ከነገ ጀምሮ 450 በርሜል ነዳጅ የሙከራ ምርት ማምረት እንደሚጀመር አብይ አህመድ ይፋ አደረጉ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ የቻይናው ፖሊ ሲ ጂ ኤል ኩባንያ በምስራቅ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ሲያደርግ የቆየው የድፍድፍ ነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋ ውጤት ማስገኘቱን ተናግረዋል።ከነገ ሰኔ 21 ቀን ጀምሮም በሙከራ ደረጃ በቀን 450 በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ የማውጣቱ ስራ ይጀመራል ብለዋል።አሁን የማውጣቱ ስራ ሃገሪቱ ያላትን አቅም ማወቅን ታሳቢ ያደረገ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፥ አጠቃላይ አቅም ታውቆ በቀጣይ በሙሉ አቅም ድፍድፍ ነዳጁን የማውጣት ስራ እንደሚሰራም አስታውቀዋል።

ይህ መሆኑም ስራ አጥነትንና የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ለመቅረፍና ዘላቂ እድገትን ለማምጣት ይረዳልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ባለፈው በኢትዮጵያ ሶማሌ ባደረጉት ጉብኝት የተፈጥሮ ሃብትን በሰላማዊ መንገድ መጠቀም እንዲቻል መግባባት ላይ መደረሱን አስታውሰዋል።የተፈጥሮ ጋዝን በተመለከተም በሚቀጥለው መስከረም ወር ወደ ጅቡቲ መላክ የሚያስችል የጋዝ ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ይጀመራል ብለዋል።

የማስተላለፊያ መስመሩ ዝርጋታ በሁለት አመት ውስጥ የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ በሙከራ ደረጃ ጋዝ ማስተላለፍ ሲጀምር በአመት 1 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስገኝ ጠቅሰዋል።በቀጣይ በሙሉ አቅም ጋዝ ማስተላለፍ ሲጀምርም በአመት 8 ቢሊየን ዶላር እንደሚያስገኝ ነው የተናገሩት።ኢትዮጵያ በርካታ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ሃብት አላት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ የነበረው ልዩነት ይህን ሃብት በአግባቡ እንዳንጠቀም አድርጎን መቆየቱን አውስተዋል።

ከዚህ አንጻርም የተገኘውን የተፈጥሮ ሃብት በእኩልነትና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ በጋራ መጠቀም እንደሚገባም አሳስበዋል።የተፈጥሮ ሃብትን መቀራመት ትልቁ የአፍሪካውያን ችግር መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ አሁን የተገኘውን ሃብት በሰላማዊ መንገድ በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።አሁን የተገኘው ድፍድፍ ነዳጅም አዳዲስ ሃብቶችን ለማምጣት እንደሚያግዝ ጠቅሰው፥ በቀጣይም የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ሃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሚገኙ እምነቴ ነው ብለዋል።

ኩባንያው ለሰራው ስራ ምስጋናቸውን አቅርበው በቀጣይም በማውጣት ሂደቱ ውስጥ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።ህብረተሰቡም ከሃብቱ ተጠቃሚ ይሆን ዘንድ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።ለመላው ኢትዮጵያውያም የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው፥ የተገኘው ሃብት ለብጥብጥ ሳይሆን ለጋራ ተጠቃሚነት እንዲውልም ጥሪ እንዳቀረቡ የዘገበው ፋና ነው


DONATE US – ቢረዱን አስፍተን ለመስራት አቅም ይፈጥሩልናል

About topzena1 2661 Articles
A journalist

Be the first to comment

Leave a Reply