ከኢዜማ የተለዩት አመራሮች ወደ ባልደራስን?

ቀደም ሲል የለቀቁትን ሰባት አመራሮች እግር ተከትሎ ተጨማሪ አርባ አንድ የኢዜማ አባላት ፓርቲውን መለየታቸው ይፋ ሆኗል። ፓርቲው ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን ሁኔታ የሚገመግም የጥናት ሠነድ አዘጋጅቶ ከአባላቱ ጋር መምከሩን አስታውቋል።

በጥቅሉ ኢዜማ ከብልጽግና ጋር ያለው ግንኙነት ትክክል እንዳልሆነ፣ የመሪው ዶክተር ብርሃኑ ነጋ መሾምም ትክክል እንዳልሆነ ሶስቱ አመራሮች የልዩነት መነሻና መድረሻ መሆኑንን በአንድ የዩቲዩብ አውድ አስታውቀዋል። በትግራይ የተደረገው ጦርነትንም ፓርቲው አቋም ይዞ እንዳልደገፈ በማስታወስ የፓርቲውን መሪ ኮንነዋል።

በዚሁ አልፋ በሚባል የዩቲዩብ አውድ ሰማያዊ ፓርቲን በክርከር አሸንፈው የተረከቡት አቶ የሺዋስ ” ለኢትዮጵያ ስንል ውሳኔውን ወስነናል። ለማስተካከል ብንጥርም አልሆነም” ሲሉ ተናግረዋል። በቃለ ምልልሱም ሆነ ባወጡት መግለጫ ስለወደፊት ዕቅዳቸው በይፋ ምን እንደሚያደርጉ ባያስታውቁም፣ በቅርቡ ራሱን ወደ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲነት ያሳደገውን ባልደራስን የመቀላቀል ዕቅድ እንዳላቸው እየተሰማ ነው።

ዶክተር ብርሃኑ ነጋና አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ኢዜማን እንዳፈረሱ፣ በፓርቲው ውስጥ ሌላ ፓርቲ እንዳቋቋሙ በገለጹበት ቃለ ምልልሳቸው፣ በርካታ ጉዳዮችን ቢያነሱም፣ በዋናነት ዶክተር ብርሃኑ የትምህርት ሚኒስትር መሆናቸው ከፓርቲው መርህ ውጭ እንደሆነ በገሃድ ተቃውመዋል። ይህ በሌሎች አገራት የተለመደ አሰራር እንዴትና በምን ምክንያት ኢትዮጵያ ውስጥ ሃጤያት ሊሆን እንደቻለ ትንታኔ ግን አልሰጡም። በጥቅሉ ” ብልጽግናን ለማርቅ አያመችም” ነው ያሉት።

አቶ ልደቱ እንደጠየቁት ” ፊት ለፊት ቀርበን እንነጋገር” ሲሉ ጥሪ ባቀረቡበት ቃለ ምልልስ አንድ አስተያየት ሰጪ ከውጭ አገር ” ታስራችሁ ነበር። ከእስር ተፈታችሁ ብሏል” በሚል ጠያቂው ስሜቱን ያንጸባረቀበትን ጥያቄ አንስቶ ሁሉም “ተፈተናል” ሲሉ የኢዜማ ቆይታቸውን ከቁም እስር ጋር አገናኝተዋል። በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው በርካታ ጉዳዮች ላይ የውስጥ ትግል ሲያደርጉ፣ ከሰፊ ክርክርና ፍጭት በሁዋላ በድምጽ እንደሚሸነፉ አስታውቀዋል። የፓርቲው መሪ ምርጫ ላይም በተመሳሳይ በድምጽ መሸነፋቸውን ” ተጠለፍን” ሲሉ አመልክተዋል።

በፓርቲ አሰራር ለአብዛኞች ድምጽ መገዛት ህግም፣ የአሰራር ተፈጥሮ እንደሆነ ቢታወቅም በኢዜማ በድምጽ መበለጥ እንዴትና ለምን ወንጀል ሊሆን እንደቻለ ጠያቂው አላነሳም። ከትህነግ ጋር የተደረውን ውጊያ እንደማይደግፉ፣ በሰላም እንዲቁጭ ዕቅድ ማቅረባቸውን ሲያስታውቁ፣ ትህነግን መቀለ ድረስ በመሄድ ለሰላማዊ ውይይት ፈቃደኛ እንዲሆን እናቶች እያለቀሱ ሲማጸኑ እንደነበር አስታውሶ ጥያቂው አልሞገተም። በዚህም ላይ ጦርነቱን ባይደግፉም በአማራና አፋር ክልል ላይ የተካሄደውን ወረራ አስመልክቶ ምን መደረግ እንደነበረበት ሲያመላክቱ አልተሰማም።

