በባለቤታቸው የጥምባሆ ጭስ ካንሰር – “አልወቅሰውም”

“በአፍንጫዬ መተንፈስ አልችልም። የምተነፍሰው ‘ስቶማ’ በሚባልና አንገቴ ላይ በሚገኝ ቀዳዳ አማካይነት ነው’’ ይላሉ የ75 ዓመት የዕድሜ ባለጸጋዋ ናሊኒ ሳትያናርያን።

ናሊኒ በህይወታቸው እንድም ቀን ሲጋራ አጭሰው አያውቁም። ነገር ግን ላለፉት 33 ዓመታት ባለቤታቸው ከሚያጨሱት ሲጋራ የሚመጣ ጭስ ሲተነፍሱ ኖረዋል።

ባለቤታቸው ሕይወታቸው ካለፈ ከአምስት ዓመታት በኋላ በአውሮፓውያኑ 2010 ላይ ናሊኒ ካንሰር እንዳለባቸው ተነገራቸው።

“ባለቤቴ አጫሽ ነበር። የእሱ ሲጋራ ማጨስ እኔን ይሄን ያክል ይጎዳኛል ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር። ለእሱ ጤና ነበር የምጨነቀው። ሁሌም ሲጋራ ማጨሱን እንዲያቆም ነበር የምነግረው። ነገር ግን ሲጋራ ማጨሱን አልተወም ነበር” ይላሉ በሕንዷ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ሀይድራባድ የሚኖሩት ናሊኒ።

የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ሲጋራ በየዓመቱ እስከ 8 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ይገድላል። ከእነዚህ መካከል ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ ሲጋራ አጫሽ አይደሉም። አብዛኞቹ በዙሪያቸው የሚገኙ ሰዎች ሲጋራ አጫሾች የሆኑ ናቸው። 

በርካቶችም በዚሁ ምክንያት ለተለያዩ ሕመሞች እየተጋለጡ ነው። በየዓመቱ ግንቦት 23 የዓለም የፀረ ትንባሆ ቀን ነው።

ግራፍ

የጉሮሮ ካንሰር

ናሊኒ በአንድ ወቅት ለልጅ ልጃቸው ታሪክ እያጫወቷት እያለ ነበር ድንገት የድምጻቸውን መቀየር ያስተዋሉት። በአጭር ጊዜ ውስጥ ደግሞ በትክክል አንዳንድ ድምጾችን ማውጣት እያቃታቸው መጣ። ከትንሽ ጊዜ በኋላ ደግሞ መተንፈስ ጭምር ከባድ እየሆነ መምጣት ጀመረ። 

ናሊኒ ወደ ህክምና ቦታ ሲሄዱ ያልጠበቁትን ዜና ሰሙ። ካንሰር እንዳለባቸውና በቀዶ ሕክምና ጉዳቱን መቀነስ እንደሚቻል ተነገራቸው። በቀዶ ሕክምናውም ድምጽ የሚያወጣው የጉሮሯቸው ክፍልና የታይሮይድ ዕጢያቸው እንዲወገዱ ተደረገ።

“ከሕክምናው በኋላ መናገር አልቻልኩም። በጣም የሚያሳዝን አጋጣሚ ነበር። ዶክተሮቹ የቀድሞ ድምጼን ደግሜ ማግኘት እንደማልችል ነገሩኝ።”

የናሊኒ የልጅ ልጅ የሆነችው የ15 ዓመቷ ጃናኒ ተጨዋች የሆኑት አያቷ ላይ የሆነውን ነገር በደንብ ታስታውሳለች። “ካንሰር እንዳለባት ሲነገራት ለረጅም ጊዜ እኛ ጋር አልነበረችም። ተመልሳ ስትመጣ የአራት ዓመት ልጅ ነበርኩ። ሆዷ አካባቢ ቱቦ ነገር ተለጥፎባት ነበር። ቤታችንን ቶሎ ቶሎ ማጽዳት ነበረብን። አያቴ ምን አይነት ችግር ውስጥ እንደነበረች በደንብ አይገባኝም ነበር” ትላለች።

