይዝ” በህትመት ላይ ያሉ በርካታ ወረቀቶችም መገኘታቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ከሃሰተኛ የብር ኖቱ ባሻገር ተጠርጣሪው ሀሰተኛ የብር ኖት የሚያትምበት ማሽን፣ ኬሚካል፣ ቀለም እና ሌሎችም ቁሳቁሶች በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች፣ ተጠርጣሪው ድርጊቱን ለመፈጸም ገንዘብ የሚለዋወጥበት ከፍተኛ የብር መጠን የያዙ የተለያዩ የባንክ ሂሳብ ደብተሮችም እንደተገኙ አመልክተዋል፡፡

የከተማዋ አስተዳደር ፖሊስ ባለፉት ሁለት ወራት የሃሰተኛ የብር ኖት ምንጩን ለማግኘት እልህ አስጨራሽ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ያስረዱት ኮማንደር ቡሽራ ባለፈው ሳምንት የዛሬውን ሳይጨምር በአሶሳ 60 ሺህ የሚጠጋ ሃሰተኛ የብር ኖት በቁጥጥር ስር መዋሉን አስታውሰዋል፡፡

ከግለሰቡ ጋር ተባባሪ የነበረ አንድ ተጠርጣሪ ለጊዜው መሰወሩን ጠቁመው፤ ፖሊስ ቀሪ የሃሰተኛ ገንዘብ ምንጮችን ለማድረቅ ምርመራ እና ክትትሉን አጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡

ህብረተሰቡ በግብይት ወቅት ጥንቃቄ እንዲያደርግ ያሳሳቡት ኮማንደሩ፤ ችግሩ በዘላቂነት እንዲወገድ ጥቆማ የመስጠት ድጋፉን እንዲያጠናክር መልዕክት አስተላለፈዋል፡፡ (ኢ ፕ ድ)

Leave a Reply