ኦነግ በአማራ ክልል የተጀመረው ግጭት ወደ ኦሮሚያ እንዳይስፋፋ ጥንቃቄ ይደረግ አለ፤ “ፖለቲካዊ መፍትሄ” ብሏል

ኦነግ ሰሞንኛ ውጥረትን አስመልክቶ መግለጫ አውጥቷል። በመግለጫው አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጎልቶ የተስተዋለው አለመረጋጋት ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዳይሰፋና የበዛ ቀውስ እንዳይፈጥርም ጥንቃቄ መወሰድ እንዳለበት አሳስቧል። ቃል አቀባዩ አቶ ለሚ ገመቹም፤ «ኦነግ ጥሪ ሲያቀርብበት የነበረውና አሁንም የሚያምነው ለሚስተዋለው ፖለቲካዊ ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሆነው የውይይት መንገድ መፈለግ ነው» ማለታቸውን የጀርመን ድምጽ አስታውቋል።

ኦነግ ለፖለቲካ ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ እንደሚበጅ ቢያመላክትም ለአማራ ክልል ግጭት ይበጃል ያለውን የፖለቲካ መፍትሄ በግልጽ አላስቀመጠም። የጀርመን ድምጽ ያነጋገራቸው የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ አሁን አማራ ክልል እየተደረገ ያለውን ጦርነት የሚመሩት ክፍሎች ” ወለጋን ጨምሮ በርካታ አካባቢዎች የአማራ ናቸው፤ ኦሮሞ ጋት መሬት በኢትዮጵያ የለውም” በሚል ስለተሰጠው መግለጫ ጥያቄ አልቀረበላቸውም። በመግለጫውም ይህን አስመልክቶ የተባለ ነገር የለም።

«ኦሮሚያ የፍቅርና የሰላም ቀዬ መሆን ሲገባት ጸረ-ሰላምና ጸረ-ኦሮሞነት መርህን የሚያቀነቅኑ ተፈራርቀውባት ሰላሟን አጥታለች» ሲል መግለጫ ያወጣው የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በክልሉ ሰላም ማስፈን ይገባል ሲል አመለከተ። በኢትዮጵያ እየተስፋፋ መጥቷል ያለው ውስብስብ የፖለቲካ ሂደትም በኦሮሚያ የዜጎችን ሕይወት ክፉኛ ጎድቷል ያለው ኦነግ፤ ዘለቄታዊ መፍትሄ ሊሰጠው እንደሚገባም በመግለጫው ጠይቋል። የፓርቲው ቃል አቀባይ አቶ ለሚ ገመቹ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት ኦነግ መግለጫውን ባሁን ወቅት እንዲያወጣ ያስገደደው፤ «በኢትዮጵያ እየተከሰተ ባለው የስርዓት መሸራረፍ እና አለመረጋጋት የዜጎቻችን ደህንነት ስጋት ውስጥ መግባቱ ነው» ብለዋል።

ኦነግ በዚህ መግለጫ በተለይም ባለፉት አራት ዓመታት አገሪቱ መቋጫ በሌለው ግጭትና ጦርነት ውስጥ መግባቷ ከዴሞክራሲያዊ መብትም መጣስ ባለፈ የህልውና ፈተናን ደቅኖ ቆይቷል ብሏል። ፓርቲው በመግለጫ በተለያዩ ጊዜያት በአገሪቱ ፖለቲካዊ ውይይቶች እንዲደረጉ የቀረቡ ጥሪዎችም ተቀባይነት ማጣታቸው አሁን ለሚስተዋለው የከፋ አለመረጋጋት ምክንያት ነው ብሎ እንደሚያምንም ጠቁሟል። ኦነግ በመግለጫው አክሎም አሁን ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ ጎልቶ የተስተዋለው አለመረጋጋት ወደ ኦሮሚያ እንዳይሰፋና የበዛ ቀውስ እንዳይፈጥርም ጥንቃቄ መወሰድ አለበት ብሏል። ቃል አቀባዩ አቶ ለሚ ገመቹም፤ «ኦነግ ጥሪ ሲያቀርብበት የነበረውና አሁንም የሚያምነው ለሚስተዋለው ፖለቲካዊ ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሆነው የውይይት መንገድ መፈለግ ነው» ብለዋል።

See also  በምሥራቅ ወለጋ ዞን 312 የአሸባሪው ሸኔ አባላት እጅ ሰጡ

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ ኢትዮጵያ ባለፉት 3-4 ዓመታት እየገፋች ላለው የሰላም እጦትና ያለመረጋጋት መንገድ ለመውጣት ለውይይት ዕድል እሰጣለሁ ከማለት ቦዝኖ እደማያውቅ ተደጋጋሞ ይገለጻል። የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከበደ ዴሲሳ ይህንኑን በማስመልከት ዛሬ ለዶቼ ቬለ በሰጡት አስተያየት በኢትዮጵያ አለመረጋጋቶች መንግስታዊ ለውጥን ተከትሎ መከሰቱን አስታውሰዋል። «መንግሥት በሆደ ሰፊነት በውጪም የነበሩትን ኃይሎች ጭምር ወደ አገር እንዲገቡ አውድ አመቻችቶ ነበር። ያ በሂደት ውሎ አድሮ በየአከባቢው አለመረጋጋት ፈጥሯል።»

አሁን ላይ አማራ ክልልን ለከፋ የጸጥታ ችግር ዳርጓል ያሉት ክስተትም ከዚህ እንደማይለይ የገለጹት አቶ ከበደ በተለይም ለሁለት ዓመታት በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ የተጠቀሙ አካላት ትልቅ ስጋት ሆነዋል ነው ያሉት።

 ይሁንና መንግሥታቸው ጉዳዩን በሰላም ለመፍታት ከአገር ሽማግሌ እስከ የሃይማኖት አባቶች በመላክ ሰፊ ጥረት አድርጓል ያሉት አቶ ከበደ፤ አሁን አማራ ክልልን ጨምሮ በአገሪቱ በተለያዩ አከባቢዎች ላሉ ችግሮች ወታደራዊ እርምጃዎች የሚወሰዱት የሰላም መንገዱ በር ሲደፈን ብቻ ነው ብለዋል። «የዜጎች እንቅስቃሴ በመገደብ መከላከያ ሠራዊቱ ከቦታ ቦታ እንዳይሄድ በማድረግ የሰላም ጥረቱ ፍሬ እንዳላፈራ በመታየቱ ነው መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አውጆ ዜጎችን ለመታደግ ወደ እርምጃው ለመግባት በዝግጅት ላይ ያለው።» ያሉት አቶ ከበደ አክለውም በአማራ ክልል አሁን ጎልቶ የሚስተዋለው የሰላም እጦት ወደ ሌላ አካባቢዎች እንዳይዛመትና ችግሩ እንዳይሰፋም መንግሥታቸው ዝግጅት ማድረጉን አመልክተዋል።


Leave a Reply