ንጹሃን ምን በደሉ? የንጹሃን ደም ይጮሃል- “ኢንተርኔትና የግንኙነት መስመር ይዘጋ”

በኢትዮጵያ ነጹሃንን መግደል፣ ማፈን፣ ማሰቃየት፣ ማፈናቀልና ንብረታቸውን መዝረፍ የተለመደና እንደ ጽድቅ በማህበራዊ ሚዲያ በኩራት የሚሰራጭ ገድል ነው። ባለፉት 27 ዓመታት ሲዘራ የነበረው የዘርና የጥላቻ ፍሬ ውጤት የሆነው ጥቃት በተለይ አማራው ላይ ለምን እንዳነጣጠረና ምን ምክንያት እንደሚቀርብለት ግራ ያጋባል። ማንም ይሁን ማን ንጹሃንን ዘርና አካባቢ መርጦ መጨፍጨፍ እጅግ የሚወገዝ ተግባር ነው። ይህን ተግባር የማያወግዙ ሁሉ የድርጊቱ ተባባሪና ተሳታፊ መሆናቸውን ከማሳየት የዘለለ ምንም ዓይነት ምክንያት ሊያቀርቡ አይችሉም።

በኦሮሚያ ክልል በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ የአማራ ብሔር ተወላጆች የሁኑ በሚኖሩባቸው መንደሮች ጥቃት ተፈጽሟል። በጥቃቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ ራሳቸውን ለማትረፍ ሸሽተው ቤትና ቀዬ አልባ ሆነዋል።

አብዛኞቹ የአማራ ብሔር ተወላጆች መሆናቸውንና ከ200 በላይ የሚሆኑ መገደላቸውን እማኞች አመልክተዋል። የኦሮሚያ ክልል መንግስት ቁጥርና ዝርዝር መረጃ ባያቀርብም በመግለጫው ድርጊቱን በአሸባሪነት የተፈረጀው ታጣቂ ቡድኑ የፈጸመው መሆኑንን አመልክቷል። በጥቃት በንጹሃን ሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት እንደደረሰ አስታውቋል። ድርጊቱን “በንጹሃን ላይ የተፈጸመ ጭካኔ የተሞላበት ” ሲል ገልጾታል። በስም ጠቅሶ ኦነግ ሸኔ ይህንን ወንጀል መፈጸሙን ሲገልጽ እንደምክንያት ያቀረበው “በፌደራልና በክልሉ የፀጥታ ኃይሎች እየተወሰደበት ያለው እርምጃ መሆኑን ገልጾ፣ “ይህንን እርምጃ መቋቋም ሲያቅተው በንጹሃን ላይ ጭካኔ የተሞላበት ጥቃት ፈጽሟል” ነው ያለው።

ራሱን የኦነግ ሰራዊት የሚለው ሃይል ጥቃቱን የፈጸመው የመንግስት ሃይል መሆኑንን እንዳስታወቀ ቢቢሲ አስታውቋል። ቢቢሲ ድርጅቱን ጠቅሶ ለጥፋቱ መንግስት ተጠያቂ እንደሆነ ባመለከተበት ዘገባው ከጥቃት የተረፉትንም አነጋግሯል። የአይን እማኞቹ ለሮይተርስና ለቢቢሲ እንደመሰከሩት በጅምላ ጭፍጨፋ የፈጸሙት የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች ናቸው።

”መንግስት የጀመረው የህግ የበላይነትን የማስፈን ስራ በሽብር ቡድኖች ሴራ በፍጹም አይደናቀፍም!”ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ “መንግስት በመላ ሃገሪቱ ሰላምን ለማስፈን የኢ-መደበኛ ታጣቂዎችንና በሽብርተኛነት የተፈረጁ ቡድኖችን እንቅስቃሴ ለመግታት ሁሉን አቀፍ ጥረት እያደረገ ይገኛል” ብሏል። አያይዞም “ይህ የመንግስትና የመላው ጸጥታ ሃይላችን የህግ የበላይነትን የማስከበር ተልእኮ ያነጣጠረበት የሸኔ የሽብር ቡድን እየደረሰበት የሚገኘውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፈን የጥፋት በትሩን ወደ ንጹሃን አዙሯል” ሲል ምንም በማያውቁና መሳሪያ ባልያዙ ዜጎች ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን አውግዟል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በኦሮሚያ ክልል በንጹሀን ላይ የተፈጸመውን ግድያ “አሸባሪው ሸኔ በንጹሐን ወገኖች ላይ በፈጸመውን ግድያ የተሰማኝን ሀዘን እየገለጽኩ፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን እመኛለሁ” ሲሉ ድርጊቱን አውግዘዋል።

“የሽብር ቡድኑ በቅርቡ በጋምቤላ፣ በደምቢዶሎና በጊምቢ ከተሞች ላይ የሰነዘራቸው የሽብር ጥቃቶች በጸጥታ ሃይሉ ቅንጅት ሲከሽፍ በበቀል የሽብር ተግባሩ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ንጹሃንን ህይወት በግፍ ቀጥፏል፣ ንብረትንም አውድሟል” በማለት “ይህ ቡድን በንጹሃን ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የቡድኑን ትክክለኛ ማንነት የሚያሳይ በመሆኑ የጥፋት ሃይሉ ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ በመላው የክልልና የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች የተጀመረው የተቀናጀ ተልእኮ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲል ኦፕሬሽኑ እንደማይላላ አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው በንጹሃን ዜጎች ላይ በህገወጥና በኢመደበኛ ኃይሎች የሚደርስ ጥቃት እንደሌለው አመልክተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በማህበራዊ ትስስር ገፆቻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቤኒንሻንጉል ጉሙዝና ኦሮሚያ ክልሎች፥ ዋና ዓላማቸው ኅብረተሰቡን ማሸበር በሆነ አካላት የተፈጸመው የሰው ልጆችን ህይወት የሚቀጥፍ ዘግናኝ ድርጊትን መንግስት እንደማይታገስ አስታውቀዋል። ጥቃት በደረሰባቸው አካባቢዎች ሰላም እና ደህንነትን መመለስ አሁንም ቅድሚያ የሚሰጠው ተግብር መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።

