ስንዴና ፖለቲካው!!

የኢትዮጵያ ስንዴ ምርት መጨመሩን፣ ጭማሬው ደግሞ በጋና ክረምት ሳይል፣ ቦታ ሳይመርጥ በሶማሌና አፋርና ክልል በርሃ ላይ ሳይቀር መታየቱ “እስከዛሬ የት ነበርን?” የሚል ቁጭትን ፈጥሮ ገሃድ የታየ ነው። በዛው ይህል የስንዴ ምርት በማደጉ ” ሃዘን የገባቸው” እንዳሉም ይታወቃል። ሁሉንም ነገር በማንቋሸሽና ከፖለቲካ ጋር በማጋባት ለህዝብ ማቅረብ የተለመደባት ኢትዮጵያ፣ የኤክስፖርት ጅማሬውን እንዳላየ ባለፉ ሚዲያዎች የዱቄት አምራቾችን ቅሬታና ለቅሶ እንዲሁ እንደወረደ እየቀረበለት መሆኑ አግባብ እንዳልሆነ የሚናገሩ አሉ። አራት ዓመት በተከታታይ ዝናብ ባጡ አካባቢዎች ችግሩ እየተባባሰ ሲሄድ ምን ሊያስከትል እንደማይችል የማይረዱ ስብሰባ አድማቂዎች ጉዳይ አሳሳቢ እነደሆነም በተመሳሳይ የሚናገሩ ጥቂት አይደሉም።

ጥያቄው “ለምን እጥረት አለ ተባለ” ሳይሆን፣ አቤቱታ የቀረበበትና እንዲቀጣጠል የተደረገበት መንገድ ግርምት መፍጠሩ፣ ዜናውን የሚያሰራጩት ደግሞ የተመጠነና ጥንቃቄ የተሞላው መረጃ አለማቅረባቸው እነደሆነ ትዝብታቸውን የገለጹ ያስረዳሉ። እነዚ ወገኖች ለኢትዮጵያ ህዝብ መልካም ዜና እንዳይሰማ የተፈረደበት ያህል ዕለት ዕለት ተሳ እንዲያጣና ትውልዱ አርቆ እንዳያይ ጫና እየፈጠሩ መሆናቸውን ስለም መረዳት እንዳቃታቸው የሚያስረዱት በመገረም ነው።

እነዚ አካላት እንደሚሉት ኢትዮጵያ ስንዴ ኤክስፖርት ማድረግ መጀመሯ ይፋ በሆነ ማግስት “ስንዴ ለአገር ሳይተርፋት ለውጭ” በሚል የፖለቲካ ካባ አልብሰው ማቅረባቸው ሚዛን የጎደለው ነው ሲሉ የዜናውን ቃና አልወደዱትም። ልክ እንደ አባይ ግድብ ሙሌት። አባይ ተርባይኑ ተቀንሶ አቅሙን በማሳደግ በአነስተኛ ቁጥር የቀደመውን ሃይል ለማምረት ክለሳ ሲደረግ በአሜሪካ የሚደጎሙ ወገኖቻችን ሳይቀሩ “ውስጥ አዋቂ ነገረን” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግድቡን ለመሸጥ መስማማታቸውን አትመው እንደነበር የሚያስታውሱ፣ ዛሬም እነዛ ወገኖች የተከፋይነታቸውን ዓላማ እንጂ የአገሪቱን ችግር እንደማያስቀድሙ ያመለክታሉ።

የስንዴ አቅርቦትና ክትትል ጉዳይ ላይ ችግር እንዳለ የማይክዱ ወገኖች ” ስንዴ ከመንግስት በተመጣጣኝ ዋጋ እየገዙ አየር በአየር የሚቸበችቡና የሚከዝኑ እንዳሉ እናውቃለን” ይላሉ። አያይዘውም የስንዴ ወደ ውጭ መላክ ዜና ሲጀመር የዱቄት ነጋዴውች ጩኸት ለምን እንደበረከተ አለመጠየቃቸው ሰሞኑንን ይፋ የሆነውን የኢትዮጵያ ትምህርት ጥራት ደረጃና አቅም መለስ ብሎ መቃኘትና የ”ቅሌታችን” ውጤት ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል ባይ ናቸው።

