“…ጎን ለጎን ከ20 ሀገራት ስኬታማ የዲፕሎማሲ ውይይት” አምባሳደር ታዬ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ጎን ለጎን ከ20 ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ስኬታማ የዲፕሎማሲ ውይይት ማድረጋቸውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አማካሪ አምባሳደር ታዬ አፅቀስላሴ ገለጹ።

የአፍሪካ ሕብረት 42ኛ የስራ አስፈፃሚዎች ምክር ቤት ስብሰባ እና 36ኛው የመሪዎች መደበኛ ጉባኤ በስኬት መጠናቀቁን አስመልክቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አማካሪ አምባሳደር ታዬ አፅቀሥላሴ፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ እና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

አምባሳደር ታዬ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በጉባዔው ዋዜማ የጊኒ ቢሳው ፕሬዚዳንት ዑማሮ ሲሶኮ ኢምባሎ በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ዋና ዓላማ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተለያዩ መስኮች ማጠናከርን መሰረት ያደረገ ነው።

የሳይንስ ሙዚየምን ጨምሮ ዘመኑን የዋጁ ተቋማትን እና ለሀገሪቱ የብልፅግና ጉዞ መሰረት የጣሉ ስራዎችን ለፕሬዝዳንቱ በማስጎብኘት ልምድ እንዲቀስሙ መደረጉንም ነው ያነሱት።

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ ላጋጠሟት ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ፈተናዎች ሳትበገር ዘርፈ ብዙና አስደናቂ ለውጥ ማስመዝገቧን በማየታቸው መደነቃቸውን እንደተናገሩም እንዲሁ።

አምባሳደር ታዬ አክለውም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ በመሪዎቹ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግራቸው ከ60 ዓመታት በፊት የአፍሪካን ትብብር ለማረጋጥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሰረቱ ቀደምት አፍሪካውያንን ራዕይ ማድነቃቸውን ጠቅሰዋል።

ከእነሱ በመማር የአፍሪካን መፃኢ እድል ብሩህ ለማድረግ የሚያግዙ አዳዲስ ሀሳቦችን በንግግራቸው እንዳንጸባረቁም እንዲሁ።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ያጋጠሙ ችግሮችን በኢትዮጵያዊ ጥበብና አርቆ አሳቢነት በመሻገር የቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴን ንግግር በተግባር መፈጸሙን ማውሳታቸውን አንስተዋል።

አፍሪካ ችግሯን በራሷ መፍታት እንደምትችል ጠቅሰው፤ የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የአህጉሪቱን ፈተናዎች በአፍሪካዊ ትብብር መቋቋምና መፍታት እንደሚቻል የኢትዮጵያን የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን በአብነት ጠቅሰው አብራርተዋል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመረችውን ጉዞ ሌሎችም አፍሪካውያን በመከተል ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሔ የመስጠት መርህን በተግባር መተርጎም እንዳለበት በንግግራቸው ማመላከታቸውንም ነው ያነሱት።

See also  የአለም ባንክ ለኢትዮጵያ 195 ሚሊዮን ዶላር ሰጠ

የአህጉሪቱ 60 በመቶ ጉዳዮች በሚስተናገዱበት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ መቀመጫ ባለማግኘቷ የመብትና የፍትህ ጥያቄዋ እየተመለሰ እንዳልሆነ በመጠቆም፤በቀጣይ በፀጥታው ምክርቤት፣ በቡድን ሰባትና በቡድን 20 አባል እንድትሆን በአፅንኦት መጠየቃቸውን ተናግረዋል።

የዓለም አቀፉን ሚዲያ የተንሸዋረረ አተያይ ለመቀልበስ አፍሪካ የራሷን ሚዲያ አቋቁማ የገፅታ ማስተካከል ስራ ላይ እንድታተኩርም በንግግራቸው ጠቁመዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ከ36ኛው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ጎን ለጎን ከ20 ሀገራት መሪዎች እና ዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች ጋር ስኬታማ የዲፕሎማሲ ውይይት ማድረጋቸውንም ነው አምባሳደር ታዬ የተናገሩት።

በዚህም ኢትዮጵያ ከሀገራትና ከተቋማት ጋር ያላትን የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከፍ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል። OMN

Leave a Reply