በአማራ ክልል ጦርነቱ ህዝቡን አሰላችቷል፤ በጎንደር ሽንኩርት በኪሎ 120 ብር ገባ

በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው አዲስ ጦርነት ህዝቡ ላይ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖበታል። ከጦርነት ያላገገመ ክልልና ህዝብ ለሌላ ችግር ተጋልጧል። ጦርነት ዳፋው ሰላማዊ ነዋሪዎች ላይ ነውና አሁን ላይ ከክልሉ የተለያየ አካባቢዎች የሚወጡ መረጃዎች ዕረፍት የሚነሱ፣ መፍትሄው ምንድን ነው? እስከመቼ በዚህ ይቀጥላል? የሚሉ ስጋት አዘል ጥያቄዎችን ለማንሳት ያስገድዳል።

የጤና ተቋማት፣ የትራንስፖርት አውታሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ እርሻ፣ ንግድ፣ ማህበራዊ አገልግሎቶች ተዳክመዋል። ሙሉ በሙሉ የቆሙባቸው አካባቢዎችም አሉ። አሁን ላይ አንጻራዊ መሻሻል እየታየ እንደሆነ ምስክሮች ቢናገሩም ችግሩ አሳሳቢ ስለመሆኑ የሚከራከር የለም።

ክልሉ ገቢውን መሰብሰብ አልቻለም። አገለግሎት በወጉ ካልቀረበና የክልሉ እንቅስቃሴ በሁሉም መልክ ወደ ቀድሞ ካልተመለሰ ቀጣዩ ዓመት አሳሳቢ እንደሚሆን ከወዲሁ ባለሙያዎች በስጋት እየተናገሩ ነው።

በተለያዩ አደረጃጀቶች ጦርነት የከፈቱት ሃይሎች የሚፈለጉትን በአጭር ጊዜ አሳክተው የክልሉን ህዝብ ከመከራ ይታደጉታል የሚለው እይታ እጅግ የተመናመነ በሚመስልበት በአሁኑ ወቅት፣ በቅርብ ዓመታት መሪዎቹን ያጣው፣ በጥቅሉ መሪ የማይበረክትለት የአማራ ክልል ጉዳይ በንግግር እንዲቋጭ መፍትሄ ለመፈለግ የሞከሩ ” የጦርነቱ ባለቤቶች ብዙ ናቸው” ሲሉ ዋናውን ባለቤት አግኝተው ለማነጋገር መቸገራቸውን አስታውቀዋል። ይሁን እንጂ ሙከራው እንደቀጥለ እነዚህ ክፍሎች ገልጸዋል።

በአማራ ክልል የልማት ስራዎች ተስተጓጉለዋል። አንዳንዶቹም ፕሮጀክቶች “አልቆሙም” ለማለት ያህል ካልሆነ በቀር ይህ ነው የሚባል እንቅስቃሴ አይታይባቸውም። የአባይ አዲሱ ድልድይ እንኳን እየተጓተተ ነው። የአማራ ክልል ወቅታቂ ሁኔታ የሚያስጨንቃቸው በየትኛውም መንገድ ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ እየወተወቱ ነው። አለያ ችግሩ ተባብሶ የክልሉን ህዝብ መከራ የከፋ እንደሚያደርገው እየገለጹ ነው።

ሕዝብም በገሃድ ” ተነጋገሩ” እያለ ምሬቱን እየገለጸ ነው። የኑሮ ውድነት የሚለበለበው ህዝብ ” ችግር ጠናብን” በሚል ህምመማቸውን እያስታወቁ ነው። እንቅስቃሴ ቆሞ፣ ገቢ ቆም፣ ኑሮ ንሮ … በዚህ ላይ ሌባ ነጋዴዎች ዝርፊያ ላይ መሰማራታቸው የህዝቡን ስቃይ አንሮታል። አሁን ላይ በየሚዲያው የሚነገረው የክልሉ ህዝብ ሮሮ ሁሉንም ወገኖች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርግ ሆኖ ሳለ ” ከውጭ ግፋ በለው” የሚለው ፕሮፓጋንዳ ይህ እንዳይሆን አበርክቶ አለው። አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ” ከውጭ ፕሮፓጋንዳ የሚያሰራጩት ክፍሎች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ለክልሉ ህዝብ ሰላምና መረጋጋት ከቶውን ም የሚያስቡ አይደሉም። ከፍተኛ ንግድ ላይ ናቸው። ጦርነቱን እየነገዱበት ነው። ህዝብ ቆሞ ሊያስብና ችግሩ በውይይት እንዲፈታ ጫና ሊያደርጉ ይጋባል” ሲሉ ይደመጣሉ።