ለምሳሌ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ እያለ ከውጭ አገር እየገዛ የሚያስገባውን ስንዴ በእርሻ ሰብል በኩል በተመጣጣኝ ዋጋ ለዱቄት፣ ፓስታና መኮሮኒ አምራቾች ስንዴ በኮታ ይሰጥ እንደነበር የሚያስታውሱ፣ በአንድ ወቅት ወደ ኢህአዴግ ስንብት መቃረቢያ ዳቦ አምራቾች ” ዱቄት አጣን” ሲሉ በተደረገ ማጣራት በርካታ ዱቄት ፋብሪካዎች ስንዴውን አየር በአየር ያሻግሩት እንደነበር በማስረጃ ተረጋግጧል። እህል በረንዳ ምስክር ነው።

See also  ኢትዮጵያና አረብ ኤምሬትስ 2 ሺህ ሜጋ ዋት የፀኃይ ኃይል ማመንጫ ለመገንባት ስምምነት ተፈራረሙ

በወቅቱ እህል ተራ ያሉ ጫኚና አውራጆች፣ የእህል ደላሎችና ገዢዎች ሲመሰክሩ ” ለምን የሰራተኛ ደሞዝ፣ ነዳጅ፣ ኤሌክትሪክ ወጪ እናወጣለን? ማሽን ማስጠገን ማሰራት ውስጥ ምን ከተተን?” እያሉ ሶስትና አራት እጥፍ ስንዴውን በመሸጥ ትርፍ ይሰበስቡ እንደነበር ገልጸዋል። በውቅቱ አንድ ዱቄት ፋብሪካ ተቃጥሎ የመድን ካሳ ሲጠይቅ ከፍተኛ ዕህል ክምችት እንዳለው ጠቅሶ ነበርና ዋትና የገባበት ድርጅት በህግ እንደሞገተው ማስረጃ በመጠቀስ ምን ያህል አሳፋሪ ቅጥፈት ይፈጸም እንደነበር ገልጸዋል። ጉዳዩን ከብዙ ጎኑ ማየትና የማየት አቅም ግድ የሚሆነው እዚህ ላይ እንደሆነም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ የዕህል ምርት፣ ሰሊጥና መላው የቅባት እህል ጨምሮ እያለ፣ በብዙ ሚሊዮን ኩንታል ልዩነት አሳይቶ እያለ እጥረት ለምን ይፈጠራል? በሚል ሚዲያዎች ከስር ገብተው ችግሩን ማሳየት ሲገባቸው እያግለበለቡ የሚሰሩት ዓላማው የማይታወቅ ዜና ህዝብ ግራ እያጋባ ነው። ኢቶጵያ የቅባት ምርቷ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ ሳለ፣ ቡናና የጥጥ ምርቷ አድጎ ሳለ ለምን ከፍተኛ ምንዛሬ እንዳልተገኘ መመርመር የሚዲያዎች ተግባር መሆኑን የሚናገሩት ወገኖች ” የወደፊቱ አሳሳቢ ጉዳይ የፉክክር ቤት ነው” ብለዋል። ሁሉም በሚቀርበው በኩል እያጋዘ እንደሆነ ሲጠቁሙ ነገርየው እስከ ምጽዋ መድረሱንም ፍንጭ በመስጠት ነው።

በርካቶች እንደሚሉት ኢትዮጵያን የኢኮኖሚ አሻጥር አንቆ ይዟታል። በሲሚንቶ እንደታየው ሁሉ በግብርና ምርቶችም ላይ ተመሳሳይ ቀውስ አለ። ምርት በከፍተኛ መጠን ጭምሯል። ዋጋ ግን እየናረ ነው ለምን? ይህ ብቻ አይደለም ትርፍ ማግበስበስም ይስተዋላል።

ተራ የቲማቲምና ሽንኩርት ገበያ ቢመረመር የሚገዛበትና ለተጠቃሚ የሚደርስበት ዋጋ አስደንጋጭ የትርፍ ስዕል የሚታይበት ቢሆንም ለሚዲያ ፍጆታ የሚውለው ” ሽንኩርት በኪሎ …. ገባ” የሚለው ዜና እንጂ በአብዛኛው በገዢውና በአምራቹ መካከል ያሉትን አሳማዎች እንደማይዳስስ የሚናገሩ ወገኖች፣ አካሄዱን በአብዛኛው የአገሪቱ ሚዲያዎች ሰባራ የመሆናቸው ምልክት አድርገው ይወስዱታል።

አንድ ኪሎ ስጋ ከአጥንት ጋር ለዚያውም ሰው እየተመረጠበትና የኪስ እየታከለበት 1500 ብር በላይ ሲሸጥ ” የሚዲያ ሰዎችና ካድሬዎች ሲቆርጡ እንጂ፣ እንዴት ሆኖ? በማለት ዋጋውን አስለተው አይተቹም” የሚሉ እነዚህ ወገኖች የስንዴውንም ጉዳይ የሚያነሱት በዚሁ አግባብ ነው።

See also  “ዓላማችን ዶንባስን ነጻ ማውጣት ነው” ሩሲያ አልተሳክቶም?