See also  I hope Taliban has revised its medieval view of the world

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መጋቢት 02/2015 ዓ.ም. ባደረገው 2ኛ መደበኛ ጉባዔው እንደ ሀገር እየሄድንበት ያለውን ፖለቲካ ሁኔታ በመገምገም ቀጣይ የትግል አቅጣጫዎችን የሚያጠና ግብረ ኃይል ማቋቋሙን አስታውሶ፣ በዚህ ሰነድ ላይ ውይይት አድርጎ ማዳበራሪያ አሳብ በመሰብሰብ ውይይቱን መቋጨቱን ከማስታወቅ በዘለለ ኢዜማ ስለተለዩት አባላቱ ያለው ነገር የለም። የፓርቲው መሪ ብርሃኑ ነጋ እንዲከሰሱ የቀርበውን አቤቱታ አስመልክቶም ምላሽ አልሰጠም።

ይልቁኑም ፓርቲው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባለፉት አምስት ዓመታት የነበረውን ሁኔታ የሚገመግም የጥናት ሠነድ ተዘጋጅቶ ከሚያዚያ 27/2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለያየ ጊዜ ብሔራዊ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በቂ ጊዜ ወስዶ ሰፊ ውይይት አድርጓል፡፡ በትላንትናው ዕለት ማለትም ግንቦት 13/2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ መካተት የሚገባቸውን ማስተካከያዎች እንዲጨመሩ በመስማማት የጥናት ሠነዱን ማጽደቁን ነው ያመለከተው። በቀጣይም ከብሔራዊ አመራር ጀምሮ በየደረጃው ላሉ መዋቅሮች ቀርቦ ውይይት በማድረግ ግብዓቶችን ለመሰብሰብ እንዲቻል መርሃ ግብር እንዲዘጋጅ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

ከተለዩ በሁዋላ መዘነጣጠልን ባህሉ ያደረገው የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ጎራ በተመሳሳይ የአብን አመራሮች አማራ ክልልና በፌደራል ደረጃ መሾማቸውን ይነቅፋል። ተጻራሪ ፓርቲዎች በአገር ደረጃ ልዩነታቸውን ጠብቀው፣ ሲያሻም አስወግደው አብረው መስራት፣ ጥምር መንግስት ማቋቋም፣ የካቤኔ አባል መሆን እጅግ የተለመደና ሊበረታታ የሚገባው ጅምር ሆኖ ሳለ መወንጀሉን በርካቶች ሲነቅፉት ስንብተዋል።

የመንግስትን ሹመት መቀበላቸው ለውግዘት የዳረጋቸው ኢዜማና አብን አብሮ ለመስራት የጀመሩት መሳሳብ የት እንደደረሰ ባይታወቅም፣ እስከ መዋሃድ የሚያደርስ ጉዞ የመጀመራቸው ዜና ወደፊት አማራ ክልል ላይ ምን አይነት ድርጅት ሊቋቋም እንደሚችል ጠቋሚ እንደሆነ አመላካች ተደርጎ ተወስዶ ነበር።

ውስጡ በችግርና በአመለካከት ልዩነት እየታመሰ ያለው አብን በአቶ ክርስቲያን ታደለ ጎታችነት አብሮ ሊቀጥል እንደማይችል የሚገልጹ፣ የአብንና ኢዜማ መቀራረብ ሁሉንም “ኢትዮጵያ” የሚለውን ማስመሳያ ጭንብል እንዲያወልቁ እንደሚያደርጋቸው አስቀድሞ ተገልሶ ነበር። እነዚሁ ወገኖች እንደሚሉ ይህ አሁን ይፋ ወደ መሆኑ እየተቃረበ ነው።

