ደብዳቤ ለኢትዮጵያ – ከቢልለኔ ስዩም

– ኢትዮጵያዬ ይህንን ደብዳቤ ስደመድም የምመኘው ሦስት ነገሮችን ብቻ ነው። እነርሱም፣

ውድ ኢትዮጵያ

ትናንት ከሰዓት በኋላ አራት ኪሎ የሚገኘውን የሳይንስ ሙዚየም ፕሮጀክት ስፍራ ተዘዋውሬ ስመለከት እና በብራማ አሉሙኒየም የተሸፈነውን ባለጉልላት የቴአትር ማሳያ ስመለከት የመደነቅ ስሜት ወረረኝ። በዓይነ ሕሊናዬ የቴአትር ስፍራው ግንባታ ከተጠናቀቀ በኋላ በብዙ ሰዎች፣ ወጣቶችና አዛውንት ተሞልቶ፣ ደረጃዎቹን ወጥተው ወደ አዳራሹ ሲገቡ፣ መቀመጫዎቹን ሲይዙና ትርዒት ወይም ፊልም ለማየት ሲታደሙ ታየኝ። ከግማሽ ሰዓት በኋላ በሸገር ፕሮጀክት የሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክት የአበባ መናፈሻ፣ ትንሹ የእግር ኳስ ሜዳ እና የህፃናት መጫወቻ ስፍራ መካከል ሳልፍ በህይወት ዘመኔ አስቤ የማላውቀው ሀሳብ ውስጤ ገባ። ዝናብ ካረገዘው ሰማይ ጠብታዎች ወርደው በስሱ ፊቴን ሲዳስሱት ዳግመኛ የ20 ዓመት ወጣት ሆኜ ከዚህ መደነቅ እና መገረም ከሞላበት ቅጽበት አንስቶ አንቺን – ኢትዮጵያዬን ደግሜ ልኖርሽ ተመኘሁ። ያለሽን አቅም እና ቀስ በቀስ እየያዝሽ የምትገኚውን ገጽታ ወጣት ሆኜ ማጣጣም ፈለግሁ። ይህ መደነቅ እና ተስፋ በእነዚህ ስፍራዎች ብቻ የተወሰነ አይደለም። ከጥቂት ሳምንታት በፊት፣ የደህንነት ተቋማት እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎችሽን እና ተዛማጅ የልማት ክንውኖችሽን በጎበኘሁ እና ካስተዋልሁ ጊዜ አንስቶ ገደብ የለሽ ተስፋን በውስጤ ተክሏል!

ኢትዮጵያ

ሕይወቴን በሙሉ አውቅሻለሁ። ነገር ግን፣ ባለፉት አራት ዓመታት በቅርበት ላውቅሽ ችያለሁ። ብዙ ስፍራዎችሽን፣ ሸለቆዎችሽን እና ከፍታዎችሽን አካለልሁ። ባገኘሻቸው ድሎች እና ባጋጠሙሽ ፈተናዎች አብሬሽ ስቄ ካንቺው ጋር አልቅሻለሁ። በምድርሽ ተረማምጄ ከገጽታሽ ተላመድሁ፣ ስፋትሽንም ከከፍታሽ ሆኜ ተመለከትሁ። ከላይ እሰከ ታች፣ በስፋትሽና በርዝመትሽ ልጆችሽ ገና ሙሉ በሙሉ ባላወቅነውና የቱን ያህል ዕድለኛ መሆናችንን ባልተገነዘብንበት ልክ በገጸ በረከት ተሞልተሻል። ወዳጆችሽ ዞረው ጠላት ሲሆኑሽ አይቻለሁ። ጠላቶችሽ ተብለው የተቆጠሩ ደግሞ በችግርሽ ቀን አብረውሽ ቆሙ። ድብቅ የተፈጥሮ በረከቶችሽ የልጆችሽ አቅም እና የውጤታማነት ምናብ በተግባር የታየውን ያህል ሊገለጡ ጀምረዋል። ቀድሞ ለማሰብ እና እውን ለማድረግ የማይቻሉ ጉዳዮች ላባቸውን አንጠፍጥፈው በሚሠሩ ትጉሀን አማካኝነት ወደ መቻል እየቀረቡ ነው።