በገንዘብ፣ በሃላፊነትና በጦርነት አፈ ቀላጤነት ከየግንባሩ ያሉትን፣ በዞን፣ በሰፈርና በተወላጅነት በየአቅጣጫው ተከፋፍለው ጸብ የገቡት የማህበራዊ ሚዲያ አዝማቾች የተጋነነ፣ አንዳንዴም የፈጠራ፣ ሲልቅም ለማመን ያሚያስቸግር መረጃ እያሰራጩ ነው። ጉዳዩ ከቤተክርስቲያን ጋር በማቆራኘት የሚሰራው ቅስቀሳም ሰሞኑንን ከላሊበላ በግልጽ አባቶችና ነዋሪዎች እንደምሰከሩት መሰረቱ የተናጋ ቢሆንም ሊያደርስ የሚችለው ጣጣ የከፋ፣ የህዝብን ስሜት የሚያበላሽ፣ ከምንም በላይ ሊተካና ሊመለስ የማይችል ነብስ የሚያጠፋፋ በመሆኑ እነዚህኑ አካላት የሚደግፉ ረጋ ብለው ከራሳቸው ጋር ሊመክሩ እንደሚገባ እየተገለጸ ነው።

See also  የድሮ ሪፖርት ቃል በቃል ገልብጦ ሪፖርት ያቀረቡት ሚኒስትር “ ነውረኛ” ተባሉ

የክልሉ መንግስታን አሁን በውጊያ ላይ ያሉትን የተለያዩ አካላት አንድ ላይ ሊወያዩ የሚችሉበት አግባብ እንዲፈጠር ግፊት ማድረግ የሚጋባቸው ሚዲያዎች፣ በማወቅም ይሁን በልዩ አጀንዳ ተሸካሚነት፣ በየሰዓቱ እየደፉ ያለው የትርምስ መረጃና ቅስቀሳ ” አስቀድሞ ነበር …” የሚለውን ተረት የሚያስታውስ በመሆኑ ” እስከዛሬ የነገዳችሁት ይበቃችኋል። ህዝቡን ተውት” ሊባሉ እንደሚገባ አሁን አሁን ድምጽ እየተሰማ ነው።

ከምንም በላይ የአማራን ህዝብ የሚመጥኑ፣ አርቀው የማያዩ፣ ሌሎችን በመሳደባን በመግፋት ሳይሆን በበሰለ ፖለቲካ የክልሉን ህዝብ በደል አንስተው መታገልና ማታገል የሚችሉ ባለ ግርማ ሞገስ ፖለቲከኞች በአማራ ክልል አለመፈጠራቸው በርካቶችን የሚያሳዝን ጉዳይ ነው። አሁን አሁን እንደሚባለው እዛና እዚህ የሚለጠፉና የሰው አጀንዳ ተሽክመው ክልሉን እንደሚማግዱ የጸብ አትራፊ ነጋዴዎች ሳይሆን፣ ማንም ሊክደው የማይችለውን የአማራን ህዝብ በደል የሁሉም ዜጎች በደል በማድረግ የሰለጠነ ፖለቲካ ማራመድ የሚችሉ አለመፈጠራቸው ምክንያቱም የማይገባቸው በርካታ ናቸው።

ለስልጣን አቋራጭ መንገድን የሚመርጡ ሳይሆኑ በትክክል የህዝቡን ጥያቄ በማንሳት፣ ለህዝብ ጥቅም የሚታገሉ ጀግኖች ቢኖሩም የሚዲያው የደቦ ዘመቻና ማስፈራሪያ አብዛኞችን እያሸማቀቀ በዝምታ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል። አብዛኞች በዚህ ሳቢያ ዝም ማለታቸው የአማራ ህዝብ ጉዳይ እማይሆኑ እጅ ሊወድቅ እንደቻለ በጥናት የሚናገሩ አሉ።

ቀደም ሲል ጀምሮ እንደ እራፊ ጨርቅ እየተለጣጠፈ የኖረው የክልሉ ፓርቲ ከልወጡ በሁዋላ በድፍረት ራሱን ባለማጽዳቱ መላ ሰውነቱ መንተቡን ያመለከቱ እንደሚሉት፤ ጥሩ ከሚባሉ አገር ውስጥ ካሉ ተቃዋሚ ሃይሎች ጋር መክሮ በጋራ መስራቱ ይጠቅማቸዋል። አሁን ላይ የማጥራት ስራ እየሰራና አዲስ አደረጃጀትና አመራር እየሰየመ ያለው የክልሉ መንግስት ይህንንም ቢያስብበት እንደሚበጀው ያክልላሉ።

