“ለተስፋፊው አማራ” ጻድቃን ክፍት የአጋርነት የስራ ማስታወቂያ ይፋ አደረጉ

አማራና አፋርን ወሮ የሰነበተውን የትህነግ ጦር በአዛዥነት የመሩትና የወረራውን ዕቅድ በማዘጋጀት በተለይ በእንግሊዝ ሚዲያዎች “ምጡቅ” ተብለው የተወደሱት ጻድቃን ገብረትንሳይ የግል አመለካከታቸው እንደሆነ ጠቅሰው ጽሁፍ አሰራጭተዋል። በዚሁ በወዳጆቻቸው ሚዲያዎች ባሰራጩት ጽሁፍ ” ተስፋፊ” እያሉ ለሚጠሩት አማራ አዲስ ጥሪ አቅርበዋል። ጥሪውም የክልሉን መንግስት ለመደምሰስና ከስልጣን ለማንሳት እንዲቻል ነው። ዳግም ጥቃት ከተሰነዘረ ” ብቻችንን አይደለንም” ሲሉ ጠቅሰዋል።

” ሂሳብ ይወራረድብሃል” የተባልኩ አማራ ነኝ። እንደተባለውም ያሻቸውን አድርገዋል። ወደፊትም እንደማያርፉ እያስታወቁ ነው። የቀረባቸውን ባዶ የበላይነት መንፈስ ካላስመለሱ አይተኙም። በልካቸው፣ በቁመናቸውና በወርዳቸው የሚሰላ የፖለቲካ ጨዋታና ተሳትፎ ሊዋጥላቸው ባለመቻሉ የገቡበት ቀውስ አገርን ለመከራ፣ እንወክለዋለን የሚሉትን ህዝብ ለጣር፣ አርፎ በየሰፈሩ የተቀመጠውን ነዋሪ ጓሮው ድርስ በመሄድ ለበቀል ዳርገዋል። ይህ ሁሉ አልበቃ ብሏቸው ለአማራ ” ኑ” የሚል የትግል ህብረት ጥሪ አቅርበዋል።

ትህነግ ያበሰበሳቸውና በዛው ብስባሽ ላይ የቆሙ ከሃጂዎች ሙሉ በሙሉ ባይጠፉም የማድረግ አቅም የሌላቸው ትንኞች ሆነዋል። ትሀንግ የሚባለው የባንዳዎች ጥርቅም አበስብሶ ያኖራቸው ገረዶች ዛሬ እንኳን ትህነግን ሊያግዙ ከህዝብ ዕይታ እንዴት እንደሚሰወሩ እያሰሉ ነው። ለቀጣሪዎች የሚያፈነድደው ትህነግ፣ ልክ እሱ እንደሚየደርገው፣ ከዛም አልፈው በክህደት ” ስሪያ” የዘሞታቸው ጭራቸውን ቢቆሉለትም ያሰበው አልሆነም። ትህነግ በቀጣሪዎች ዕለት ዕለት የሚሰረር ፖለቲካ ውጤት በመሆኑ የሞራል ልዕናው ሸቷል። ወይም ውርዴ ይዞታል። በውርዴነቱ ሳቢያ አስተሳሰቡ ስለነተበ ” አማራን በዚህ ደረጃ፣ ሂሳብ እናወራርዳለን በሚል የእሪያ መንፈስ መፈክር ተነስቶ ያደረገውን አድርጎ ሲያበቃ፤ ኑ መንግስት እንጣል” ማለቱ ሙሉ የሰው ስብዕና የሌለው የውርዴ ውጤት እንደሆነ የሚያመላክት ነው።

ከተማ እምሽክ አድርጎ እንዲበላ፤ ሳይመርጥ እንዲደፍር፣ ዘርፎ እንዲያከማች፣ በተደራጀ አኳሗን ንብረት እንዲያግዝ፣ እንሣስትን እንዲፈጅና በጅምላ እንዲጨፈጭፍ እቅድ አውጥተው ጭፍራ ያዘመቱ መሪ ዛሬ ለአማራ ጥሪ ሲያቀርቡ ከውርዴም በታች መሆኑን ከማረጋገጥ ያለፈ ምንም ሊባል አይችልም።