“አምራች ድርጅቶቹ እጥረት ቢኖርባቸውም ይህን ያህል የጮሁት እውነት ዳቦ ጋግረው፣ ፓስታ አምርተው ለደሃው ህዝብ በተመጣጣኝ ዋጋ ለመሸጥ? ወይስ?” የሚል ጥያቄ የሚነሳበት የስንዴ እጥረት ዜና ስንዴን ኤክስፖርት ከማድረግ በላይ የገነነው በሌላ ተልዕኮ ስለመሆኑ ከጥርጣሬ በላይ ሆኖባቸዋል። በአባይ ግድብ ሙሌት “ኒኩሌር ታጠቀች” የተባለችው ኢትዮጵያ የስንዴ ቸነፈሯን የሚያራግፈውን ዜና ለማወየብ የሚኬድበት መንገድ ችግሩን ሊቀርፈው እንደማይችል እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።

ሚዲያ ካለ ዩኒየኖች ዘንድ ሄዶ፣ አርሶ አደሩ ዘንድ ገብቶ፣ ፋብሪካ የተባሉት አካላት ዘንድ ዘልቆ፣ የስንዴ ገበያ ያለበት እህል በረንዳ ገብቶ በመሰለል ጥልቅ መረጃ ከመስጠት ይልቅ በስልክ የዕለት ፕሮግራምና ማስታወቂያ ማፈላለጊያ የሚሆን ሰባራ ዜና መስራት ከችግሩ በላይ አሳዛኝ እንደሆነም እንደ አገር ውድቀት መሆኑ የገባቸው ወገኖች በቅሬታ ይገልጹታል። ሲሳሳት ይቅርታ የማያውቀው የኢትዮጵያ የሚዲያ የሙቀት ልክ በዚህ ግለቱ ከቀጠለ አገሪቱን በማወክ፣ ትውልዱን ተስፋ በማስቆረጥ፣ ህዝብን ወደ ማይሆን ጠርዝ በመግፋት በአንድ ትውልድ የሚኮነንና ” ሚዲያ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ነበር” የሚያሰኝ ታሪክ የሚመዘገብለት እንደሚሆን ያምናሉ።

“የተሰማውን ሁሉ ማስጮኸ፣ ደርሶ ታጋይና አታጋይ የመሆን፣ በሌለ ማንነት ተጽዕኖ ፈጣሪ የመሆን አባዜ፣ ለገበያ የሚውል ከሆነ ምንም የማይመረጥበት የኢትዮጵያ ሚዲያ ህዝብን መጠቀም ቢፈልግ ልክ በአውቶቡስ ግዢ ላይ የታየውን ማጭበርበር ተረባርበው ያጋለጡበትን ዓይነት ሚና በተጫውቱ ነበር” በማለት ቁጭታቸውን የሚገልጹ ወገኖች ” አንዳንዶቹ እንኳን በሙያው ስም ሊጠሩ፣ የሰፈር ባህሪያቸውን ተከትሎ በተሰጣቸው ማንነት እንኳን ለመሰየም የማይመቹ ጨዋዎች፣ ደርሰው ፖሊሲ፣ ህግ፣ ፖለቲካና ማህበራዊ አውድን እንተቻለን ብለው ሲንጠራወዙ አለማፈራቸው ዶክተር ብርሃኑ ሰሞኑንን ያጋለጡት የትምህርት ንቅዘት ውጤቱ እዚህ እንዳደረሰን ነው” በማለት ከዚህ ቀውስ እንዴት መውጣት እንደሚቻል ማሰቡ ጭንቀት ውስጥ እንደሚከታቸው ይጠቅሳሉ።

ካድሬዎች ችግር አይፈጥሩም፣ እጥረቱም ሙሉ በሙሉ ተቀርፏል የሚል መከራከሪያ እንደማያቀርቡ የሚናገሩት ክፍሎች ” አገሪቱም ከውፍጮ ቤት በሚገዛ ዲግሪና በኩረጃ በተገኘ ማዕረግ ስለምትመራ ነገሩ አጠቃላይ ክሽፈት ነው” ሲሉ ያማርራሉ። ሕዝቡ ጨዋ በመሆኑና ቢዝቁት የማያልቅ ፈርሃ አማልክ ስላለው መሽቶ ይነጋል እንጂ በአብዛኛው የሚታየው ሁሉ አሳዛኝ እንደሆነ የሚገልጹት ወገኖች ” ነገሮችን ለያይቶ ማየት” ቢጀመር ሲሉ ይመክራሉ።

