” ኢትዮጵያ ትውደም፤ አቆርቋዦቿም ይለምልሙ ” ቀይ ባህር !!

ጎበበዝ ሞተናል። ወይም የምናስበው የበድን ያህል ነው። መቀላቀል፣ መምታታት፣ መወዛገብ፣ መደናገር … የሚሉት ቃላቶች አይገልጹንም። ማሰብ ተስኖን ማንም ኮልኮሌ፣ ዓለማአቀፍ ለማኝ ይነዳናል። ልመና ብርቃቸው ለሆነ ይሉኝታ ቢሶች አጎብዳጅ ሆነናል። ከትልቅነት ይልቅ ትንሽነት ተጣብቶናል። በዚህም ሳቢያ “ትልቅ ነን” የሚሉ ሲነሱ ዘለን አመድ ላይ መንደባለል እንመርጣለን። መርመጥመጥን ወግ አድርገን የማጅራት መቺ መሪ አጎብዳጅ ሆነናል። ማጅራት መቺ!! ያበደው ይደግመዋል ማጅራት መቺ …. “ኢትዮጵያ ትውደም። አቆርቋዦቿ ይለምልሙ” የምትሉ የኢትዮጵያ እንግዴዎች …. ያበደው አዘነ። ተመልሶ “እንግዴዎች ጥቂት ናቸው” ሲል ተጽናና … ቀይ ባህር ወይም ሞት!!

ኢትዮጵያ ለወደብ በየዓመቱ የምታወጣው አንድ የህዳሴ ግድብ ይገነባል። ሰላሳ ዓመት የገፍገፍነው ሃብት ምን ያህል ነው? ማን አስገፈገፈን? ማን እዚህ ውርደት ውስጥ ጣለን? ሰላሳ ዓመት በገፍገፍነው ሃብት ምን ለናደርግበት እንችል ነበር? ያበደው ጠየቀ። ቀይ ባህርን ላስቆለፉብን … ያበደው በሆዱ ተራገመ። “የአማራ ቀይ ባህር አራት ኪሎ ነው” ያበደው ሳቀ። ” መጀመሪያ አራት ኪሎ፣ ቀጥሎ ቀይ ባህር?” መሆኑ ነው። ያበደው አሽካካ። “መጀመሪያ አማራ ክልልን፣ ቀጥሎ ኢትዮጵያ” ብለው ነበር ታላቁ …. በቅጽበት መፈክሩ ተቀይሮ ” የአማራ ቀይ ባህር አራት ኪሎ ነው” ሆነ!! ያበደው አስተያየት ከመስጠት ይቆጠባል!!

” ወሬ ሲወስድ እያስገለፈጠ፣ ወሬ ሲገድል እያስደነሰ ነው” ቢባል ማን ከልካይ አለ? “ውሃ ሲወስድ እያሳሳቀ ነው” እንደሚባለው ማለት ነው። ለተረትና ለስሜታዊ አገላለጽ ደረጃ የምትመድቡ የራስችሁ ጉዳይ። በብሄርም፣ በጎሳም፣ ከዛም ወርዳችሁ በደም ተደራጁ … ያበደው አያገባውም። ለብሄር እርምጥምጦችም ጆሮ የለውም። “ኢትዮጵያ ትውደም፤ አቆርቋዦቹ ይለምልሙ” ለሚሉ ያበደው መስሚያው ጥጥ ነው። እንደውም … ይቅር … ሊለው ያለውን ዘለለው፤

እንዴት ሰነበታችሁ። እዚህ በጋው አልቆ ክረምትን የሚያስገመግመው አደንዛዥ ብርድ ጀምሯል። እዚያ እናንተ ዘንዳ መስኩ አሽቷል። አብቧል። ቡቃያው ወደ ጎተራ ሊሰበሰብ ነው። ተጠፋፍተን ከረምን…. ሰላም የለም። እዛም እዚህም ሞት ነው። ዩክሬን አሜሪካና አጀንዳዋን ወክላ የሩሲያን አረር እየጠጣች ነው። አይናቸው እያየ አገራቸው ወደ አመድነት ስትቀየር ያልነቁትን ዩክሬናዊያን “የፈረንጅ መሃይሞች” እያሏቸው ነው። አይናቸው እያየ በማያውቁት ጉዳይ ወደ አገራቸው ወደ አፈርነት ተቀየረች። እነሱም ተሰልፈው መብላት ጀመሩ። ተሰደዱ። “አሜሪካ የጅሽን ይስጥሽ” ትላለች ቦሰና። እውነቷን ነው!!

