ወንጀል ሲፈፅም ጤነኛ ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ እንደ እብድ እያደረገው ሲያጭበረብር የነበረው ”አውቆ አበድ” በቁጥጥር ስር ውሏል

ወንጀል ሲፈፅም ጤነኛ የነበረው ግለሰብ ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ እንደ እብድ አድርጎታል፡፡ ዕብደቱ ግን ”አውቆ አበድ” ይሉትን አይነት ነበር፡፡ ሽንት እና ሰገራውን በላዩ ላይ ይፀዳዳል፡፡ የአዕምሮ ህመምተኛ መስሎ ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ያልቆፈረው ጉድጓድ፣ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም።

ጌቱ ከበደ እና ጌቱ ነጋሽ በሚል የተለያዩ ስሞች የሚጠቀመው ይኸው ግለሰብ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ሉባር ሆቴል ተብሎ ቢጠራው አካባቢ ከለሊቱ 10፡ 40 ሰዓት ገደማ በአንድ የመኖሪያ ቤት ውስጥ ገብቶ 19 ሺህ ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ አልባሳትን ሰርቆ ሲወጣ በአካባቢው ነዋሪዎች እጅ ከፍንጅ ሲያዝ ነበር ዕብደቱ የጀመረው፡፡

ወዲውኑ ራሱን የሳተ መስሎ መሬት ላይ ተጠቅልሎ ተኛ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ግን በተፈጠረው ድንገተኛ ነገር ተገርመውም ተደናግጠውም ፖሊስ ጠሩ፡፡ ፖሊስ በስፍራው ሲደርስም ወንጀል ፈፃሚው አይናገርም፤ አይጋገርም፡፡

ችግሩን በህክምና ለማወቅ ወደ ጤና ጣቢያ ተወሰደ፡፡ ጤና ጣቢያውም ወደ ቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሪፈር ፃፈ፡፡ ሆስፒታሉም ባደረገው ምርመራ ምንም ችግር የለበትም ብሎ ምላሽ ሰጠ፡፡ ወንጀል ፈፃሚው ግን የጤና ለውጥም ሆነ መሻሻል አላሳየም፡፡ በድጋሚ ወደ ተለያዩ የህክምና ተቋማት ለተጨማሪ ምርመራ በተደጋጋሚ በተለያዩ ቀናት ተወሰደ፡፡ አሁንም ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡፡

ፖሊስ ጥርጣሬ ገብቶታል፡፡ ከተጠያቂነት ለማምለጥ የፈጠረው ዘዴ መሆኑን በተለያዩ ሁኔታዎች አረጋግጧል፡፡

ግለሰቡ ከ1990 ዓ/ም ጀምሮ 16 የተለያዩ ወንጀሎችን ስለመፈፀሙ፣ በተለያዩ 6 ስሞች የሚጠቀም ስለመሆኑ ከፌደራል ፖሊስ ፎረንሲክ ምርመራ የተገኘው የጣት አሻራ ሪከርድ ማስረጃ የፖሊስን የጥርጣሬ ከፍታ ጨምሮታል፡፡ ምናልባት የአዕምሮ ችግር ይኖርበት ከሆነ በሚል እሳቤ ከአቃቤ ህግ ጋር በመነጋገር የወንጀሉን ጉዳይ እየተመለከተ የሚገኘው ፍርድ ቤት ለአማኑኤል የአዕምሮ ህክምና ሆስፒታል ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠየቁ፡፡ ሆስፒታሉም ምርመራ ለማድረግ በቀጠሮ አሰናበታቸው፡፡

ጌቱ ከበደ ወይም ጌቱ ነጋሽ ለ3 ወራት ያህል ፖሊስ ጣቢያ ሲቆይ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሰው ፖሊስ ተሸክሞት ነበር፡፡ ቀን ቀን መፀዳጃ ቤትም አይሄድም፡፡ ምሽት ላይ ደግሞ እዚያው ማረፊያ ክፍል ውስጥ ይፀዳዳል፡፡ ፖሊስ ደግሞ የቆሸሸውን እና የተበላሸውን ማረፊያ ክፍል ያፀዳል፡፡ አንዳንድ ወንጀል ፈፃሚዎች እንዲህ አይነት የማምለጫ ዘዴዎችን ይጠቀማሉ፡፡ ወንጀል ከፈፀሙ በኋላ ሰገራቸውን እላያቸው ላይ በመፀዳዳት ማንም እንዳይጠጋቸው ያደርጋሉ፡፡ ይህ ዘዴ ደግሞ ለፖሊስ አዲስ አልነበረም፡፡ እናም ጌቱ ከበደ ወይም ጌቱ ነጋሽ በዚህ መንገድ ዕድሉን እየተጠቀመ በነፃ እንዲለቀቅ ጥረት ሲያደርግ ተስተውሏል፡፡

ፖሊስ ምግብ ሲያቀርብለት አይበላም፡፡ ነገር ግን ጭር ሲልለት የተሰጠውን ምግብ ይሰለቅጠዋል፡፡ ፖሊስ ሲያየው ይተኛል ፤ ፖሊስ ከአጠገቡ ሲርቅ ደግሞ ተነስቶ ይቀመጣል፡፡ እንዲህ ሲያደርግ ደግሞ የፖሊስ አባላት ተከታትለው በሞባይል ስልካቸው በድብቅ ቀርፀውታል፡፡

የ3 ወራቱ የፖሊስ ጣቢያ ቆይታው በዚህ ሁኔታ ከተጠናቀቀ በኋላ ፍርድ ቤቱ በማረሚያ ቤት ቆይቶ ጉዳዩን እንዲከታተል ወሰነ፡፡ ፖሊስም ተጠርጣሪውን ለማረሚያ ቤት ወስዶ ሲያስረክብ ማረሚያ ቤቱም በሸክም የመጣ ተጠርጣሪ አንቀበልም ብሎ መለሳቸው፡፡

ይህንኑ ፍርድ ቤቱ እንዲያውቀው ከተደረገ በኋላ ተጠርጣሪውን እንዲቀበል ፍርድ ቤቱ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ የጤንነቱን ሁኔታ የሚያረጋግጥ የህክምና ማስረጃ እስኪመጣ ድረስ በዚህ ሁኔታ ውሳኔ እየተጠባበቀ ማረሚያ ቤት ውስጥ ለ 1 ዓመት ያህል ከቆየ በኋላ ከአማኑኤል ሆስፒታል የህክምና ምርመራ ውጤት መጣ፡፡ ጌቱ ከበደ ወይም ጌቱ ነጋሽ ምንም አይነት የአዕምሮ ህመም የለበትም የሚል፡፡

ጉዳዩን ሲመለከት የቆየው የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አዲስ ከተማ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የህክምና ማስረጃውን ከተመለከተ በኋላ ጥር 25 ቀን 2013 ዓ/ም በፈፀመው የስርቆት ወንጀል በ5 ዓመት እስራት እንዲቀጣ በቅርቡ በዋለው ችሎት ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡

አውቆ አበድነቱ እውነትን አላሸነፈለትም፤ አሸናፊው የፖሊስ ትዕግስት ሆኗል፡፡ ፖሊስ በትዕግስቱም የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ አድርጓል፡፡

Ena news

Leave a Reply