የእጅ ስልክ የሰውን ልብና አዕምሮ በምን ያህል ደረጃ እንደተቆጣጠረ አስተውለዋል?

ብዙዎቻችን ስልካችን ላይ የምናጠፋው ጊዜ ሠፋ ያለ እንደሆነ እናውቃለን። በዚህም ምክንያት የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማናል። ከስልክ ለመራቅ ሲሉ ስልካቸውን የሚያጠፉ፣ ስልካቸውን ከራሳቸው የሚደብቁም አሉ። ከስልክ መላቀቅ ግን እንዲህ ቀላል አይደለም። በስልክ ብቻ የሚሠራ ነገር እንዳለ ወዲያው ይሰማቸው እና ስልካቸውን ይከፍታሉ። ሱስ ነው።

ቤተሰብ የሚጠየቀው፣ የቡና እንጠጣ ግብዣ የሚተላለፈው፣ ቤት ኪራይ የሚከፈለው፣ ማስታወሻ የሚያዘው፣ መብራት የሚበራው፣ ሒሳብ የሚሠራው በስልክ ነው። ታዲያ እንዴት ከስልክ ጋር ተለያይቶ ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት ይቻላል?

በአሜሪካ አዋቂዎች በቀን 344 ጊዜ ስልካቸውን እንደሚያዩ አንድ ጥናት ጠቁሟል። ይህም ማለት በየአራት ደቂቃው ስልካቸውን ያነሳሉ ማለት ነው። በቀን ወደ ሦስት ሰዓት ገደማ ስልክ ላይ ያጠፋሉ።

ኢሜይል ለማየት ወይም ማኅበራዊ ሚዲያ ለመጠቀም ስልካችንን ካነሳን በኋላ መልሶ ማስቀመጥ ይከብደናል። ነገሩ መውጫ የሌለው አዙሪት ነው። ስልክ የሚሰጠው ጥቅም በበዛ ቁጥር ስልክ ላይ የምናሳልፈው ጊዜ ይረዝማል። ስልክ ላይ የምናሳልፈው ጊዜ በረዘመ ቁጥር ስልክ የሚሰጠው ጥቅም ይበዛል። ማኅበራዊ ሚዲያ የእያንዳንዱ እንቅስቃሴ ‘የጀርባ አጥንት’ መሆኑ አእምሯችን ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አጥኚዎችን ያሰጋል።

ስልክን አዘውትሮ የማየት ጉጉት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለው ጥናቶች ይጠቁማሉ። በአንድ ጊዜ ብዙ ክንውን ለመፈጸም መሞከር በራሱ ውጤታማነት እና የማስታወስ ችሎታን ያውካል። ከዚህ ሁሉ ግን የከፋው ምሳሌ መኪና እያሽከረከሩ ስልክ መጠቀም ነው። የጽሑፍ መልዕክት ባያዩ እንኳን ስልክ እያወሩ መሄድ በራሱ አሉታዊ እንደሆነ ነው ጥናቶች የሚያሳዩት።

የስልክ መልዕክት ድምጽ ሲሰሙ ከሥራቸው የሚሰናከሉ ጥቂት አይደሉም። ስልክ መጠቀም ብቻ ሳይሆን፣ የስልክ መኖር በራሱ አስተሳሰባችን ላይ ተጽዕኖ እንዳለው የሚናገሩም አሉ። አንድ ጥናት ሲካሄድ የጥናቱ ተሳታፊዎች ስልካቸውን ማየት የሚችሉበት ቦታ ወይም ድብቅ ቦታ እንዲያስቀምጡ ተጠየቁ። የተለያዩ ጥያቄዎች ተሳታፊዎቹ እንዲመልሱ ተደረገ። የተሻለ ውጤታማ ሆነው የተገኙት ስልካቸውን ማየት የማይችሉበት ቦታ ያስቀመጡ ተሳታፊዎች ናቸው።

ስልክ

ስልክ ቅርባችን ሲሆን አእምሮ በግልጽ እንዳያሰላስል ያደርጋል። ስልክ ቅርብ ሲሆን ማየት እንዳለብን አእምሯችን መልዕክት ያስተላልፋል። አጥኚዎች መፍትሔ የሚሉት ስልክን እኛ ካለንበት ክፍል ውጭ ማድረግ ነው። በሌላ በኩል ስልክ ላይ የተንተራሰ ሕይወት አወንታዊ ነው ብለው የሚከራከሩም አልታጡም። ስልክ የዘነጋነውን እንድናስታውስ ያግዛል።

See also  ያልተገረዛችሁ ተገረዙ!! አሉ ጌታቸው ረዳ

ክቦች የተሰባሰቡበት ምሥል ተመልክተው ክቦቹን በአንድ ወገን ለይተው እንዲያወጡ ከተጠየቁ ሰዎች መካከል የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡት በስልካቸው የታገዙት እንደሆኑ አንድ ጥናት ይጠቁማል። አእምሮ መረጃ የሚያከማችበትን፣ አንዱን መረጃ ከሌላው አስቀድሞ የሚያቀብልበትንም መንገድ እንደሚያሻሽል አጥኚዎቹ ተገንዝበዋል። ችግሩ ግን ስልክ አጠገባቸው ከሌለ ሰዎች በራሳቸው ነገሮችን አለማስታወሳቸው ነው።

ሞባይል ስልክ የያዙ የሚመስሉ ጥንዶች አልጋ ላይ
የምስሉ መግለጫ,ሞባይል ስልክ የያዙ የሚመስሉ ጥንዶች

ከስልክ ጋር ያለን ቁርኝት አእምሯችን ላይ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ በትክክል ለማወቅ የዓመታት ጥናት ይሻል። በራስ መወሰን፣ ማሰላሰል፣ ማስታወስ እና ሌሎችም የአእምሮ ክኅሎቶች ላይ ምን እንደሚያሳድር የሚታወቀው ከዓመታት በኋላ ይሆናል።

ዴቪድ ሮብሰን በጉዳዩ ላይ መጽሐፍ አሳትሟል። ስልክ ደጋግመን ሳናይ አንድ ሥራ ላይ ማተኮር የማንችልበት መንገድ ማዳበር እንደምንችል ይገልጻል።

ስልክ ሳላይ መቆየት አልችልም ብለው ራሳቸውን ያሳመኑ ሰዎች ራሳቸውን ለመቆጣጠር ሲቸገሩ፣ በተቃራኒው ራሳቸውን የሚያጠነክሩ ሰዎች ያለ ስልክ ዘለግ ላለ ጊዜ እንደሚቆዩ ይናገራል።

ስልክን ሌላ ክፍል እያቆዩ ራስን ማለማመድ፣ አእምሮ ያለ ስልክ ድጋፍ የታመቀ አቅም እንዳለው ራስን ማሳመን እና ስልክ ማየት ሲያምረን ራሳችንን ማረሳሳት የተወሰኑ መፍትሔዎች ናቸው።

Leave a Reply