“አስገድዶ ደፍሮኛል” ስትል በሐሰት የወነጀለችው ተከሳሽ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣች

ተከሳሽ ዘማ ደባሽ የተባለችው በ1996 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. የወንጀል ህግ አንቀጽ 447/ለ/ ላይ የተደነገገውን ድንጋጌ በመተላለፍ በፈፀመችው በሐሰት መወንጀል ዐቃቤ ህግ ክስ መስርቶባታል፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ተከሳሿ የሌላውን ሰው ንጽህና እያወቀች ጥቅምት 22 ቀን 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 4፡00 ሰዓት አካባቢ በአራዳ ክፍለ ከተማ ጋንዲ ሆስፒታል ምርመራ ክፍል በመስከረም ወር 2014 ዓ.ም ከጠዋቱ 2፡00 አካባቢ ቴዎድሮስ አበበ የተባለ ግለሰብ ቤት ውስጥ በሰራተኝነት ተቀጥራ ስትኖር “አልጋ አንጥፊ ብሎ ጠርቶኝ አስገድዶ ደፍሮኛል” በማለት ቃል ሰጥታ ተጠርጣሪው ተይዞ ጊዜ ቀጠሮ ከተጠየቀበት በኋላ ታህሳስ 7 ቀን 2014 ዓ.ም ለኮልፌ ቀራኒዮ ፖሊስ መምሪያ ሴቶችና ህፃናት ምርመራ ክፍል ከቤቱ መውጣት ፈልጌ እንጂ አልደፈረኝም በማለት በድጋሜ ቃል የሰጠች በመሆኑ በፈፀመችው በሐሰት መወንጀል ወይም መክሰስ ወንጀል ተከሳለች፡፡

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሿ የተከሰሰችበትን የወንጀል ድርጊት እንደ ክሱ ሙሉ በሙሉ ያመነች በመሆኑ ባመነችው መሰረት በተከሳሿ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ይሰጥልኝ ሲል አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም ተከሳሿ በተከሰሰችበት ድንጋጌ ስር በዝርዝር ያመነች በመሆኑ ባመነችው መሰረት ጥፋተኛ ነሽ ብሏታል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተው የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ኮልፌ ቀራኒዮ ምድብ ፈጣን የወንጀል ችሎትም ታህሳስ 13 ቀን 2014 ዓ.ም በዋለው ችሎት ተከሳሽ በ1 ዓመት ከ6 ወር ፅኑ እስራት እና አምስት መቶ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ሲል ወስኖባታል፡፡

Leave a Reply