የጦርነቱን ጅማሮ አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ በቆሙለት አለማ ለክተው፣ ደርዘውና የግለቱ ምንጭ በሆነው በምስራቅ አፍሪቃን ፖለቲካ አስደግፈው ባሰራጩት ጽሁፍ የቀድሞው ሌተናል ጄነራል ጻድቃን ” ትግራይ ሰላም ካልሆነች ምስራቅ አፍሪካ ሰላም ሊሆን አይችልም” በሚል የጋላቢዎቻቸውን ቃል ደግመዋል። በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመራው መንግስት ሰላም ማስፈን የማይችል በመሆኑ ” እኛ ነግሰን ሰላም እናስከብራን” ሲሉ ለመላላክ የተመቹ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ለዚህም ተግባራዊነት መንግስትን ለማስወገድ ከኦሮሞ፣ ከቤኒሻንጉል፣ ከአፋር … ሃይሎች ጋር ጥምረት መፍጠራቸውን አስታውሰው በአማራ ክልልም በተመሳሳይ ይህንን ጥምረት ለመቀላቀል ፍላጎት ላላቸው “ኑ” ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ቀደም ሲል ድርጅታቸው ለይቶ ” ነፍጠኛና ትምክህተኛ” ሲለው የነበረውን የህብረተሰብ ክፍል በጽሁፋቸው ደጋግመው “የአማራ ተስፋፊ ሃይል” በሚል እየጠቀሱ መልሰው ” ኑ መንግስትን እንጣል” የሚል ጥሪ ማቅርባቸው ከላይ እንዳልኩት ባተቃላይ የአመልካካት ቀውሳቸው መገለጫ እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። ከአማራ ክልል ጉዳት ደርሶበት በሃይል እንዲወጣ የተደረገውን ወራሪ ሃይል የመሩትና ዕቅድ ያወጡለት ጻድቃን፤ በአማራ ክልል ይህ ሁሉ በደል፣ ግፍ፣ የጅምላ ጭፍጨፋ፣ አስገድዶ መድፈር፣ዝርፊያና ውድመት በወጉ ተነገሮና መረጃው ተሰብስቦ ሳያልቅ ነው ” ኑ” ሲሉ ለአማራ የፖለቲካ ድርጅቶች ጥሪ ማቅረባቸውን “ውርዴ” እንድል ያስገድደኝ።

እዚህ ላይ በፈለጉት ደረጃ፣ ያዋታናል ያሉትን ዓላማና ፕሮግራም ማራመዳቸውን እንደማልነቅፍ ማስታወቅ እወዳለሁ። እንደ አንድ አማራ ግን አንድ የትግራይ ሰው አሁን ባለነበት ደረጃ ስምችንን አንስቶ ምንም የማለት “ሞራል” አይኖራቸውም። አማራ ከሚመስሉት ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር አሁን መልሶ ማቋቋምን እንጂ ሌላ ነገር ሊያስብ አይችልምና እንዲህ ያለውን የጦርነት ጥሪ እንደ እናንተው የእሪያ ፖለቲካ ከሚያራምዱ ጋር አድርጉት። ተውን። ልቀቁን። እኔ 39 ዓመቴ ነው። ምንም አልደረግናችሁም። እባካችሁን ራሳችሁን ቻሉ።

ሌላው የገርመኝ በጽሁፋቸው ኦነግ ሸኔ ሰፊ ሃይል እንዳለው ጻድቃን ግልጸዋል። በአማራ ክልልም ልክ ሸኔ እያደረገ እንዳለው የራሱን ሕዝብና መሪዎች፣ እንዲሁም ንጹሃንን እያደፈጠ የሚያጠቃ ሃይል ለመትከል መመኘታቸውን አስታከው ገልጸዋል። ይህ ማለት የአማራ ክልል መሪዎችን፣ አሁን ደግሞ በህልውናው ጦርነት ህዝባቸውን ማዕከል አድረገው የተነሱትን የአብን አመራሮችና ቤተሰቦች እያደባ የሚገልና ጌታቸው እዳን አማራ ላይ አንግሶ ከበሮ የሜደልቅ አማራ አስመኝቷቸዋል። እስከማውቀው ይህ አማራ ምድር አይሆንም። አምራ አማራን ጨርሶ በትግሬ ወራሪ እንዲተዳደር ጥሪ የቀረበው ለማን እንደሆነ አለማወቅ በራሱ ከአፈጠጠር ጀምሮ የሚከሰት የአንጎል ውቅር ችግር ነውና ጥናት ቢደረግበት እላለሁ።

