“አእምሮዬ አልዳነም!”

“በማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ ቶርቸር (አካላዊ ስቃይ) የሚፈጸምባቸው ጩኸታቸው ይሰማኛል፡፡ የቃሊቲ ማጎሪያ ውስጥ የታሰሩ ተማሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ፖለቲከኞች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ ንጹሃን ዜጎች፣ ስቃይ አሁንም ከፊቴ አለ፤ የሚሞቱት ሰዎች ሊረሱኝ አይችሉም፤ የእስር ቤቱ ጠረንና ሽታ ይከተለኛል፤ በአካል ደህና ብመስልም አእምሮዬ ግን አሁን ድረስ ሰላም የለውም” በማለት የስዊድን ጋዜጠኛ ማርቲን ሺብዬ በተለይ ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ተናገረ፡፡

ዮሐን ፔርሶን ኦጋዴን በረሃ
ዮሐን ፔርሶን ኦጋዴን በረሃ

አንድ ዓመት ከሁለት ወር (14 ወራት) ከሥራ ባልደረባው ዮሐን ፔርሶን ጋር ኢህአዴግ አስሮት የነበረው ጋዜጠኛ ሺብዬ ለጎልጉል የአውሮጳ ዘጋቢ ይህንን የተናገረው በዖጋዴን ክልል የተፈጸመውን ጭፍጨፋ የሚያጋልጥ ዘጋቢ ፊልም መሰራጨቱን ተከትሎ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ በሰጠበት ወቅት ነው፡፡

“በአካል ሰላም አለኝ፤ አእምሮዬ ግን አልዳነም፤ ሁሌም እረበሻለሁ፤ በዓይኔ ያየኋቸው፣ በጆሮዬ የሰማኋቸውና በበቂ ምስክሮች ያረጋገጥኳቸው ሁኔታዎች ዕረፍት ይነሱኛል” ሲል አስተያየቱን የጀመረው ሺብዬ በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግፍ ከሙያው አስገዳጅነት በመነሣት ከተባባሪዎቹ ጋር በመሆን ለዓለም እንደሚያሳውቅ ግልጽ አድርጓል፡፡

ከጥቂት ሳምንታት በፊት “ከፌዴራል ፖሊስ ምርመራ ተገኘ” በሚል ዘወትር እሁድ በሚተላለፈው የፖሊስ ክፍለ ጊዜ የተላለፈውን ዘጋቢ ፊልም (ድርሰት) የኢህአዴግን ዓመታዊ ቋት የምትሞላውን አሜሪካ በእስረኞች አያያዝ የገሃነም ተምሳሌት አድርጎ ያቀረበ ነው፡፡ ኢህአዴግ በልማት ስም የሚያገኘውንና ለባለሥልጣኖቹ የግል ሃብት ማካበቻ እንዲሁም በየጎሬው ለተፈጠሩ እስር ቤቶች ግንባታ የሚደጉሙትን አገራት በሰብዓዊ መብት አያያዝ ከዜሮ በታች አድርጎ ያብጠለጠለ ነበር፡፡ ከተለያዩ ድረገጾችና የዩትዩብ ምስሎች በተለያዩ እስርቤት ያሉትን በማነጋገር ተገጣጥሞ የቀረበው “ድርሰት” (ዘጋቢ ፊልም) ተከትሎ ይሁን አይሁን በግልጽ ባይታወቅም የኢህአዴግ የልብ ወዳጅ ኖርዌይ እነ ሺብዬ ያዘጋጁትን ዘጋቢ ፊልም ይፋ አድርጋለች፡፡

Nrk2 በተሰኘው የኖርዌይ መንግሥታዊ ቴሌቪዥን ማስተባበል በማይቻልበት ደረጃ በዖጋዴን የተፈጸመውን ርኅራኄ የሌለውን ዘግናኝ ሰቆቃ ለመመልከት ተችሏል፡፡ (በተለይ በአውሮጳ የሚኖሩ ቪዲዮውን እዚህ ላይ መመልከት ይችላሉ)

አብዱላሂ ሁሴን
አብዱላሂ ሁሴን

የቀድሞ የክልሉ ፕሬዚዳንት አማካሪና የሚዲያ ክፍል ኃላፊ የነበረው አቶ አብዱላሂ ሁሴን ከሱማሌ ክልል ይዞት ወደ አውሮጳ ባመጣው በራሱ በኢህአዴግ ባለሙያዎች የተቀዱ ማስረጃዎች፣ ሰለባዎችና የክልሉ (ምክትል) ፕሬዚዳንት በግልጽ ሰቆቃና ግፍን ሲያውጁ በሚሰማበት፤ ወታደሮች ሲገድሉ፤ በቢሮ ግምገማ ላይ ተቀምጠው ስለፈጸሙት የግፍ ጀብዱ ሲተርኩና የፈጸሙት ግፍ አልቃም ተብሎ ሲገመገሙ እንደወረደ በሚያሳየው በዚህ ዘጋቢ ፊልም የእነ ሺብዬ መከራ በውል ቀርቧል፡፡ (ቪዲዮውን እዚህ ላይ መመልከት ይቻላል) በተለይም ፎቶ አንሺው ዮሐን ፔርሶን የክንዱ አጥንት በጥይት ተሰብሮ፣ ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ ቀብረው ስቃዩን ሲያዳምጡ የሚያሳየው ምስል እጅግ የሚዘገንን ነው፡፡ ኢህአዴግ በእስረኞች አያያዝ “ጻድቀ ጻድቃን” ነኝ ባለ 24 ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የኖርዌይ ቴሌቪዥን ያሰራጨው ዘጋቢ ፊልም የኢህአዴግን አውሬነት ያሳየ ለመሆኑ አብዛኞች አስተያየት እየሰጡ ነው፡፡

