ዐቃቤ ህግ የኮንዶሚኒየም እጣ እንዲጭበረበር አድርገዋል የተባሉት ላይ በሙስና ወንጀል ክስ መሰረተ

ዐቃቤ ህግ የኮንዶሚኒየም እጣ እንዲጭበረበር አድርገዋል የተባሉት የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ የነበሩትን ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱን ጨምሮ 11 ተከሳሾች ላይ በሙስና ወንጀል ክስ መሰረተ

ተከሳሾች፡-1ኛ. ዶ/ር ሙሉቀን ሀብቱ ምሩፅ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የቢሮ ኃላፊ የነበረ) 2ኛ. አቶ አብርሃም ሰርሜሎ ኪዳኔ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ ምክትል የቢሮ ኃላፊ የነበረ ) 3ኛ. አቶ ኩምሳ ቶላ ገኖ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የአይሲቲ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበረ ) 4ኛ. አቶ መብራቱ ኪ/ማርያም በርሄ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ሲስተም ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር የነበረ) 5ኛ. አቶ ስጦታው ግዛቸው ደገፋ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ፕሮግራመር የነበረ) 6ኛ. አቶ ባዩልኝ ረታ ጸጋ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ፕሮግራመር የነበረ) 7ኛ. አቶ ሚኪያስ ቶሌራ ወ/እየሱስ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሲስተምና ዳታ ቤዝ ባለሙያ የነበረ) 8ኛ. አቶ አሚ አምባዬ ማሞ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ፕሮግራመር የነበረ) 9ኛ. አቶ ዮናስ ወ/ጊዮርጊስ ነዳሳ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የመረጃ ባለሙያ የነበረ) 10ኛ አቶ ዘካርያስ አያለ ገቢ (በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የሲሰተም ዳታ ቤዝ አድሚንስትሬተር) 11ኛወ/ሮ ኤደን ካሳሁን ተሰማ ሲሆኑ ዐቃቤ ህግ 3 ክሶችን የኢፌደሪ ፍትህ ሚኒስተር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዐቃቤ ህግ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት በትላንተናው ዕለት ክስ መስርቶባቸዋል፡፡

የሙስና ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀኔራል ዐቃቤ ህግ በ1ኛ የክስ ዝርዝር 1ኛ ፣2ኛ እና በ3ኛ ተከሳሾች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊነት ላይ ተመድበው ሲሰሩ የማይገባ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በማሰብ ስልጣናቸውን ወይም ሃላፊነታቸውን ተጠቅመው በሀምሌ 01 ቀን 2014 ዓ/ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶች እድለኞችን በፍትሃዊ የሎተሪ እጣ በሲስተም ለመለየት ተብሎ ከወጣው የ14ኛ ዙር የ20/80 እና የ3ኛ ዙር የ40/60 የወጣበትን ሲስተምን የማልማት፣ እጣ የማውጣት እና የኮንደሚኒየም ቤት የቁጠባ ተመዝጋቢዎችን የዳታ ቅብብሎሽ ሂደትን በተሰጣቸው ኃላፊነት መሰረት ሊከላከሉት፣ ሊጠብቁት እና የጥራት ደረጃውን በጠበቀ መንገድ ለውጤት ማብቃት ሲገባቸው 1ኛና 2ኛ ተከሳሾች በስራ ሃላፊነታቸዉ ሊጠብቁትና ሊከላከሉት የሚገባዉን የመንግስትና የህዝብ ጥቅም ወደጎን በመተዉ እድለኞችን መርጦ የሚያወጣ ሲስተምን የማልማት የፕሮጀክት ስራ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ እንዲለማ ማድረግ ሲገባቸው ሲስተሙ በትክክለኛ መንገድ ባለማበት እና ደህንነቱ ባልተጠበቀበት ሁኔታ ፡ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ለሲስተሙ የደህንነት ማረጋገጫ ሳይሰጠው ለእጣ ማውጣት እንዲወል በማድረግ፣ እጣው ዝቅተኛውን የቁጠባ መስፈርት የሚያሟሉ፤ ከአዲስ ተመዝጋቢነት ወደ ነባር ተመዝጋቢት የተቀየሩ፤ ቁጠባቸውን ያቋረጡ ግለሰቦች የእጣው ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ክፍተት እንዲፈጠር በማድረጋቸው 3ኛ ተከሳሽ የተመዝጋቢዎች ዳታ እንዳይቀየር መጠበቅ እና መከላከል ሲገባው ዳታው ተጋላጭ እንዲሆን በማድረግ ህገ-ወጥ ጥቅሞችና ጉዳት እንዲደርስና እጣዉን ለመሰረዝ የሚያበቃ ከፍተኛ ክፍተት እንዲፈጠር በማድረጋቸዉ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈጸሙት የመንግስት ስራን በማያመች አኳኋን በመምራት ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

See also  ‹‹ በምርጫው ሂደት በጥላቻ ንግግር ላይ የሚሰማሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አመራርና አባላትን በህግ የመጠየቅ ስራ ይሰራል›› አቶ አወል ሱልጣን በጠ.አ. ህግ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ

2ኛ ክስ ከ4ኛ እስከ 10ኛ በተጠቀሱት ተከሳሾች ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን 4ኛ ተከሳሽ የእጣ ማዉጫ ሶፍትዌሩን በበላይነት የሚመራዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቴክኒክ ሙያ ስልጠናና ቴክኖሎጂ ልማት ቢሮ የሶፍትዌር ሲስተም ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በመሆኑ ህገወጥ ድርጊቱን ማስቆም ሲገባዉ በድርጊቱ ተባባሪ በመሆንና የራሱንም ስም በማስገባት እጣ እንዲወጣለት በማድረጉ፤ 5ኛና 6ኛና ሶፍተዌሩን እንዲያለሙ፣7ኛ ተከሳሽ ደግሞ ከቤቶች የተዘጋጀዉን ዳታ እንዲያስተዳድር የተሰጣቸዉን ሃላፊነት ወደጎን በመተዉ እርስ በዕርሳቸዉና ከ8ኛ፣ 9ኛ እና 10ኛ ተከሳሾች ጋር በጥቅም በመመሳጠር ለእጣ ብቁ ያልሆኑ ሰዎችን ብቁ እንደሆኑ በማስመሰልና በእጣዉ ዉስጥ በማካተት አብዛኛዎቹ እጣ እንዲወጣላቸዉ በማድረግ በህዝብና በመንግስት ጥቅም ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ያደረጉ በመሆኑ በዋና ወንጀል አድራጊነት በፈፀሙት በስልጣን አለአግባብ መገልገል የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡

3ኛ ክስ 5ኛ እና ከ7ኛ እስከ 11ኛ የተጠቀሱት ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን ተከሳሾች ገንዘቡ የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ ወይም ማወቅ ሲገባቸው በስማቸዉ በከፈቱት የባንክ ሂሳባቸዉ ላይ እንዲገባ በማድረግና እርስ በርሳቸዉ በማስተላለፍ በዋና ወንጀል አድራጊነት ተካፋይ በመሆን በፈፀሙት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ ወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡

ከ10 ኛ እና 11ኛ ተከሳሽ ውጪ ያሉት ሁሉም (9ኙ) ተከሳሾች ፍ/ቤት ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ተደርጓል ቀጣይ ቀጠሮዎችን ተከታትለን የምናሳውቅ ይሆናል፡፡

Leave a Reply