የትግራይ ወራሪ ሃይል ወደ ትግራይ ወዶና ፈቅዶ መመለሱን ጻድቃን ደጋገመው ገልጸዋል። ጭራቸውን ወደ አፍሪካ ለመቁላት ትግራይን “የፓን አፍሪካ አሳብ አቀንቃኝ ናት”ሲሉ ከኢትዮጵያ ላይ ተንጠራርተዋል። በዚህ በገሸበ አስተሳሰብ ልኬት ለፓን አፍሪካ አሳብ አራማጆች ስለ ፓን አፍሪቃ ሊሰብኳቸው ሞክረዋል። ይህ መንጠራራት ዓላማው ከዕሪያ ወደ ትንኝ ፖለቲካ የተደረገ ሽግሽግ እንጂ ሌላ ምንም ሊባል አይችልም። “ደሃ ግን ልዩ ማንነት ያለው” ሲሉ ዛሬም ባደረ የቅዠትና የስካር ስሜት ውስጥ ሆነው የትግራይን ህዝብ ልክ እንደ አቶ መለስ አሞካሽተዋል። መለስ ብለውም የመወረር ስጋት እንዳለባቸው አመልክተዋል። ይህ ሁሉ መሳከር ዓላማው ግልጽ ቢሆንም እንደፍጥርጥራቸው ራሳቸው ይወጡት ከማለት የዘለለ የምለው የለም።

“ለዳግም ጂኖሳይድ ሙከራ ከተደረገ ብቻችንን አይደለንም” ሲሉ በገሃድም ተናግረዋል። የግል እምነታቸው እንደሆነ ገልጸው ባሰራጩት ጽሁፍ “ብቻችንን አይደለንም” ሲሉ በግል የተዋዋሉት ጉዳይ ይኑር በድርጅት ደረጃ ማብራሪያ አልሰጡንም። ይሁን እንጂ አማራውን ለማስቦካት ወይም መንግስትን ለማሳራድ አስበው እንደሆነ ግልጽ ነው። ይህም የሆነው ” እርቅ እንቀመጥና ወደ አንበሳ ባንክ ቢሮዬ ልመለስ” የሚል ማመልከቻ እንጂ ሌላ አይደለም።

ይህማ ባይሆን “ብቻችንን አይደለንም” ሲሉ እነማን አብረዋቸው ጦርነት እንደሚገጥሙላቸው ዝርዝር መረጃ ባቀረቡ ነበር። በቅጽበት ከድፍረት ማስፈራሪያቸው ወርደው ቻይናና ሩሲያ በጸጥታው ምክር ቤት ውስጥ ይህ ነው የተባለ ውሳኔ እንዳይወሰን እንቅፋት መሆናቸውን ኮንነዋል።

ዶ/ር ደብረጽዮን ቀደም ሲል ያለ ማንዴታቸው ጻፉት በተባለው ደብዳቤ ” ትግራይ ሰፊ ሰራዊት አላት ህዝቡ ተከቦ ሲራብ ዝም ብሎ አያይም” ማለታቸውና ጻድቃን ” ብቻችንን አይደለንም” ሲሉ በይፋ ድጋፍ ሊደረግላቸው የተመቻቸ ነገር ስለመኖሩ መናገራቸው በሳምት ውስጥ የታየ የሃሳብ መለያየት ሆኗል። ዳሩ ግን ለአማራ ፣ ለአፋርና ለፌደራሉ መንግስት ታላቅ ማስጠንቀቂያ መሆኑ አይካድም።

ትህነግ ለሰላም እድል ለመስጠት ሲወስን ደርሶበት ከነበረበት ቦታ ወደ አዲስ አበባ ቢያቀና ሰባ ከመቶ ሊሳካ እንደማይችል ገምግሞ ማፈግፈጉ ሲገለጽ ቆይቷል። ጻድቃን እንዳሉት ማፈግፈጉ በራሱ ከባድ ኦፕሬሽን እንደነበረ አመልክተው ሃሳቡን ደግመውታል። ” መውጣት እንደ መግባት አይቀልም” በሚል ዘመቻውን የመሩት የጥመ ሃይሎች በትህነግ ሃይል ላይ በሰማይ ፤አይ ጥቃት እየታገዙ ሰፊ የሚባል ሰብአዊ ቀውስ ማድረሳቸውን ትህነግ ባያምንም መረጃዎች ያሳብቃሉ። እኔ እራሴ ምስክር ነኝ። ሁሉም በፊልም ተሰንዶ ይፋ ይሆናል። ጊዜው ሲደረስ!!