See also  ኢትዮጵያ በግዛቷ የሚያልፉ ሳተላይቶችን መረጃ መቀበል የሚያስችል ቴክኖሎጂ መግጠሟን ገለጸች

ናሊኒ በወቅቱ የነበረን ጥሩ ሕክምና ስላገኙ ከጊዜ በኋላ ተመልሰው መናገር ቻሉ። ነገር ግን በተለያዩ መርጃ መሳሪያዎች በመታገዝ ነው ድምጽ የሚያወጡት።“ይሄ ካንሰር የያዘኝ በባለቤቴ ማጨስ ምክንያት ነው” ይላሉ ናሊኒ። “አጫሾች በጣም ጎጂ የሚባለውን የሲጋራውን ጭስ ወደ ውጪ ነው የሚተነፍሱት። በዚህ መሀል በጣም ተጎጂ የሚሆኑት በአቅራቢያቸው የሚገኙና ያንን ጭስ ወደውስጣቸው የሚያስገቡ ሰዎች ናቸው።”  

ለሲጋራ ጭስ ተጋላጮች

የዓለም ጤና ድርጅት ሁሉም አይነት ሲጋራዎች ጎጂ እንደሆኑ ሁሌም ያሳስባል። ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ በማንኛውም የጤንነት ሁኔታ ላይ የሚገኙ ለጭሱ የሚጋለጡ ሰዎችም ተጎጂዎች ይሆናሉ።

በዓለም ጤና ድርጅት የአውሮፓ ቢሮ የትንባሆ ቁጥጥር ባለሙያ የሆኑት አንጄላ ቺባኑ እንደሚሉት፣ የማያጨሱ ሰዎች ለአንድ ሰዓት ያክል ለሲጋራ ጭስ ቢጋለጡ በተለይ በጉሮሯቸው አካባቢ ቀላል የማይባል ጉዳት ይደርስባቸዋል።

አክለውም “ከሌሎች ሰዎች ለሚመጣ የሲጋራ ጭስ የሚጋለጡ ሰዎች ከ700 በላይ ኬሚካሎችን ነው ወደ ውስጣቸው የሚያስገቡት። ከእነዚህ ኬሚካሎች መካከል ደግሞ 70 የሚሆኑት ለካንሰር የሚያጋልጡ ናቸው። እነዚህ ሰዎች በሳንባ ካንሰር የመያዝ ዕድላቸው ከ20 እስከ 30 በመቶ ከፍ ያለ ነው” ይላሉ ባለሙያዋ።

የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ 65 ሺህ የሚሆኑ ህጻናት በየዓመቱ በሲጋራ ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍ ይገልጻል። ከዚህ በተጨማሪ ለሲጋራ ጭስ የሚጋለጡ ህጻናት በጆሮ ኢንፌክሽን የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው። አንዳንዴ ባስ ሲል ደግሞ  የመስማት ችሎታቸውን ሊያጡ ይችላሉ።

“ለሲጃራ ጭስ የተጋለጡ ህጻናት ለመተንፈሻ ችግር የመጋለጥ ዕድላቸው ከ50 እስከ 100 በመቶ ከፍ ያለ ሲሆን፣ ለአስም እንዲሁም ለድንገተኛ ሞት የመጋለጥ ዕድላቸውም ከፍተኛ ነው” ይላሉ አንጄላ ቺባኑ።

ጥቂት የማይባሉ ሲጋራ የሚያጨሱም ሆነ የማያጨሱ ሰዎች ሲጋራ ማጨስ መከልከል አለበት ብለው እንደሚከራከሩ የዓለም ጤና ድርጅት ይገልጻል።

