ሙርሌዎች የሚያደርሱትን ጥቃት ከምንጩ ለማስቆም ከደቡብ ሱዳን ጋር መግባባት ተደረሰ

(ኢ ፕ ድ)
የሙርሌ ጎሳ አባላት የሚፈጽሙትን ጥቃትን ከምንጩ ለማስቆም ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር መግባባት ላይ እንደተደረሰ የጋምቤላ ክልል አስታውቀ።

ባለፉት ሶስት ወራት የሙርሌ ጎሳ አባላት ወደ ጋምቤላ ክልል ሰርገው በመግባት በፈጸሙት ጥቃት ሰባት ህፃናት የታገቱ ሲሆን፤ 13 ሰዎች ተገድለዋል።

የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኦጌቱ አዲንግ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ የሙርሌ ጎሳ አባላት በየዓመቱ በጋ ወራት ወደ ጋምቤላ ክልል ሰርገው በመግባት በሠላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ይፈጽማሉ። ይህን ጥቃት ከምንጩ ለማስቀረት የፌዴራል መንግሥቱ ከደቡብ ሱዳን ጋር ባደረገው ውይይት ችግሩን ለመፍታት መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል።

የሙርሌ ጎሳ አባላት እንደ ባህል ወደሌላ አካባቢ ሄዶ የመዝረፍና ጥቃት የማድረስ ልምድ አላቸው። ጥቃቱን ማስቆም የሚቻለው ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው ከመግባታቸው በፊት ከመነሻቸው ከደቡብ ሱዳን ነው። ለዚህም የሚረዳ ውይይት ከደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጋር ተደርጓል፤ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅም መግባባት ላይ ተደርሷል ብለዋል። 

በኢትዮጵያ በኩል የሕዝብ ተወካዮች አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝና የጋምቤላ ክልሎች መስተዳድሮችና ሌሎች ኃላፊዎችም በውይይቱ መሳተፋቸውን ተናግረዋል። 

ውይይቱም የሙርሌ ጎሳ አባላት በጋምቤላ ክልል ሰርገው እየገቡ የሚፈጽሙትን ጥቃት ለማስቆም የደቡብ ሱዳን መንግሥት ጠንካራ ሥራ ማከናወን እንዳለበት መግባባት ላይ የተደረሰበት ነው። የደቡብ ሱዳን መንግሥትም ለዚህ ጥቃት መቆም እንደሚሰራ ማስታወቁን ገልጸዋል። 

የሙርሌ ጎሳዎች ሰባትና ስምንት ሰው በመሆን በጫካ እየተደበቁ ወደ ክልሉ በመግባት ጥቃት እየፈሙ ይገኛል ያሉት አቶ ኦጌቱ፤ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለው ድንበር ሰፊ በመሆኑ ሰርገው በተለያየ አቅጣጫ የሚገቡበት ዕድል እንዳለ ተናግረዋል።

አሁንም ከ300 በላይ የሙርሌ ጎሳ አባላት ከአካባቢያቸው ተነስተው በአዋሳኝ ድንበሮች በሚገኙ ጫካዎች መግባታቸውን ጠቁመው፤ የጋምባሌ ክልል ጸጥታ ኃይልም ይህን በተበታተነ መልኩ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል። 

ከዚህ ጥረት ባለፈ የጋምቤላ ነዋሪዎች በበጋ ወራቶች ሊፈጸም ከሚችል የሙርሌ ጎሳ አባላት ጥቃት እራሳቸውን እንዲከላከሉ ጥሪ መተላለፉን አስታውቀዋል። 

ከትናንትና በስቲያም ሰርገው የገቡ የሙርሌ ጎሳ አባላት ሶስት ህጻናትን አግተው መውሰዳቸውንና ሶስት ሰዎችን መግደላቸውን አስታውቀዋል። 

በዲማ ኦኩጎ የስደተኞች ካምፕ ዘልቀው በመግባት ሁለት ሰዎች ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

ባለፉት ሶስት ወራት የሙርሌ ጎሳ አባላት በተፈጸሙት ጥቃት ከጋምቤላ ክልል ሰባት ህፃናትን አግተው ከመውሰዳቸው በተጨማሪ 13 ሠላማዊ ሰዎችን ገድለዋል ሲሉ ተናግረዋል። 

ከዚህ ባለፈ በዘንድሮ ዓመት ብቻ 101 የቁም እንስሳትን ዘርፈው መውሰዳቸውን ጠቁመው፤ የሙርሌ ጎሳ አባላት በባህላቸው ወደሌላ አካባቢ በመሄድ ንብረት መዝረፍና ጥቃት ማድረስን የጀግንነት ምልክት አድርገው መቁጠራቸው ችግሩን እያባባሰው መሆኑን አስረድተዋል።

እንደ አቶ ኦጌቱ ገለጻ፤ ጥቃቱን ለማስቀረትና ሙርሌዎችን ከመነሻቸው ደቡብ ሱዳን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት የደቡብ ሱዳንን መንግሥት ትብብር ይጠይቃል። አሁን በተደረሰው መግባባት መሰረት ከሶስት ወራት በኋላ ዘላቂ መፍትሄ ይመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

 ጌትነት ተስፋማርያም 

አዲስ ዘመን የካቲት 4/2022

Leave a Reply