ጻድቃን ቀደም ሲል ገና ለውጡ ሲያፍገመግም መከላከያ፣ ፖሊስና ደህንነቱን ትህነግ እንዲቆታጠረው ( ባለበት እንዲቀጥል ሆኖ) ለውጥ እንዲካሄድ ሃሳብ ማቅረባቸውን አልዘነጋም። የጸጥታና የድህነነት ሃይሉ በትግራይ ሰዎች እጅ እንዲቀጥል በሚጠይቀው ረጅም የለውጥ አፈጻጸም መፍትሄ ሲያቀርቡ በተመሳሳይ አቋሙ የግላቸው መሆኑንን አመልክተው እንደነበር ዛሬ ድጋሚ በርቶልኛል።

ልዩነቱ በአሁኑ ጽሁፋቸው ሰላምን የሚማለዱ ቢሆንም አልፎ አልፎ ” ከበባውን ሰባብረን፣ ድምስሠን” እያሉ የሃይል አማራጭን የመጠቀም አቅም እንዳላቸው ለማመላከት መሞከራቸው ነው። “አልተሸነፍንም” ቢሉም ለቢቢሲ አፍሪካ በድሮን መደብደባቸው ሃይላቸውን በሎጅስቲክና በሰው ሃይል ማገዝ እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው በመግለጽ የመንግስት ሃይሎች በሰው አቅርቦት ላይ የተሳካ ጥቃት ማካሄዳቸውን በተደጋጋሚ ሲልገልጹ ለነበረው ምስክር መሆናቸውን ሳላመሰግን አላለፍም።

“ጦርነቱ አብቅቷል። ድርድር የለም። ከማን ጋር ነው የምንደራደረው?” ሲሉ የነበሩት ጻድቃን “ገፍተን የሄድነው መንግስት አስገድዶ ለድርድር ለማስቀመጥ፣ ወይም ለመጣል ነበር” ብለዋል። መንግስት የቀረበለትን ስምንት ቅድመ ሁኔታዎች አልቀበልም ማለቱን አንስተው የወቀሱት ጻድቃን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚፈለገው መተን ጫና አለመደረጉን ወርፈዋል። የነበረውን ጥረትም ቻይናና ሩሲያን ጠቅሰው እንዳበላሹት አመልክተዋል። በዚህም ” ትህነግ ከፍጥረቱ ጀምሮ የውጭ ሃይሎች ጥገኛና አምላኪ ነው” የሚለውን ትንታኔ ደግሜ እንዳስበው አድርጎኛል።

በጽሁፋቸው በአማራና አፋር ክልል እሳቸው ዕቅድ ነድፈው ያሰማሯቸው ወራሪዎች ስላደረሱት በደል ያሉት ነገር የለም። እሳቸው በክፍት የስራና የትብብር ጥያቄ መሰረት በውጭ አገር ሆነው ከሚርመጠመጡ የቀድሞ የኢህዴን ሰዎችና በሁለት ቢላዋ ከሚጫወቱ የምላስ ፖለቲከኞች በስተቀር መሬት ላይ አቅም ያላቸው የአማራ ድርጅቶች እስካሁን ምላሽ እንዳልሰጡ አረጋግጠዋል።

“ራሱን የአማራ ነጻ አውጪ” ብሎ የሰየመውና ከዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የቀጥታ የስራ ማስኬጃ የተበጀተለት ድርጅት ቀድሞ ማንነቱ ስለታወቀ ከወዲሁ ተቀላቅሎ በምስኪኑ የአማራ ህዝብ ላይ እንዲቆምር ምክር ልለግሰው እወዳለሁ። ሌላው የአማራ “ሸኔ” እንዲሆን እግረመንገዴን ምኞቴን አድርሱልኝ።ድርጅቱ ባሰራጨው የመረሃ ግብሩ ጽሁፍ ላይ ” አማራ ባለበት ሁሉ እየተወረወረ ጥቃት የሚፈጽም ልዩ ሃይል በማደረጃት የአማራን ህዝብ በሚኖርበት ሁሉ የሚታደግ ልዩ ሃይል ይኖረዋል” ብሏል። እንደ ድርጅቱ አባባል ጀግጅጋ አንድ አማራ ከሞተ ልዩ ሃይሉ ሄዶ ይበቀላል። አንድ አማራ ባሌ ጎባ ጥቃት ከደረሰበት ባሌ ጎባ ድረስ የሚወረወረው ሃይል የበቀል ጥቃቱን ሰንዝሮ ይመለሳል… ስለ ድርጅቱ የቅዠት አስተሳሰብና ተልዕኮ በቀጣይ ሰፋ ያለ ዘገባ አቀርባለሁ።

ሰለም ለኢትዮጵያ ትግራይን ጨምሮ!!

ቾምቤ ቀለመወርቅ ( ዝግጅት ክፍሉ ጽሁፉ የጸሃፊው ሙሉ እምነትና አቋም እንጂ የዝግጅቱን አቋም አያንጸባርቅም። ማልሽ ወይም በድጋፍ ለመጻፍ ለምትወዱ መድረኩ ክፍት ነው )


Leave a Reply