“በትግራይ ክልል ከኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ውጭ በግዳጅ ላይ ያለ ሌላ የፀጥታ ሀይል የለም”

በትግራይ ክልል ከኢፌዴሪ የመከላከያ ሰራዊት ውጭ በግዳጅ ላይ ያለ ሌላ የፀጥታ ሀይል የለም፦ ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ

መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ለተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ፤ የአፍሪካ ህብረት ተወካዮች ፤ ከቀይ መስቀልና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለተውጣጡ አመራሮች በሰላም ስምምነቱ ትግበራ ዙሪያ ማብራሪያ ተሰጥቷል።

ማብራሪያውን የሰጡት የመከላከያ የውጭ ግንኙነት እና ወታደራዊ ትብብር ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ተሾመ ገመቹ ፤ የተፈጠረው የሰላም ስምምነት ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው ሀገራትም የሰላም አየር ለመተንፈስ አስችሏል ብለዋል።

የሰላም ስምምነቱን ወደ ተግባር ለመለወጥ ብዙ አበረታች ስራዎች መሰራታቸውን የገለፁት ጄኔራል መኮንኑ የመንግስት ከፍተኛ የሥራ ሀላፊዎች ጉብኝትን ጨምሮ በክልሉ ለሚገኙ ዜጎች የአገልግሎት መስጫ ተቋማት እንዲከፈቱ መደረጋቸውን ተናግረዋል።

ከሰላም ስምምነቱ በኋላ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ዜጎች ከሰባ ስምንት ፐርሰንት በላይ ዕለታዊ እርዳታ በመንግስት መቅረቡ የተገለፀ ሲሆን አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶችና መንግስታት የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ተጠይቋል።

በአፍሪካ ህብረት የተፈረመውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚታዩ አነስተኛ ችግሮችን በውይይት ለመፍታት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

ተሳታፊዎቹ በበኩላቸው የኢትዮጵያ መንግስት ለሰላም ስምምነቱ ተግባራዊነት በቁርጠኝነት እየሰራ በመገኘቱ ያላቸውን ምስጋና አቅርበው የሚያደርጉትንም ድጋፍ ለወደፊቱ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

ብዙአየሁ ተሾመ
ፎቶግራፍ ሀይለማርያም ተፈራ , የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት

See also  መከላከያ መቀለ 15 ኪ ዙሪያ፤"ያለፈው ስህተት አይደገምም" መሪዎች

Leave a Reply