አድርቃይ በቁጥጥር ስር ዋለች – አፋር እየገፋ ነው፤ “ስለ ጦርነቱ ዝርዝር መረጃ አትስጡ”

ራሱን ” ጦርነት ሰሪና ለጦርነት የተፈጠረ” አድርጎ በመሳል የሚታወቀው የትግራይ ወራሪ ሃይል በዛሬው እለት አድርቃይን ማስረከቡ ተገለጸ። ስለ ጦርነቱ ድል ሳይሆን ዝርዝር መረጃዎችን የሚሰጡና በሰበር እያስጮሁ ሳንቲም የሚለቅሙ ሚዲያዎች ስራቸውን በሃላፊነት እንዲሰሩ ተጠየቀ። በሱዳን የሰለጠነውና የሚደገፈው የዚሁ ወራሪ ሃይል አካል ተደጋጋሚ ሙከራ መክሸፉም ታውቋል።

ከትግራይ ተነስቶ አብዛኛውን የአማራና አፋር አካባቢዎች በመውረር ለጆሮ የሚታክት፣ ለማየት የሚያም፣ ህሊናንና ማንነትን የሚፈታተን ተግባር ፈጽሞ በዘመቻ ለህብረትና ለአንድነት ሰፊ የተባለ ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት ደርሶባት እንደተሸነፈ በመረጃ የተረጋገጠበት ይህ ወራሪ ሃይል በአዲርቃይ በኩል ትንኮሳ መፈጸሙን ተከትሎ ነው ጥቃት የተፈጸመበት።

በጥቁር የተከበበው የተለቀችው ከተምና በአፋር በኩል ወደ ትግራይ የዘለቀውን የጦርነት አቅጣጫ ለማሳየት ነው

ከትናንት በስቲያ ትንኮሳ የጀመረው ወራሪ ሃይል በኢትዮጵያ የጥምር ሃይሎች ገንብቶት የነበረው የአምባ ጉላይ የኮንክሪት ምሽግ በአጭር ውጊያ ተደርምሶበታል። በዚያው ቀን የጨው በርና በርማ ማሪያምን ለማስረከብ እንዲገደድ የሚያችል ጥቃት ከምድርና ከላይ ወርዶበት ጉዳት ደርሶበት እንዳፈገፈገ ታውቋል። እግሩን የነቀለውና ከምሽጉ የወጣውን ወራሪ የትህንግ ሃይል በመከተል ወደ አዲርቃይ የተወረወረው ሃይል ዛሬ አመሻሽ ላይ ማረፊያውን አዲርቃይ ላይ ማድረጉ ተሰምቷል።

የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል “እንዴት ነው አድርቃይ ጋራ ሸንተረሩ፣ ጀግኖች የዋሉበት አፈሩና አየሩ” ሲሉ ለድሉ በቀጥታም ባይሆን በተዘዋዋሪ አድናቆታቸውን አበርክተዋል።

“ክብር ልጀግናው የጥምር ሰራዊታችን፣ ክብር ለጀግኖች እናት ኢትዮጵያ” ሲል ውዳሴያቸውን በማሰማት አድርቃይ ከትህነግ መነጠቋን አረጋግጠዋል።

አድርቃይ በሰሜን ጎንደር ዞን የምተገኝ፣ በደቡብ ዣን አሞራ፣ በደቡብ ምዕራብ ደባርቅ፣ በሰሜን ከትግራይ፣ በምስራቅ ከጠለምት ኩታ ገጠም የሆነች ህጋዊ የአማራ ክልል አካል የሆነች ከተማ ነች።

በሌላ ዜና በአባላ በኩል ወደ አፋር ዘልቆ የገባ የትግራይ ወራሪ ሃይል የገነባው ምሽጉ ተድርምሶና ጉዳት ደርሶበት ከሸሸ በሁዋላ የአፋር ልዩ ሃይሎች ጥቃታቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን አስታውቀዋል። ሰፊ ቁጥር ያላቸው እጅ መስጠታቸውንም አመልክተዋል። “እጅ የሰጡት ቁጥር ስፍር የላቸውም” ከማለት ውጪ በአሃዝ አላስታወቁም። የአፋር ልዩ ሃይል ዛሬም የማጥቃትና የከበባ ስፍራውን በማጠናከር ዛሬ ጦርነቱ ኩይሃ ላይ መድረሱን አመልክተዋል። የት ሲደርሱ እንደሚያቆሙ ለጊዜው ያሉት ነገር የለም። ስለ አድርቃይም ሆነ በአፋር ግንባር ጦርነቱ ኩይሃ ስለመድረሱ የትህነግ የኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት በተለመደው የማህበራዊ ገጹ ያለው ነገር የለም። አቶ ጌታቸው አረዳም እንደወትሯቸው በቲውተር ገጻቸው ምላሽ አልሰጡም።