ይህን ተከትሎ በተወሰደ እርምጃ ከመቶ ሃያ በላይ ታጣቂዎች መደምሰሳቸውና የልዩ ሃይል ኮማንዶ አካባቢዉን በመክበብና ቅኝቱን በማስፋት የማጥራት ዘመቻውን አጠንክሮ እየሰራበት እንደሆነ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አመልክተዋል። ቆስለው የተማረኩ መኖራቸውምንም ገልጸዋል።

በስፍራው የነበሩና የተረፉ የዐይን እማኞችና መንግሥት ጥቃቱን የፈጸመው ሸኔ በመባል የሚታወቀው ታጣቂው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት እንደሆነ ሲገልጹ፣ ቡድኑ ግን ለጥቃቱ የመንግሥት ኃይሎችን ተጠያቂ ማድርጉን ቢቢሲ አስታውቋል።

እንደ ቢቢሲ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ጥቃቱን በማስመልከት ሰኞ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ “ታጣቂዎቹ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽሙና የጊምቢው ጥቃትም መንግሥት አደራጅቶታል ባለው ኢ-መደበኛ ኃይል የተፈጸመ ነው ብሏል። ጨምሮም ይህ ክስተት በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ጠይቋል” ሲል አስታውቋል።

ቢቢሲ የኦሮሞ ነጻናት ግንባር ተዋጊዎች መግለጫ ጠቅሶ ይህንን ቢልም በተመሳሳይ “የዓይን ዕማኞች ነገሩኝ” ሲል እንዳመለከተው ጭፍጨፋውን የፈጸመው ኦነግ ነው።

አንድ ቢቢሲ ያናገራቸው እማኝ “ጥቃቱ የጀመረው 3፡20 አካባቢ ነበር። እስከ 7፡00 [ታጣቂዎቹ] አልወጡም። ልዩ ኃይልና መከላከያ የገባልን 11፡00 ላይ ነው። እስከዚያ ድረስ ማንም ሊረዳን አልመጣም። የሚመለከተው አካልም አልረዳንም” ብለዋል።

በቶሌ ቀበሌ፣ ስልሳው የተባለው መንደር ውስጥ ተወልዶ ያደገው አርሶ አደር ከማልደግሞ እሱ በሚኖርበት አካባቢ “እስካሁን 250 ሰው ቀብረናል” ብሏል። “ትላንት [እሁድ] ስንቀብር ዋልን። አሁን ደግሞ ሌሎችን ሊቀብሩ ሄደዋል” ያለው ከማል ገና አስከሬናቸው የሚነሳ ነዋሪዎች እንዳሉም ተናግሯል። ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች ኦነግ-ሸኔ እንደሆኑና “ብሔር ለይተው፣ አማሮችን እንደጨፈጨፉ” አክሏል ይላል ቢቢሲ።

በጋምቤላ በዚህ ሳምንት ከተፈፀመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ንፁሃን ዜጎች ላይ ከማዋከብ አንስቶ እስከ ግድያ የደረሰ ከዚህም በተጨማሪ የዝርፊያ ድርጊት መፈፀሙ መጠቆሙ ይታወሳል።

ጭፍጨፋው የከፋ ነው። ተቸፍቻፊዎቹ የአማራ ተወላጆች ናቸው። ድርጊቱ አሁን ላይ በአማራና በኦሮሚያ ድርጅቶች መካከል ያለውን መላክም ግንኙነት ለማደፍረስና የውስጥ ልዩነቱን ለማጋም ታቅዶ የተፈጸመ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። “ጭፍጨፋውን ከፈጸሙት ውስጥ ኦሮሚኛ የሚናገሩ የሌላ አንድ ብሄር ተወላጅ ታጣቂዎች አሉበት” ሲሉ እማኝነታቸውን የሚሰጡ አሉ። የአንድ ብሄረሰብ አባል ያሉዋቸውንና በስም የጠቀሷቸውን ክፍሎች ለጊዜው ከመጥቀስ ተቆጥበናል።

ጉዳዩን ጠጋ ብለው የሚያዩ በአካባቢው ያለውን የግንኙነት መስመርና ኢንተርኔት በማቋረጥ መንግስት ዘመቻውን ማስፋት እንዳለበት የሚጠቁሙ፣ ይህ ከሆነ ታጣቂዎቹ የግንኙነት መስመራቸውና የሎጂስቲክ ቅብብላቸው እንደሚበላሽ፣ ከዛም በላይ ተናበው ለመንቀሳቀስ ስለሚቸግራቸው ሃይላቸውን ለማሰባሰብ አዳጋች ሁኔታ ይፈጥርባቸዋል ብለዋል። የግንኙነት መስመሮች መቋረጥ ህዝቡን የሚጎዳ ቢሆንም ከንጹሃን ሞት አይብስምና የግድ ተግባራዊ ሊሆን ይገባል።

Leave a Reply