“ሙሉ በሙሉ ከሲጋራ ነጻ የሆኑ አካባቢዎች መኖር ውጤታማ የሆነ ለውጥ ማምጣት ይችላል። ሰዎች አጠገባችሁም ሆነ ልጆቻችሁ አካባቢ እንዲያጨሱ አትፍቀዱላቸው። ንጹህ አየር መተንፈስ ሰዎች ሰብአዊ መብት ነው” ይላሉ አንጄላ ቺባኑ። 

See also  ‘ፓትሪዮት’ አሜሪካ ለዩክሬን የምትሰጣት ብዙ የተነገረለት አየር መቃወሚያ  

ነገር ግን ሲጋራ ማጨስን ሙሉ በሙሉ መከልከል በጣም ከባድ ነው። በዘርፉ ላይ በተሰራ አንድ ጥናት መሰረት የሲጋራው ኢንዱስትሪ በአውሮፓውያኑ 2021 ብቻ 850 ቢሊዮን ዶላር አንቀሳቅሷል። ይህ ቁጥር በአፍሪካ ከፍተኛውን የህዝብ ቁጥር ከያዘችው ናይጄሪያ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት ሁለት እጥፍ ነው።   

ጥናቱ እንደሚለው በቢሊየኖች ዶላሮችን መድበው የሚንቀሳቀሱት ከፍተኛ ትርፍ የሚያገኙ ትልልቅ ድርጅቶች ሲጋራ ማጨስን ለማስከልከል የሚደረጉ ጥረቶች ላይ ጫና ያሳድራሉ። 

ለሲጋራ ጭስ መጋለጥ እራሱ ለጤና ችግር ያጋልጣል
የምስሉ መግለጫ,ለሲጋራ ጭስ መጋለጥ እራሱ ለጤና ችግር ያጋልጣል

ረጅም ትግል

አይኑሩ አልቲቤቫ መሰል ሕጎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ከሚሰሩ የሕንድ የሕዝብ እንደራሴዎች አንዷ ናቸው። በአውሮፓውያኑ 2018 ላይ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ሲጋራ ማጨስ እንዲከለከል ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረውም ነበር።

እሳቸው እንደሚሉት ሕንድ ውስጥ በየዓመቱ ከሲጋራ ጋር በተያያዘ ከ6 ሺህ በላይ ሰዎች ሕይወታቸው የሚያልፍ ሲሆን መሰል ቦታዎች ላይ ማጨስን መከልከል ደግሞ የሚደርሰውን ጉዳት እስከ 10 በመቶ ድረስ መቀነስ ይቻላል።

ነገር ግን የሕዝብ እንደራሴዋ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።

“የሕዝብ እንደራሴዎቹ እራሳቸው በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከትምባሆ ኢንዱስትሪው ጋር ግንኙነት አላቸው። ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ሲጋራ ማጨስ የሚከለክለው ሕግ ወደተመረጡ ኮሚቴዎች ነበር የተመራው። ነገር ግን ኮሚቴዎቹ ሆነ ብለው እንዲያዘገዩት ነው የተደረገው። የኢኮኖሚ ጉዳዮች ሚኒስቴርም ቢሆን ከታክስ የሚገኝ ገቢ ላይ ቅናሽ እንደሚኖር በመግለጽ ሀሳቡን አልደገፈውም ነበር’’ ይላሉ።

“አንዳንድ ሰዎች እንዲያውም በማኅበራዊ ሚዲያዎች በኩል እኔንም ሆነ ቤተሰቤን ማጥቃት ጀምረው ነበር።”

አይኑሩ አልቲቤቫ ላለፉት ዓመታት እልህ አስጨራሽ ትግል ካደረጉ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2021 ላይ ሕንድ ውስጥ ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ሲጋራ ማጨስ ተከልክሏል። ነገር ግን ሥራው እዚያ ላይ አላበቃም።