See also  ፑቲን ከዩክሬን ወደ አፍሪካ ለሚገቡ የስንዴ ምርቶች ሁኔታዎችን እንደሚያመቻቹ አሳውቀዋል

“ቦርና ድርቅ መግባቱ ዜና የሆነው ዛሬ አይደለም። ቦረና አራት ድፍን ዓመት ዝናብ ጠብ አላለም። ኢትዮጵያ አራቱን ዓመታት ወያኔ ከሚባል የሴራዎች ሁሉ አባትና እሱ ፈልፍሎ ካስፈለፈላቸው ሃይላት ጋር ትንቅንቅ ላይ ነበረች” ብለው ይጀምሩና ” ምንም እንኳን ጦርነት ላይ ቢኮንም፣ አራት ዓመታት ድርቁ እየሰፋ ይህን ያህል ጉዳት እስኪያደርስ ድረስ ዝምታ መመረጡ አግባብ አይደለም። ያስጠይቃል” ቢባል ለሰሚው ሚዛን የሚጠብቅ እንደሚሆን ይናገራሉ።

“ድርቅ ሃብቱን፣ ልጆቹንና ያለውን ሁሉ ላከሰመበት የቦረና ህዝብ መከራ፣ የቦረና ህዝብ ድርቅና የድርቁ ጣጣ ሁሉንም ፖለቲካው ላይ ለሚያንጠለጥሉ ሰርግና ምላሽ ሲሆን ማይት ያማል” የሚሉት ወገኖች የመንግስት ካድሬዎችን ልብስና መለዮ እየቀያየሩ በከተማ ምስረታና ተራ ጉሽሚያ ንብረትና ጊዜ ከሚያባክኑ ዓይናቸውን ሁሉ ወደ ቦረናና አካባቢው ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል። ድግስ በዝቷልና ይብቃ ሲሉም መክረዋል። የፎቶና የማህበራዊ ዳንኪራ በማቆም ትክረት ወደሚሻው ጉዳይ ማምራት አማራጭ እንደሌለውም ጠቁመርዋል።

“ዘይት አመርታለሁ” ብሎ በሚሊዮን ከመንግስት፣ “እሸጥላችዃለሁ ብሎ” የወረፋ ( ገና ለገና ምርት ይጀመራል ተብሎ ነው) በመቶ ሚሊዮኖች ከባንክ ወስደው ዘይት አከፋፋይ ለመሆን ጎምጅተው እዳ ታቅፈው ለኖሩት ሚዲያው በሩ ዝግ ነው። ለምን ቢባል ብሩ የመንግስ፣ ዘራፊው ጋባዥና ደጋሽ፣ ተዘራፊዎቹ … ሁሉም ቀርቶ ከሰማይ በላይ ተንሳፈው ዘይት በዘይት እናደርጋለን ብለው አንድ ሊትር ዘይት ያላመረቱ የሰሊጥና ኑግ ፖለቲከኞች ጉዳይ ግምት ውስጥ ማስገባቱ ይበልጥ ዋጋ እንዳለው እነዚሁ ወገኖች ይመክራሉ። ይህን አካሄድ ምጽዋም ድረስ ሄዶ ማረጋገጥ ካስፈለገ ቀዳሚ ሊሆን የሚገባው እንዲህ ያለው ጉዳይ እንደነበር ይጠቁማሉ። ሚዲያዎች ራሳቸውን እንዲያዩም ይማጸናሉ።

ስንዴ በቀጥታ ለዳቦ ፋብሪካዎች የሚደርስበትና ፓስታና መኮሮኒ በኪሎ ተሰልቶ ምርቱ ለመንግስት በስሌት የሚቀርበበት ስሌት ሊዘረጋ እንደሚገባ የሚናገሩት ክፍሎች ” አሁን አሁን መተማመን የለም፤ ሁሉም ከዛኝ፣ ሁሉም ደብቆ ከባሪ፣ ሁሉም ለግልና ለቡድን ጥቅም ቅድሚያ እየሰጠ አገሪቱን መከራ ላይ ጥለዋታል። ምስኪን ዜጎች እየተጎዱ ነው። ሚዲያ ምስኪን ዜጎችን ግንባር አድርጎ ሊሰራ የገባል” ሲሉ አስተያየታቸውን ያጠቃልላሉ።

Leave a Reply