ሰኔ 22 ቀን 2014 ዓ.ም

አሸባሪው የህወሃት ቡድን የመዋጋት አቅምም ሞራልም የሌላቸውን በማስገደድ ወደ ውጊያ እንደሚያስገባ እጃቸውን ለምዕራብ ዕዝ የሰጡ ወዶ ገቦች ተናገሩ።

ወዶ ገቦቹ እንደሚሉት የሽብር ቡድኑ ከ13 ዓመት ጀምሮ ያሉ ህፃናቶችን እና አዛውንቶችን ጭምር በማስገደድ አጭር ስልጠና ሠጥቶ ወደ ጦርነት እንደሚማግድና ወደ ኋላ የሚመለስ ከጀርባው እንደሚመታ ገልፀዋል።

ማዕሾ ገ/ሄር የሰባት ልጆች አባትና የ60 ዓመት ሽማግሌ ሲሆኑ በማላውቀውና በደካማ ጉልበቴ ትግራይን ነፃ አውጣ ተብዬ በግዴታ ወደ ጦርነት አስገብተውኝ የእርጅና ዘመኔን ፀጋነት ቀምተው መከራ አድርሰውብኛል ይላሉ።

ልጆቼ የት እንዳሉና እንዴት እንደሚኖሩ አላውቅም የሚሉት የ60 ዓመቱ አዛውንት ትግራይ ከተቀሩት ኢትዮጵያዊያን ጋር ለምን ጦርነት ውስጥ ትገባለች ተስማምተን ለምን አንኖርም የሚል ሃሳብ የሚያቀርቡ አባላት በርካታ መከራዎችን ይቀበላሉ ብለዋል።

ህወሃቶች አስገድደው ወደ ጦርነት የሚያስገቡትን ሠው በፈጠራ እና በሀሰት ፕሮፖጋንዳ እንደ ህዝብ ሊያጠፉን የሚያስቡ ሃይሎችን ነው የምንዋጋው ይላሉ ያሉት አዛውንቱ እኛ የተለየን ጀግኖች ነን እያሉም በመስበክ ወጣቱን በጦርነት አስጨርሰውታል ብለዋል።

ኢትዮጵያን አፍርሰን ታላቋን ትግራይን እንፈጥራለን የሚሉን የህወሃት መሪዎች በጦርነቱ የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመደበቅ አዲስ አበባ ሳንገባ የተመለስነው የውጭ መንግስት ተመለሱ ብሎን ነው በማለት ህዝቡን ለሌላ እልቂት ይቀሰቅሡታል ብለዋል።

የህወሃት መሪዎች እጃችሁን ለመከላከያ ከሰጣችሁ ቆራርጠው ነው የሚገድሏችሁ። እጃችሁን ከምትሰጡ እራሳችሁን ብታጠፉ ነው የሚሻላችሁ ይሉናል። እኛ ግን እጃችንን ለመከላከያ ስንሰጥ አሸባሪው ቡድን እንዳለው ሳይሆን ደስ በሚልና በተለየ እንክብካቤ ተቀብሎናል ብለዋል።

ታገል አልማው
ፎቶግራፍ ሽመልስ እሸቱ via ENDF

Leave a Reply