በተቸርሽው ጸጋ ላይ ብርሃን እንዲሆን ማልደው ጎህ ሳይቀድድ ሚነቁ እና ላባቸውን የሚያፈስሱልሽን አግኝቻለሁ። ደግሞም ያልደከሙበትን አመድ ለማድረግ የሚበረቱ ሰዎች ድርጊት እያስቆዘመኝ ብዙ ምሽቶችን በሃዘን ተጠፍንጌ አሳልፌያለሁ። ይኀውልሽ፣ ደክሞ ማፍራት የሚጠይቀውን ተግባርና ያለበትን ጉልበት ፈታኝ ዝለት የሚገነዘቡት ጥቂቶች ብቻ ናቸው። ወደዚህ ዓለም ሀሳብን አፍልቆ ወደ ፍሬያማነት የማድረሱን ብርቱ ትግል የሚያውቁት እና ልምዱን ያካበቱት ብቻ ናቸው ያንን ራዕይ መጠበቅ የሚያስከፍለውን ዋጋ የሚገነዘቡት። እናም ኢትዮጵያ፣ አንዳንዶች ህይወትን የሌሎች ጩኅት ላይ ፊት ብለው ሲንሸራሸሩባት፣ በጸጥታ በሚለፉት አያሌ ልጆችሽ ልትኮሪ ይገባል። አዝመራውን የሚሰበስቡት በጩኀት የተካኑት እና ድምጻቸው ገኖ የሚሰማው እሱ ወይም እሷ ሳይሆኑ፣ የፀሃይ ሀሩር ፊታቸውን ቢያከስላቸውም፣ የጽጌረዳው እሾህ መዳፋቸውን ቢሸነትረውም በጽናት የሚጓዙት እርሷ እና እርሱ ናቸው። ኢትዮጵያዬ፣ እንዲህ ያለው ዋጋ ስላንቺ ቢከፈል ይገባሻል! ዛሬ ያሉት፣ ነገም የሚመጡት ልጆችሽ ዋጋ ቢከፈልላቸው ተገቢ ነው።

አንዳንዶች ልጆችሽ አንዳንዱን ጊዜ ለምን ችላ ሊሉሽ እንደሚመርጡ አስበሽ ታውቂያለሽ? ያውም አንቺን የምታኖሪንን እና መጋቢያችንን? ለምንድነው የተንሰራፋሽበት ሰፊ ስፍራ ለሁላችንም እንደሚበቃን ለማመን ያልፈለግነው? እንዲያውም በብዙ ጸጋ ተትረፍርፈሽ ሳለሽ፣ እጦት ላይ ባተኮረ እሳቤ እና ሆን ተብለው በተሰመሩልን የልዩነት መስመሮች ላይ ተመስርተን ፍትጊያን መቆስቆስን ለምን እንደምንመርጥ ትጠይቂናልሽ?

ኢትዮጵያ፣ ብዙ ጊዜ ልጆችሽን አስተውለሽ በዚህች ምድር ካንቺ የወረስነው ግዛት የተትረፈረፈ ግዛት ሳለ ለምን የተጋራነውን ሰብአዊነት እንደምንጥል፣ የጋራ ሀላፊነታችንን እንደምንተው እና አንድነታችንን በየጥቃቅኑ ጉዳይ አሽቀንጥረን እንደምንጥል ትጠይቂ ይሆን? በየማለዳው ታጥቀው ከእንቅልፋቸው የሚነቁ እና ለአንቺ ዘብ ለመቆም እና አንቺን ለማሳደግ ዝግጁ የሆኑ ንቁ እና ለህሊናቸው የሚገዙ አስተዋይ ልጆችን አሳድገሻል?

