ሰሞኑን በውጭ ያሚኖሩና በአማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን የትጥቅ ትግል እንደሚመሩና እንደሚያግዙ የሚናገሩ ወገኖች ” ትግሉ ወደ አዲስ አበባ መዛመቱን፣ አዲስ አበባ ላይ ትኩረት መደረግ አለበት” በሚል በተደጋጋሚ ጥሪና መልዕክት ሲያስተላልፉ ስንበተው ነበር።
እስክንድር ነጋ በግልጽ “ተነሱ” የሚል ጥሪ ሲያሰማ፣ “በቃህ” ተብለው የነበሩት ሻለቃ ዳዊትም ከቀናት በፊት ከመሳይ መኮንን ጋር “ትግሉ ወደ አዲስ አበባ ዞሯል። ካሁን በሁዋላ የሚነገርና የማይነገር ነገር አለ” በማለት አስታውቀው ነበር።
ይህን ተከትሎ ነበር አዲስ አበባ ላይ የታጠቁ የሚታወቁ የፋኖ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱ ዜናው ይፋ የሆነው። ይህንኑ ዜና ተከትሎ የሟችን ምስል በመለጠፍ ደጋፊዎች ” ጀግናች” በሚል ሲያወድሱ፣ መሳይ መኮንን ” ፊሽካው ተነፋ” በሚል እጅ አንሰጥም በሚል ተታኩሰው የሚቱትን አሞካሽቷል። የተለያዩ አሳቦችም ተሰንዝረዋል። “መገዳደሉ ይብቃ” የሚሉ ድምጾችም እየተሰሙ ነው።
ከጸጥታ አካል የተላለፈው መግለጫ ከስር እንዳለ ቀርቧል።
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በፅንፈኛው ቡድኑ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በአዲስ አበባ በህቡዕ በተደራጀው ፅንፈኛ ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በላከው መግለጫ ናሁሰናይ አንዳርጌ ታረቀኝ የተባለው የፅንፈኛው ቡድን አመራር እና አቤነዘር ጋሻው አባተ የተባለ የቡድኑ አባል ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ ሕጋዊ እርምጃ የተወሰደባቸው ሲሆን ሀብታሙ አንዳርጌ ተሰማ የተባለው የቡድኑ አባል ደግሞ በቁጥጥር ሥር ውሎ ምርመራ እየተጣራበት መሆኑን ገልጿል፡፡
በአዲስ አበባና አካባቢዋ ተወጥኖ ለከሸፈው ህቡዕ የጥፋት ተልዕኮ ዋነኛ ጠንሳሽ የሆነው ናሁሰናይ አንዳርጌ የተባለው ግለሰብ የጽንፈኛ ቡድኑ መሪ እንደነበር የጋራ ግብረ-ኃይሉ በመግለጫ አረጋግጧል።
ናሁሰናይ አንዳርጌ የጽንፈኛ ቡድኑ እኩይ ዓላማ እንዲሳካ የሽብር ጥቃት እንዲፈጽሙ የመለመላቸው ወጣቶች ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ የፋይናንስና የሎጅስቲክስ ድጋፎችን ከሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ ደጋፊዎቻቸው በማሰባሰብ ሁኔታዎችንም እንዳመቻቸ መግለጫው አትቷል፡፡
የፅንፈኛ ቡድን አባላት የተለያዩ የሽብር ጥቃት ለማድረስ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ህቡዕ እንቅስቃሴ ቢያደርጉም ከፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል እይታ ውጭ አልነበሩም ብሏል መግለጫው።
የሸብር ቡድኑ አባላት በዛሬው ዕለት በሰሌዳ ቁጥር ኮድ 2C 14373 አ/አ መኪናን በመጠቀም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 ልዩ ቦታው ሚሊኒዬም አዳራሽ አካባቢ የሽብር ተግባራቸውን ለመፈፀም በመንቀሳቀስ ላይ እያሉ በፀጥታ ኃይሉ በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ቢጠየቁም ፍቃደኛ ከመሆን ይልቅ በፀጥታ አካላት ላይ ቶክስ በመክፈት በሁለት የፖሊስ አባላት ላይ ከባድ የአካል ጉዳት አደርሰዋል ብሏል መግለጫው።
በተጨማሪም አቶ እንዳሻው ጌትነት የተባሉ ግለሰብ የሽብር ቡድኑ አባላት በመኪናቸው እንዲጭኗቸው ቢያስገድዷቸውም አልተባበር በማለታቸው በፅንፈኛ ቡድኑ አባላት ተገድለዋል፡፡
ጽንፈኛ ቡድኑ በአማራ ክልል እያደረሰ ያለው ጥቃት እንደማያዋጣው በመረዳቱ ራሱን ወደ ሽብርተኝነት ቀይሮ በአዲስ አበባ እና አከባቢዋ የመጨረሻ መፍጨርጨር እያደረገ እንደሚገኝ የገለፀው የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ-ኃይል መግለጫ የከተማዋን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ሰላም ወዳዱ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመሆን እስከአሁን ድረስ እያደረገ ላለው ትብብር ላቅ ያለ ምስጋና እያቀረበ ሆቴሎች፣ ገስት ሀውሶች፣ የቤት እና የመኪና አከራዮች እንዲሁም የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል።
ኅብረተሰቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት የተለመደ ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይሉ ጥሪውን ያቀርባል።
ሚያዚያ 4 ቀን 2016 ዓ.ም
የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል
አዲስ አበባ፣