በረከት ገበሬዋ የመደመር ትውልድ መጽሀፍን በ50 ሺህ ዩሮ ገዝታለች

በረከት ገበሬዋ በሚል ስም የምትታወቀው ባለሀብት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “የመደመር ትውልድ”መጽሀፍን በ50 ሺህ ዩሮ ገዝታለች

በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተጻፈውን “የመደመር ትውልድ” መጽሀፍ በኦሮሚያ ክልል ደረጃ የማስተዋወቂያ መርሀ ግብር ማምሻውን በአዲስ አበባ እየተከናወነ ነው።

ማምሻውን እየተካሄደ ባለው በዚሁ መርሀ ግብር የተለያዩ ባለሀብቶች መፅሃፉን በመግዛት ላይ ናቸው።

በመርሀግብሩ ላይ የተገኘችው በረከት ገበሬዋ በሚል ስም የምትታወቀውና በግብርና ላይ የተሰማራችው ባለሀብት በረከት ወርቁ መጽሀፉን በ50 ሺህ ዩሮ በመግዛት ዓላማውን ደግፋለች።

በረከት ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጠችው አስተያየት፤ እንደተናገረችው፤ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ አማካኝነት የተፃፈው የመደመር ትውልድ መፅሐፍ ሽያጭ የሚውልበትን አላማ መደገፍ ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው ብላለች።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በሚችለው መጠን ለመፅሀፉ አስተዋጽኦ ማበርከት ይገባዋል ያለችው በረከት ትውልድን የሚያቀራርብ ፍቅርን የሚያጎለብት ነውና ይህን መርዳት ምርጫ ሳይሆን ግዴታ ነው ብላለች።

ጠቅላይ ሚንስትሩ በዚህ ከባድ ጊዜ ይህን መጽሀፍ እያሳተሙ ለበጎ ተግባር ስለሚያውሉ ረጅም እድሜ ከጤና ጋር እመኝላቸዋለሁ ያለችው በረከት፤ በየክልሉ ያሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ስፍራዎች ስለሚውል መጽሀፉን መግዛት አማራጭ የሌለው መልካም ስራ መሆኑንም አክላለች።

በመጽሀፉ ማስተዋወቂያ መርሀ ግብር ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የተለያዩ ከመንግስትና ከግል ተቋማት የመጡ አመራሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በዳግማዊት ግርማ (ኢ.ፕ.ድ)

See also  የትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎች ወደ መደበኛ ህይወት ሊመለሱ ነው

Leave a Reply