አይኑሩ ሲጋራ ማጨስ በጤና ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት እንዲሁም ህጻናት ላይ የሚያመጣውን መዘዝ በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶችን ያስተባብራሉ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በትምባሆ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ለመቀነስ ከሚደረጉ ጥረቶች መካከል በአውሮፓውያኑ 2005 ይፋ የተደረገው የትምባሆ ቁጥጥር ስምምነት ተጠቃሽ ነው። እስካሁን ድረስ 182 አገራት የዚህ ስምምነት አባል ለመሆን ፈርመዋል።

See also  ሕገወጥ እርድ እስከ 25ሺህ ብር አልያም በእስር እንደሚያስቀጣ ተገለጸ

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት አገራት ሕዝብ በተሰበሰበባቸው አካባቢዎች ሲጋራ ማጨስን እንዲከለክሉም ይወተውታሉ።

ሰዎች ንጹህ አየር የመተንፈስ መብታቸው እንዲጠበቅ ሲባል መሰል ሕጎች ተግባራዊ መሆን አለባቸው የሚሉት ደግሞ በትምባሆ ቁጥጥር ላይ የሚሰራው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የሚሰሩት ዶክተር ሜሪ አሱንታ ናቸው።

“ከትምባሆ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ሞቶችን ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ማገዝ የሚችሉ በርካታ እርምጃዎች አሉ። በዋነኛነትም የትምባሆ ምርት ላይ ከፍተኛ ግብር ማስከፈል፣ ማስታወቂያዎች ላይ ቁጥጥር ማድረግ እንዲሁም ስለጉዳቱ ከፍተኛ ትምህርት መስጠት ይጠቀሳሉ።”

ናሊኒ ሳትያናርያን
የምስሉ መግለጫ,ናሊኒ ሳትያናርያን

‘ባለቤቴን አልወቅስም’

ምንም እንኳን የዓለም ጤና ድርጅት የሲጋራ አጫሾች ቁጥር ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ነው ቢልም፣ አሁን ላይ የሲጋራ አጫሾች ቁጥር 1.3 ቢሊየን ነው።

ድርጅቱ እንዲመለው ከአስር ሰዎች አንዱ ሲጋራ የሚያጨስ ሲሆን አብዛኞቹ ደግሞ የሚያጨሱት ቁጥጥር የማይደረግባቸውና በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱትን ነው።

ሕንድ ሃይድራባድ ውስጥ ነዋሪ የሆኑት ናሊኒ አሁን ላይ ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ አቅደዋል። አሁንም ድረስ ጉሮሯቸው ላይ ባለው ቀዳዳ አማካይነት ብቻ የሚተነፍሱት ናሊኒ በሲጋራ ምክንያት የማንም ሰው ሕይወት እንደዚህ ሊበላሽ አይገባም ይላሉ።

ናሊኒ ወደ ትምህርት ቤቶች እንዲሁም ማንኛውም ሕዝብ ወደሚሰበሰብባቸው ቦታዎች በመሄድ ስለሲጋራ ጉዳት የግንዛቤ ማስጨበጫ ዝግጅቶችን የሚያከናውኑ ሲሆን፣ በትርፍ ጊዜያቸው ደግሞ ከልጅ ልጆቻቸው ጋር በመጫወት ያሳልፋሉ።

በባለቤታቸው ሲጋራ አጫሽነት ምክንያት ለካንሰር ተጋልጠው ለከባድ የጤና ችግር ቢዳረጉም በሟቹ ባለቤታቸው ላይ ምንም አይነት ቂም አልያዙም።

“በባሌ ላይ ፈጽሞ አዝኜበት አላውቅም። ባጋጠመኝ ነገር ላይ ማዘን ምንም የሚለውጠው ነገር እና የሚቀርፈው ችግር የለም። አሁን እኔ እውነታውን ተቀብዬ ስላጋጠመኝ የጤና ችግር ለመናገር ፈጽሞ አላፍርም” ይላሉ።

ሙሉ ዘገባው የቢቢሲ ነው

Leave a Reply