ጋዛም በሚሳይልና ቦምብ እየነደደች ነው። እስራኤል ዙሪያዋን ፍም ሆናለች። ረምጦ የኖረው እሳት ዙሪያዋን እያጋማት ነው። የመጨረሻውን መተንበያ ባይቻልም፣ አያያዙ የወትሮው አይነት አይመስልም። ሰላማዊ ዜጎች እያለቁ ነው። እየተሰደዱ ነው። ሃማስ ድንገት አጥቅቶ ፍጅት ፈጸመ። ከዛም ከዚህም ነጹሃን አለቁ። እያለቁ ነው። ገና ያልቃሉ ….

አማራ ክልልም እየጦዘ ነው። ማን እንደሚያጦዘው ግልጽ አይደለም። ግን ከበሮ ይሰማል። ሳዋ አድብቶ ስራውን የሰራ ይመስላል። ወዲ አፎም አዲስ አበባ እየተመላለሰ … ያበደው ዝም አለ። ለማሰብ ከአንድ ሃውልት ዘንድ ቆመ። ሃውልቱ ከብዙ እርቃናቸውን ከቆሙት ሃውልቶች መካከል አንዱ ነው። ሰው ካላሰበና በልቡናው ሚዛን ካልተመራ ከሃውልት በምን ይልቃል?

ሃውልቶች!! አንዷ አንገቷን ሰበር አድርጋ እጇን እንደዋዛ እዳሌዎቿ መካከል ጣል ያደረገቸበት ጥበብ ያስገርማል። ያበደው “አሁን ከቆሙት በምን ታንሻለች?” አለና የዳሌዎቿን ውበት ገረመመ። ቦሰናን በልቡ ይቅርታ ጠይቆ “ጨዋታው ወዲህ ነው” አለና ሃውልትና ቋሚ ህያዋንን መዘነበት። ሃውልቶቹ የድንቅ ባለሙያ የእጅ ስራ ውጤቶች ናቸው። ህያዋን ሆነው እየተነፈሱ፣ ደማቸው እየተዘዋወረ ሃውልት የሆኑ አሉ…. ማሰብ ያቆሙ… የማይጠይቁ፣ የማይመረመሩ …

See also  በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሮፌሰር - የዓለምፀሐይ መኮንን

“ሰማዕት ማለት ምን ማለት ነው?” ያበደው ጠየቀ። ደብረብርሃን ድረስ ወሮ የመጣ ወይስ ደጁ ድረስ ሊወሩት የመጡትን አንጥፎ የሞተ? ጎበዝ ተዘባርቆብናል። የሰማዕትና የሰማዕታት ትርጉም በገሃድ ተቀሽቧል። ቦሰና ” ሟቾች ያሳዝናሉ። ከምንም በላይ ሃዘን የሚያቃጥላቸው እናቶች …” ትልና ….. “አማራና አፋር ደጃቸው ላይ የተዋደቁትስ ምን ሊባሉ ይሆን? ለሁሉም ነበስ ይማር” ብላ ማለት የምትፈልገውን ጉንጯ ውስጥ አጉተምትማ ታልፈዋለች።

ጌታቸው ረዳ ትላንት አዝማች ነበር። “ለጦርነት የተፈጠርክ፣ የማትወድቅ ልዩ ፍጡር…” እያለ ይማግድ ነበር። ዛሬ መርዶ አርጂ፣ የሰማእት ማዕረግ አዳይ ሆኗል። ደብሬም እንደዛው ነው። መላው ትህነግ ከነደጋፊዎቹ … የትግራይ ህዝብ ግን ምን ነካው? ያበደው ይጠይቃል? “ሰልጥን፣ ዝመት፣ ተዋጋ፣ ….” ሲባል “እሺ”፤ ወላጆችም ልጆች መርቀው ወደ ጦርነት፤ “ሃዘን ተቀመጡ” ሲባሉም “እሺ!!” …. ቦሰና “አቦ ነዲሲ” (ተወኝ) ትላለች። የትግራይ ህዝብ ትህነግ ምን ሲለው ነው “እምቢ፣ ላስብበት፣ ልመርምር፣ ጊዜ ልውሰድ የሚለው?” … በዛም ተባለ በዚህ “ነብስ ያማር”። አዎ ነብስ ይማር። ማንም ይሁን ማን ቤተስብ ነው። የአገር ልጅ ነው። ትርክቱ ግን ሁሌም ይደንቃል!! ያበደው ተቆናጠረ። ዞር ሲል አንድ አሮጊት አየ!!

