በወለጋ ንጹሃን ላይ የተፈጸመውን የጅምላ ጭፍጨፋ ተከትሎ የመከላከያ ሰራዊት በይፋ የጀመረው የማጥቃት እርምጃ መቀጠሉን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ በርካታ ታጣቂዎች መገደላቸው፣ መማረካቸው፣ የማሰልጠኛና መልሶ መደራጃቸው እንደተደመሰሰ ተሰማ። ድርጅቱ በይፋ አላስተባበለም።

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሃላፊ ሚኒስትር ዝርዝር ባይጠቅሱም ዝግጅት ክፍላችን ባገኘው መረጃ በምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ ላይ የመከላከያ ሰራዊት ሰፊ ውጤት አስመዝግቧል። የኦነግ ሸኔ መቀመጫ እንደሆነ በሚታወቀው የቤጊ ወረዳ ቴንዘ ቀበሌ ሾንጋ የበሌ በሚባል ስፍራ እንደ ጦር ካምፕ ሲጠቀምበት ነነበረውን ካምፕ ውስጥ መሽጎ የነበረ ሃይልና ቁስ ሙሉ በሙሉ ተድምሧል።

ሰኔ 23 ቀን 2014 ዓም ማለዳ በግምት ከአንድ ሰዓት አካባቢ ተጀምሮ ለአራት ሰዓት በተካሄደ ኦፕሪሽን በተወሰደ እርምጃ አርባ አምስት የኦነግ ሸኔ የሽብር ቡድኑ ታጣቂ ሃይሎች መገደላቸውን ለማወቅ ተችሏል። ሰላሳ አምስት ክላሽንኮቭ ጠመንጃና ሁለት ታጣቂዎች ከጥቃቱ ተርፈው ተማርከዋል። የተቀሩትም መሸሻቸው ተመልክቷል።

በምስራቅ ወለጋ ቢላ ወረዳ ልዩ ቢሎና ጎቤ በተባለ አካባቢዎች በጉማባስ የሚመራው የሸኔ ታጣቂዎች ቡድን የመከላከያን ጥቃት መቋቋም አቅቶት ተብትኖ መሸሹ ተመልክቷል። በተበተነው በዚህ ሃይል ላይ መከላከያ እግር በግር እየተከተለ የመቃረም ስራ እየሰራ መሆኑንን ዜናውን ያቀበሉን አመልክተዋል። ይህ መከላከያ አስመዘገበው የተባለው ድል በድርጅቱ በይፋ ማስተባበያ አልቀረበበትም። ሸኔ ይቆጣተራቸው የነበሩ ስፋራዎች በቁጥጥር ስር ውለው የቀድሞ የአስተዳደር መዋቅር ለመዘርጋት የፖለቲካ ስራ እየተሰራ መሆኑ ተመልክቷል።

ከአሁን በፊት የተወሳሰበ የጸጥታ ችግር የነበረባቸውን የኦሮሚያ፣አማራና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በተወሰደ የህግ ማስከበር ዘመቻ የተሻለ ሰላም እንደፈጠር ማድረጉን መንግስት ትናንት ማስታወቁ ይታወሳል። በነፍስ ግድያ፣በሽብር ተግባር እና ሌሎች ህገወጥ ተግባራት ተሳትፎ የነበራቸውን አካላት በቁጥጥር ስር በማዋል ህጋዊ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝም ተጠቁሟል።

እየተወሰደ በሚገኘው ህግ የማስከበር ተግባርም ለሽብርና ህገወጥ ተግባራት ሊውሉ የነበሩ ተሽከርካሪዎች፣አደንዛዥ ዕፆችና ሌሎች ቁሳቁሶች መያዛቸውን በጅምላ ዶክተር ለገሰ ቱሉ አምልክተዋል። በሽብር ቡድኖችና ኢ-መደበኛ አደረጃጀቶች ላይ በተወሰደ እርምጃም በርካታ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ማድረስ ተችሏል ብለዋል። በኦሮሚያ ክልል ቶሌ ቀበሌ በንጹኃን ዜጎች ላይ ጉዳት ባደረሱ የሽብር ኃይሎች ላይ የተቀናጀ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ እና የሽብር ቡድኖቹ የሚንቀሳቀሱባቸውን አካባቢዎች መቆጣጠር እየተቻለ መሆኑን ትናንት በመግለጫቸው አካተዋል።

ራሱን የኦነግ ጦር እያለ የሚጠራው ታጣቂ የወለጋውን እልቂት ጦራቸው አለመፈጸሙን በቅጽበት እንዳስተባበሉት ሁሉ ይህንን በተለመደውና ሃሳባቸውን በሚገልጹባቸው ሚዲያዎች አልስታወቁም። ይህ እስከታተመ ድረስ ከድርጅቱ የወጣ መረጃ ባለመኖሩ ማካተት አልተቻለም።


Leave a Reply