ይኀውልሽ፣ ትላንት ያሳለፍኩት መደነቅና መገረም ምንጩ ከልዩ ባለመብትነት የተገኘ አይደለም። ከምርጫ የመነጨ ነው። ምርጫውም ተስፋ ማድረግ ነው። ተስፋ ማድረግ እንደ አገርም ሆነ እንደ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የደረሱብንን በርካታ ፈተናዎችና ችግሮች መካድ አይደለም። በአንጻሩ፣ ጽንፍ የረገጠ ተጠራጣሪነት ደግሞ አንዳችም ወደ ልህቀት የሚያደርስ ኃይል የለውም። ዛሬ ያለሽን ነገር፣ እንዲሁም አንዳንዶች በየዕለቱ የሚወስዱብሽን ተመልክቻለሁ። አንዳንዶች ሊለጉዱብሽ ከሚሞክሩት የጥላቻና መከፋፈል ክምር ስር ያለውን ግርማ ሞገስሽን አየዋለሁ። በብዙ ጥረትና አንዳንዴም ትርምስ በበዛበት ዛሬ ላይ ቆሜ፣ በረዥሙ ነገሽ ውስጥ ተስፋ ይታየኛል። ደግሞም በጸጥታ የሚደክሙት ብዙዎችም የሚያደርጉትን የሚያደርጉት የተሻለ ነገ ራዕይ በመመልከት ነው።

አዎን፣ ልጆችሽን የሚያሰቃዩ ብዙ ፈተናዎችና መከራዎች አሉ። ነገር ግን፣ ከብዙ ባለ ልዩ መብት ልጆችሽ መካከል ለመልካም ተግባር እና ለውጥ አራማጅ የመሆን አቅም እና ምርጫ ያላቸው ይገኙበታል።

ኢትዮጵያዬ ይህንን ደብዳቤ ስደመድም የምመኘው ሦስት ነገሮችን ብቻ ነው። እነርሱም፣

1. እስካሁን ያሳደግሻቸው ልጆች እኛን ለመስበር የሚታገሉትን የውጭ ኃይሎች በመተው፣ የተሰበሩትን ድልድዮች ጠግነው አንድ ለማድረግ ቆራጥነት እንዲኖራቸው፣

2. አንድ አንዶች ተስፋ መቁረጥን በመረጡበት ጊዜ ለልማትሽ መድከምን ብቻ የሚሊፉ የምታሳድጊያቸው ልጆችሽ ተስፋን እንዲመለከቱ፣ እና

3. የምትወልጃቸው ልጆችሽ ለሁሉም የምትበቃ፤ የበለፀገች ኢትዮጵያን ለማለም እና እውን ለማድረግ ድፍረት እንዲኖራቸው ነው።

ልጆችሽ እንደ መሆናችን፣ እያንዳንዳችን ቢያንስ አስቀድመን ራሳችን የመለወጥ አቅም እንዳለን እውቅና ሳይሰጡ ሁሉንም ጣቶች በአንድ ሰው ወይም የግለሰቦች ስብስብ ላይ መጠቆም፤ ተረዳድቶ የማደግ አቅምና ማንነታችንን መካድ ነው።

እራሳቸውን ወደ በጎ መለወጥ የቻሉ ግለሰቦች በቤተሰባቸው፣ ሰፈራቸው፣ ማኅበረሰባቸው፣ ከተማቸው፣ በመጨረሻም በሀገራቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥን የማምጣት አቅም አላቸው።

ኢትዮጵያ ልጆችሽ ለመንቃት ቆራጥነቱ እንዲታደላቸው ምኞቴ ነው!

ቢልለኔ ስዩም ሚያዚያ 23፣ 2014 አዲስ አበባ

Leave a Reply