በመንፈቁ ከሁለት ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃት ተሰንዝሯል

በኢትዮጵያ ላይ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከ2 ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች መቃጣታቸውን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡ ኤጀንሲው የዘንድሮው የሳይበር ጥቃት ቁጥር ባሳለፍነው አመት በሙሉ ከተደረገው ጥቃት የሚስተካከል መሆኑንም ገልጿል፡፡ ጥቃቶቹን ማምከን ባይቻል ኖሮ ምናልባት አሁን የምናያት ዓይነት አገር ላትኖረን ትችል ነበር ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ሹመቴ ግዛው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለፁት፤ በኢትዮጵያ ላይ በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ የሳይበር ጥቃቶች ሙከራዎች ተካሂደዋል፡፡

የተቃጣው የሳይበር ጥቃት ቁጥር ከዚህ ቀደም ከነበረው አንፃር ቁጥሩ ማሻቀቡን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የዘንድሮው የሳይበር ጥቃት ቁጥር ባሳለፍነው አመት በሙሉ ከተደረገው ጥቃት እኩል መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ባሳለፍነው አመት ከሁለት ሺህ ስምንት መቶ በላይ አደገኛ የሳይበር ጥቃቶች ተሰንዝረው ሙሉ በሙሉ ማምከን መቻሉን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህ አመት በስድስት ወራት ውስጥ ብቻ ከዚህ ቁጥር ያላነሰ ተሰንዝሮ ማምከን መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ንግግር፤ ቴክኖሎጂው ባደገ ቁጥር የሳይበር ጥቃት ለማድረግ አላማቸውን አድርገው የሚንቀሳቀሱ የዘርፉ ወንጀለኞች ተበራክተዋል፡፡

በአገር ላይ ከፍተኛ ወንጀል ሊፈጽሙ የሚፈልጉ አካላት በአካል ወደ አገር መግባት ስለማይችሉ የሳይበር ጥቃት ከፍተኛ መሣሪያቸው መሆኑን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የሚሞክሯቸውን ጥቃቶች ማምከን ባይቻል ኖሮ ምናልባት አሁን የምናያት ዓይነት አገር ላትኖረን ትችል ነበር ሲሉም የጥቃቶቹን አሳሳቢነት ጠቁመዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ በንግግራቸው በየቀኑ እየጨመረ በሚገኘው ቴክኖሎጂ ምክንያት በአገርም ላይ ሆነ በተለያዩ ተቋማት ላይ የሳይበር ጥቃት እንዳይደርስ ኤጀንሲው የተለያዩ የአሠራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የኢትዮጵያን ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ ቀን ከሌት ሠራዊት ሆኖ አገሩን በመጠበቅ ላይ እንደሚገኝ መጠቆማቸውን የዘገበው ኦቢ ኤን ነው።

Leave a Reply