በተመሳሳይ ዜና በሳምንቱ ለሶስተኛ ጊዜ ሃይሉን አሰባስቦ በሱዳን ድንበር በኩል ከሱዳን ሃይሎች ድጋፍ ታግዞ ከውስጥ ያለውን የትህነግ ሃይል ለመደገፍና የውጊያ ጫና ለመፍተር የመጣውን ወራሪ ሃይል ጥምር ሃይሉ ሙሉ በሙሉ እንደደምሰሰው ለአካባቢው ቅርብ የሆኑ አመልክተዋል። በዚያ አቅጣጫ ያለው ሃይል ” አለት” እንደሆነ በመጠቀስ ስጋት እንደሌለም አነዚሁ ክፍሎች አመልክተዋል።

“ድርድር ብሎ ነገር የለም፣ ከማንስ ጋር ነው የምንደራደረው?፣ የሚድን ከተማ የለም፣ እጅ ስጡ አለያ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር ይጨርሳችኋል፣ አዲስ አበባ ዙሪያ ነን፣ ሰራዊቱ ተደምሦ አልቋል…” ሲሉ የነበሩት የወራሪው ሃይል መሪዎች ዛሬ ላይ የሰላም ጥያቄ ሲያነሱ፣ ጎን ለጎን በወልቃይት በኩል ሃይላቸውን አጠናክረው ውጊያ ሊከፍቱ ማሰባቸው ተሰምቶ እንደነበር ይታወሳል።

የዚሁ ወራሪ ሃይል መሪ ከሆኑት መካከል አንዱ የሆኑት ጻድቃን ሰሞኑንን በድርጅት ሳይሆን በግል ጻፉት በተባለው ደብዳቤ የዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ከቃል ውጪ ያደረገው ድጋፍ አለመኖሩን ማንሳታቸው ከትናንት በስቲያ ድርጅቱ ገመገመ ብለን ካተምነው ዜና አንጻር ለራሳቸው ጥቅም ሲሉ የኢትዮጵያን መንግስት ለማስገደድ የሚጠቀሙባቸው ሃይሎች በቶሎ ወደ ለየለት ድጋፍ ወይም “የሚያሽመደመድ” ማዕቀብ እንዲዛወሩ መማጸኛ ሆኖ ተወስዷል። ይህ ካልሆነና ጊዜ ከወሰደ ምን አልባትም በግምገማው እንደተቀመጠው የመክሰሙ አደጋ ፍጥነቱ እንደሚጨምርም ያመልካታል።

“የድል ዜና መዘገብና ማግነን መልካም ቢሆንም፣ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያ በድሮንና በዘመናዊ መሳሪያዎች የታገዘ ሰራዊት መግንባቷ ያበሳጫቸው ሃይሎች ገመድ ለማጥበቅ ሁሉንም መንገድ እየሞከሩ ባለበት ሰዓት መከላከያ በዚህኛው መሳሪያ ደመሰሰ። አወደመ ብሎ ምስክር መሆን ጥቅም የለውም” ሲል መረጃውን ለማረጋገጥ የደወልንላቸው የመንግስት ሃላፊ ነግረውናል። አያይዘውም ” ለሳንቲም ለቀማ እየተባለ የሚጯጯህ ዜና ጉዳት እንዳለው ከግናዝቤ ውስጥ በማስገባት የጦርነት ዜና መዘገብ እንደማይቻል መንግስት ላወጣው መመሪያ አለመገዛት ቢያስጠይቅም፣ ከዛ በላይ ሁሉም ዜጋ ሊታገለውና ሊገስጸው ይገባል” ብለዋል።

ዛሬ ወራሪው ሃይል ካደረሰው ጥፋት አንጻር ፉከራ ሳይሆን፣ ድምጽን አጥፎ በዕልህ መልሶ ግንባታና ይህ ክፉ ሃይል ዳግም እንድያጠቃ ማምከን ላይ ትክረት የሚደረግበት እና ብሄራዊ አቋም የሚያዝበት ወቅት መሆኑንን እንደ ዜጋ ሃላፊነት ወስዶ ማነቃቃት እንጂ፣ ኢትዮጵያ ይህን መሳሪያ ተጠቀመች የሚለው ዜና ላይ ማተኮር ከግል ከርስ የዘለለ እይታ አለመኖሩን ያሳያል” ብለዋል። ይህ አይነት አካሄድ ያለው በጥቂቶች ዘነድ ብቻ ሲሆን አብዛኞች ሃላፊነት ወስደው መንቀሳቀሳቸውን ደግሞ ክብር እንደሚገባው አመልክተዋል።


Leave a Reply