” ሰው በጠፋ ጊዜ ሰው ሆነው የተገኙ” በሚል የሚጠሩት አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአማራ ክልልን በመሩበት አጭር ጊዜ እውቅና አገኝተዋል። የትንሳኤ በዓለን አንተርሰው “ትንሣኤዋን እውነተኛ ልጆቿ እንጂ ጠላቶቿ ወዲያው አያዩትም ” ሲሉ ኢትዮጵያ ከተጋረጠባት አደጋ በአሸናፊነት እንደምትወጣ አመላክተዋል።

የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ተመስገን “ክርስቶስ የሞትን ጽዋ ቀምሶ ወደ መቃብር በወረደ ጊዜ፣ የትንሣኤ ተስፋ ያሠጋቸው አካላት፣ መቃብሩን በከባድ ኃይል ሲጠብቁ ነበር” በማለት የበዓሉን ቁልፍ ምክንያት አውስተዋል።፣

” መቃብር ጠባቂዎቹ” ያሉት ተመስገን ” ከመጠበቃቸው ብዛት ነገሩ ያለቀ መስሏቸው ተኝተው ነበር። ነገርግን የጥበቃው ብዛት ትንሣኤውን አላስቀረውም” ሲሉ ኢትዮጵያን በማንሳት መልዕክታቸውን ከወቅቱ ጉዳይና ከበባ ጋር አሳስመውታል።

“ኢትዮጵያ ትነሣለች ብለው የፈሩ ብዙዎች ያለ የሌለ ኃይላቸውን አሠማርተዋል። እንዳትነሣም ለመከላከል ሲሉ ሠራዊታቸውን አቁመዋል። ለጊዜው የተሳካላቸው መስሏቸዋል። የኢትዮጵያ ትንሣኤ ግን አይቀሬ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያን መነሳትና ማሸነፍ ሲያውጁ ” ያውም ሳያዩና ሳይሰሙ፤ በተኙበት ነው የምትነሣው” ብለዋል። የኢትዮጵያን ትንሳኤ ረቂቅነት ሲያስረዱም ” ትንሣኤዋን እውነተኛ ልጆቿ እንጂ ጠላቶቿ ወዲያው አያዩትም” ነው ያሉት።

“ዘግይተው ግን ይረዱታል። ያን ጊዜ እንደ መቃብር ጠባቂዎቹ የሐሰት ወሬ መፈብረካቸው አይቀርም” ሲሉ ዛሬ ላይ ወሬ ገበያ የሆነበትን አግባብ አስታውቀዋል። ሲያጠቃልሉም ” በኢትዮጵያ ትንሣኤ ለመኩራት፣ በጠባቂዎቹ የውሸት ወሬ ለመዝናናት እየጠበቅን ነው። እናምናለንና” በማለት መልካም የትንሳኤ በዓል ተመኝተዋል።፡

    Leave a Reply