ከስር ያለውን የኑሮ ውድነት ማሳያ ዜና ያንብቡ

” የሽንኩርት ሽያጭ ዋጋ በኪሎ 60 ብር ነበር አሁን በእጥፍ አድጎ እስከ 120 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው ” – የጎንደር ነዋሪ

” በሚታየው የዋጋ ጭማሪ ምክንያት የዕለት ከዕለት ኑሮን መግፋት አስቸጋሪ ሆኖብኛል ” – የጎንደር ነዋሪ

በጎንደር ከተማ ተከስቶ የነበረውን ግጭት መነሻ በማድረግ በኢንዱስትሪና በግብርና ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ በመከሰቱ የዕለት ከዕለት ኑሯቸውን ለመምራት መቸገራቸውን ያነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ይናገራሉ፡፡

See also  ”የባለቤቴን ሬሳ ከልጆቼ ጋር ለሦስት ቀን አቅፌ ሰንብቻለሁ“ ባለቤታቸው በግፍ የተገደሉባቸው እናት

ካነጋገርናቸው የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ወጣት አስተሪዮ አስማረ በሰጠው አስተያየት ቀደም የሽንኩርት ሽያጭ ዋጋ በኪሎ 60 ብር ነበር አሁን ዋጋው በእጥፍ አድጎ እስከ 120 ብር ድረስ እየተሸጠ ነው፡፡

የዘይትና የሌሎች የሸቀጥ ምርቶችም ላይም የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ታይቷል፡፡

ታዲያ የዋጋ ንረት በመከሰቱ ” የዕለት ከዕለት ኑሮዬን ለመምራት ተቸግሪያለሁ ” ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡

ሌላው በጉዳዩ ላይ አስተያየት የሰጡት የከተማዋ ነዋሪ አቶ ጎበዬ መኩሪያው ደግሞ በአካባቢው ተከሰቶ የነበረውን ግጭት ምክኒያት በማድረግ በግብርና ምርቶችና በሸቀጥ ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል ይላሉ፡፡

የጤፍ ዋጋ በኪሎ 65 ብር ይሸጥ የነበረው አሁን ወደ 110 ብር አሻቅቧል፡፡

” በእያንዳንዱ የሸቀጥ ምርቶችም ላይም በተመሳሳይ የሽያጭ ዋጋቸው እየጨመረ ነው፡፡ ነጋዴዎች ያላግባብ ምርት ያከማቻሉ፡፡ ያላግባብ ዋጋ ይጨምራሉ፡፡ ነዋሪዎች ግጭት ይነሳል በሚል ስጋት እህል እየገዙ ያከማቻሉ፡፡ ይህ ሁሉ ተደማምሮ የዕለት ከዕለት ኑሮን መግፋት አስቸጋሪ ሆኖብኛል ” ሲሉ አስተያየት ሰጭው ይናገራሉ፡፡

እየተደረገ ያለው የተጋነነ የዋጋ ጭማሪ ተገቢ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ ከሰሞኑን በነበረ አንድ መድረክ ላይ ፤ ” በከተማዋ በኢንዱስትሪና በግብርና ምርቶች ላይ ያላግባብ የዋጋ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ ይህ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን ነዋሪዎችና የመንግሰት ሰራተኞችን አስመርሯል፡፡ በቀጣይ ችግሩን ለመፍታት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት በትኩረት ይሰራል ” ብለዋል፡፡

” የከተማ አስተዳደሩ ለዳሽን የሸማቾች ህብረት ስራ ዩኔን 20 ሚሊየን ብር ያለ ወለድ ብድር ሰጥቶ በመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት አማካኝነት የግብርና ምርቶችን የማሰራጨት ስራ እየተሰራ ነው ” ያሉት ከንቲባው በቀጣይ ለመሰረታዊ የሸማቾች ህብረት ሰራ ማህበራት የሚደረገው ያለ ወለድ የገንዘብ ብድር ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ፤ የማህበራትን አቅም የማሳደግ ስራም በትኩረት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ያለ አግባብ ምርት በሚያከማቹ ግለሰቦች ላይም ክትትልና ቁጥጥር ይደረጋል ብለዋል፡፡     

መረጃውን የጎንደር የቲክቫህ-ኢትዮጵያ የቤተሰብ አባል ነው የላከው።

Leave a Reply