በሚፋጀው ብርድ ከውስጥ የሚያሞቅ ልብስ ተላብሰዋል። ከላይ የሚችሉትን ያህል ለብሰው ያበሻ ነጠላ ደርበዋል። እኚህ አዛውንት ሊኖሩ እማይገባቸው ስፍራ እየኖሩ እንደሆነ ለመረዳት ምርምር አይጠይቅም። ግን ለምን መጡ? በዚህ እድሜያቸው ለምን ይሰቃያሉ? ኢሳያስን አፉወቅን መጠየቅ ነው። እኚህ ሴትና እሳቸውን መሰል ብዙዎች “ንጻነት” ብለው ኦስሎ ፈንድሻ ሲረጩ ያበደው በየዓመቱ ያያል። ነጻነት!! … ቦሰና አዲስ አበባ ሮጠች። አዲስ አበባ ጅል ከተማ። አዲስ አበባ ቂሎ። ኢትዮጵያ ማህጸኗ … ተጉተመተመች። ቦሰና ሲያናጫት ደጎል ስለሚገባው ቀስ ብሎ ቤቱን ይለቃል።

አውሮፓ፣ አሜሪካ …. ሁሉም የዓለም ዙሪያ እድሜ ሳይገድባቸው የኤርትራ ተወላጆች ተበትነዋል። ኢሳያስ በዚህ ይኮራሉ። አዲስ አበባ ከአንድ ሚሊዮን በላይ የኤርትራ ተወላጆች አሉ። የሚኖሩት እንደ ኢትዮጵያዊ ነው። ቤት የሚከራዩት የሚገበያዩት በኢትዮጵያ ብር ልክ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ነው። ያበደው በዚህ ደስተኛ ነው። ይህን መልካምነት እንደ ጅልነት ለሚቆጥሩት ያዝንላቸዋል። በዚህ ደግነት ስር ኮንቶባንድና ገንዘብ አጠባ ይሰራል።ይህ ኢትዮጵያን ማጅራት መምታት ነው። ድግ አይደልም። ህዝብ ይቀየማል። እንዲህ የሚያደርጉት ሁሉም አይደሉም። የኢሳያስ ወኪሎች ናቸው። ኢሳያስ ኢትዮጵያን ማጅራት መምታት ስራቸው ነው። ቡና ዘርፈው ኤክስፖርት ያደርጉ ነበር። ሰሊጥ ተጀምሯል። ዶላር የተለመደ ነው። አሜሪካ ያለው ቢሮ ምስክር ነው … ያበደው ” አገር መውደድ ለአንዱ ትክክል ለሌላው ትክክል የማይሆነው ለምንድን ነው?” ሲል አዲስ አበባ የተወለዱ ወዳጆቹን “ኤርትራዊያን” ይጠይቃል።

ያበደው ድንገት ብልጭ አለበት። ለሻዕቢያ መሰለል፣ መነገድ፣ መርዳት፣ መስራት …. ኢትዮጵያ ወስጥ ለነበሩ ወይም ላሉ የኤርትራ ተወላጆች ጽድቅ ነው። ለኢትዮጵያ መስራት፣ መሰለል፣ መነገድ፣ ማሰብና መቆርቆር ኩነኔ ነው። ነበር። ያበደው ” ስለወላዲቷ” ሲል ቅን ፍርድን ጠየቀ። ሃዘኑን ወደ ላይ አንጋጦ አስተላለፈ። ሃውልቶቹ መካከል ሆነ ድንጋይ ሲጠረብ ያለውን ውበት አደነቀ!! ደንጋይ!!

See also  አረንጓዴው ጎርፍ ሲታወስ፤ "የኢትዮጵያ ህዝብ ለማስደሰት እስከመጨረሻው ተስፋ አልቆረጥኩም" ጉዳፍ ፀጋይ

ቦሰና እናቷ ” ባለሰባት፣ ያስጠምድሽ ….. እኔ ነኝ የምትይ የማሪያም ወዳጅ ” እያሉ ጽዋ ሲለዋወጡ እያየች ነው ያደገችው። አማራ ክልል ከማን ተቀብሎት እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም ትህነግ ” ባፍንጫዬ” ያለውን ጦርነት ተረክቧል። አማራ ክልል እዛም እዚህም እየነደደ ነው። በአማራ ክልል ደማቸውን ያፈሰሱ፣ አጥንታቸውን የከሰከሱ፣ ህይወታቸውን የገበሩ የአገር መከላከያ አባላት ” እንዳትለቀው በያለበት አስቀረው” እየተባሉ ነው። ኢትዮጵያ ያ ሁሉ ድንቅ ባህሏ ነጥፎ ነገር እንዲህ በፍጥነት የሚቀያየርበትና አብረው የበሉበት ሌማት የሚገለበጥበት አገር ሆና አረፈችው።

ፋኖና መከላከያ ክንዳቸውን አጋምደው፣ በአንድ ጉድጓድ እንዳልተሰው፤ ዛሬ ይጋደላሉ? ግን ማን ነው ከሁዋላ ያለው? ማን ነው የሚሾፍረው? ሳዋ የነበሩት እነማን ናቸው። ያበደው የሳዋ ስም ሲነሳ አንድ ጉዳይ ልቡና ውስጥ ተቀረቀረ። ሳዋ መቼ ነው “ለሶማሌ” እያለ ወታደር እያስለጠነ ኢትዮጵያ ድንበር ስር መድፋቱን የሚያቆመው? ከዚህ ቀደም አልሸባብ ምናምን የሚል ሃሜት ነበር። ጎበዝ ረጋ ብሎ መመርመር ይገባል።