እስክንድር ነጋ በሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ የሚመራ ግንባር መቋቋሙን ይፋ አድርጎ፣ እሱም ወደ ትጥቅ ትግል መጠቃለሉን ሲያስታውቅ፣ ባልደራስ ብሄራዊ ፓርቲ መሆኑን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል። እስክንድር “አማራ ክልል ጀምረን ኢትዮጵያ ላይ እንጨርሳለን” ሲል ይፋ እንዳስታወቀው የባልደራስ ህብረ ብሄራዊ ድርጅት መሆን ለበርካቶች ቀላል የፖለቲካ ስሌት ሆኖላቸዋል።

See also  በኢትዮጵያ የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ሃላፊ እውነት በመናገራቸው በዕረፍት ስም መጠራታቸው አነጋጋረ

በሌላው ጎን አብንና ኢዜማም ይህንኑ በማስላትም ይሁን በሌላ ራሳቸውን አጽድተው፣ የሚራገፈውን አራግፈው፣ ጥንክረው ለመውጣት በጋራም ሆነ በተናጠል ስልት መንደፋቸው እንደማይቀር ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ግምታቸውን ያኖራሉ። አብን ውስጥ በጎንደር፣ በደሲና አካባቢው፣ በራያና ዙሪያው፣ እንዲሁም በወልደያና ሰሜን ሸዋ ተቀባይነት ያላቸው እንዳሉና ይህ ሃይል ቢለይ አብን ውስጥ የሚቀረው ሃይል ከጎጃም ውስን ቦታዎች ውጭ ብዙም ተቀባይነት እንደሌለው የሚገልጹ በቅርቡ ሁሉም እንደሚገለጥ ያምናሉ።

ኢዜማ ውስጥ አሁን የተሰማው ዜና ከላይ ካሉት የሂሳብ ቀመሮች ጋር የሚቃኝና በውጭና አገር ውስጥ ካለው ፖለቲካ ጋር ተናቦ የሚሰራ እንደሆነ ጉዳዩን ከሚያጦዙት አካላት ስሜት ውስጥ ማንበብ እንደሚቻል ስምምነት አለ። ከየአቅጣጫው ሚስጢሩን የሚያውቁ፣ የሰሙ፣ ድጋፍ የሚያደርጉ ወዘተ የሚሉትም ይህንኑ ነው።

በትምህርት ሚኒስቴር የተጀመረው ጥብቅ የትምህርትና የፈተና ቁጥጥር፣ የዲግሪና ዲፕሎማ ሸማቾችን ከማስደንገጡ ጋር ተያይዞ ዘመቻ የተከፈተባቸው ዶክተር ብርሃኑ፣ ሌላው የካቢኔ ባልደረባቸው የአብኑ ዶክተር በለጠ ሞላ የሚመሯቸው ሁለቱ ፓርቲዎች ውሳኔ የሚያጓጓውም ለዚሁ ይመስላል። ማን ስሌቱን በአሸናፊነት ይደመድመዋል? የሚለው ሲሰላ ቅድሚያ የሚመጣው ደግሞ እነማን የትና በእነማን ተቀባይ ናቸው? የሚለው፣ ከዚህም በላይ በማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ሳይሆን በጭብጥ ማን ይደመጣል? እነማንስ ናቸው ተጽዕኖ ፈጣሪዎች? እነማንስ ናቸው በተለያዩ ክልሎች ሰሚና ደጋፍ ያላቸው? የሚሉት ጉዳዮች ከምንም በላይ ቀልብ የሚስቡና የስሌቱ ማስያ ቅመሞች ናቸው።

ከኢዜማ የወጡትም ሆኑ ባልደራስ ያሰሉትን ስሌት ይፋ የማይናገሩ፣ ባልደራስ ለጠቅላይ ለመጫወት ቋፍ መድረሱን ይገልጻሉ። ባልደራስ የሚዲያ ድጋፍ ያለው ድርጅት በመሆኑ በቅርቡ ወደ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲነት ማደጉ ለዚሁ እርምጃ አመቺ ሁኔታ ለመፍጠር እንደሆነ የሚገልጹ፣ ከኢዜማ የወጡን ይቀላቀሉታል ብለው ያምናሉ። አለያም ፓርቲ መስርተው በጋር ተናበው ይሰራሉ።

Leave a Reply