በሰሜን ወንድም ከወንድሙ እንዲባላ ተፈርዶበታል። በምስራቅ ወዳጅ መሳዮች ጦር እያሰለጠኑ ያፈሱበታል። ኦሮሚያ ብረት ያነገቡ ዛሬ በብረት የሚፈጸም ምን ጥያቄ እንዳላቸው ባይታወቅም እንደ ጃርት ሲቆፍሩ ነው የሚያድሩት….. ያበደው ሃውልቶቹን እይዞረ ” እናንተ ትሻላላቹህ” እያለ ተሰናበተ። በሚሊዮን የሚቆጠር ቱሪስት የሚጎበኛቸው የድንጋይ ሃውልቶች ….

እውን የኢትዮጵያን ጉዳይ ለሚከታተል፣ የሚሆነው ሁሉ ከሰው የሚጠበቅ አይደለም። ድንጋይ ተውቦ ቆሞ በልጦናል። ትልቅ ሆነን ሳለ ከእኛ ለማይሻል ልቅላቂ እንታዘዛለን። ፍጹም ደጃችን ሊደርሱ ለማይገባቸው ጅራታችንን እንቆላለን። ያበደው ተፋ። አማራ ክልል ሳያገገም እንዲደማ የምትፈርዱ …. ተጠንቀቁ። አማራ እንደ ህዝብ ጉዳት አለበት። የገባበት ውጊያ ግን መፍትሄ አይደለም። አጀንዳው የማጅራት መቺው ነው። አጀንዳው የቀይ ባህር ነው። አጀንዳው እርስ በርስ በማባለት የቀይ ባህርን አጀንዳ ለማኮላሸት ታልሞ የሚሰራ ነው። ይህ ” ኢትዮጵያ ትውደም፤ አቆርቋዦቿም ይለምልሙ ” የሚለው መፈክር ባይሳካም የማይሽር ጠባሳ ማኖሩ አይቀርም። ጠንቀቅ!!

ኢሳያስ ሽብር በመፈልፈል ምጡቅ ናቸው። ወያኔን አበቁ። ኦነግን አደረጁ፣ መሸጉ፣ የትግራይ ተቃውሚ አሰለጠኑ። የአማራ አርበኞች ግንባር ብለው አስታጠቁ። በቅርቡም ሳዋ በይፋ አሰልጥነው አስመርቀው ደፉብን። ሶማሌ እያስለጠኑ ወደ ምስራቅ እየላኩ ነው። አዲስ አበባም ኢኮኖሚውን የሚዠልጡ አሉዋቸው። ይህንን ሁሉ ሲያደርጉ ” እሳቸው ለኢትዮጵያ” የሚሉ ሚዲያዎችና አክቲቪስቶችም አሉዋቸው። ያበደው ሁሉም ይታወቃሉ” ሲል ያ እንቶኔ የተናገረውን ይደግማል። እናም ይህ ዘመን የድሮው አይነት አይደለምና ክቡር ፕሬዚዳንት ኢሳያስ “ከኢትዮጵያ ላይ እጅዎን ያንሱ” ስትል ቦሰና ትማጸናለች። “ይበቃል” ስትል ኢትዮጵያ በኢሳያስ በትር የሚደርስባትን መቋቋም እንዳቃታት ታስታውቃለች። “የወርቅ ጥርሳቸው ተነቅሎ የተባረሩት የኢትዮያን ልጆች ቁስል አትነካኩ” ትላለች። እዛ ሰፈር የተሰለፋችሁ የ ” ኢትዮጵያ ትውደም፤ አቆርቋዦቿም ይለምልሙ ” ዘፋኖች አቁሙ!! ቀይ ባህር የኢሳያስ ብቻ አይደለም። ኢትዮጵያም መብቷን በምትችለው ሁሉ ለማስከበር ትሰራለች!! አለቀ!! ይህ የማይቀር ነው!! ዝግጅቱ ሁሉ ያለቀ ይመስላል። የጅል ዘመን፣ የሴራ ዘመን በዛሬዎቹ ትንታጎች ያበቃል!! በጋር መኖር፣ በጋራ መጠቀም!!

See also  ወጣቱ ለሰባት ዓመታት እንቅልፍ ባለመተኛት ሪከርድ ያዘ

ከዚህ ሰፈርም በመንግስት ውስጥ የተወሸቃችሁ ባለ ተራዎችም አደብ ግዙ!! ያበደው አሁን መሽቶበታል። ሰላም ሁኑ!!


Leave a Reply