የኢህአዴግ የልብ ወዳጅና የልማት አጋር ኖርዌይ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ጉዳዮችን ሊነካካ በሚችል ጉዳይ ጣልቃ ስትገባ ይህ በመጀመሪነት የሚጠቀስ ነው፡፡ እንግዲህ ይህንን ተከትሎ ነበር ጋዜጠኛ ሺብዬ አስተያየት የሰጠው፡፡ እርሱ እንደሚለው ሙያዊ ኃላፊነቱ በዚህ በዖጋዴን የሚፈጸመውን ጭፍጨፋ እንዲጋልጥ አነሳስቶታል፡፡ ለወትሮው ወደ ዖጋዴን አንድም ሚዲያ እና የሲቪክ ተቋማት ድርሽ እንዳይሉ በሩን ጠርቅሞ የዘጋው ኢህአዴግ ባላሰበውና ባልጠበቀው መንገድ እነ ጋዜጠኛ ሺብዬ ይህንኑ ለመዘገብ ክልሉን ዘልቀው ሊገቡ ችለው ነበር፡፡

“ያየነውን ለዓለም ማሳየት፣ የኢህአዴግን ፕሮፓጋንዳ ማጋለጥ ዓላማችን ነው” የሚለው ሺብዬ በፖሊስ ፕሮግራም ቀረበ ስለተባለው የኢህአዴግ “ድርሰት” የሰጠው ምላሽ (ኢህአዴግ ይህንን ያህል ከሚለፋ) ማዕከላዊን እና ቃሊቲን ለጋዜጠኞች፣ ለቀይ መስቀልና ለዓለምአቀፍ ተቋማት ክፍት በማድረግ ምስክር ማግኘት ብቻ ይበቃዋል ሲል ፕሮፓጋንዳውን አጣጥሎታል፡፡ በቃሊቲ እስረኞች እንደሚሞቱ፣ በቂ የሚባል መጸዳጃ እንኳን እንደሌለ የተናገረው ሺብዬ አሁን ያለሁበት ቦታ የፈለኩትን ማድረግ የምችልበት ቢሆንም እዚያ ያሉትን ንጹሃን መዘንጋት ግን አይቻለኝም፤ ዘወትር እረበሻለሁ” በማለት ተናግሯል፡፡ በማያያዝም ይህንኑ ኢህአዴግን የሚያጋልጥ በእንግሊዝኛ የተጻፈ መጽሐፍ በሚቀጥለው ወር ለገበያ እንደሚበቃ አስታውቋል፡፡ በመጨረሻም በኢትዮጵያ ውስጥ በእስር ለሚማቅቁ ወገኖች መልካም ቀን እንዲመጣ ምኞቱን ገልጾዋል፡፡

ማርቲን ሺብዬ እና ዮሐን ፔርሶን በኦጋዴን በረሃ
ማርቲን ሺብዬ እና ዮሐን ፔርሶን በኦጋዴን በረሃ

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዘጋቢ ፊልሙ ይፋ በሆነ ማግስት ዓለምአቀፉ የጦር ወንጀለኞች መርማሪ ኮሚሽን በክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አብዱላሂ ወሬራ እና በመመሪያ ሰጪዎቹ የህወሃት/ኢህአዴግ ባለሥልጣናት በጦር ወንጀለኝነት ለመክሰስ ምርመራ ማካሄድ መጀመሩ ታውቋል፡፡

ሁለቱ የስዊድን ጋዜጠኞች በእስር በነበሩበት ወቅት አቶ መለስ “የጥቁርም የነጭም ደም ቀይ ነው” በማለት ለፈጠሩት ፓርላማ ሲፈላሰፉና በህግ የበላይነት እንደሚያምኑ እያስጨበጨቡ ሲናገሩ ቢቆዩም የልመና ኮሮጃቸውን የሚሞሉት የምዕራባውያን ዜጎችን አስረው መቀጠል እንደማይችሉ ሲረዱ “በዕርቅ” መፍታታቸው መዘገቡ አይዘነጋም፡፡

በሌላ በኩል ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ዖጋዴን ዙሪያው ገባ ታጥሮ ሰሚና ተመልካች እንዳይኖር ተደርጎ የከፋ ወንጀል ሲካሄድ እንደነበር የስዊድን ጋዜጠኞች ዜና ሳይሰማ ያገባናል ለሚሉ ወገኖች ሁሉ የማሳሰቢያ ዜና መስራቱ ይታወሳል፡፡ በተለይም የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ በቀጥታ ድርጊቱን በማውገዝ መግለጫ ማውጣቱ አይዘነጋም፡፡ ከመግለጫው የተወሰደው ቃል እንዲህ ይነበባል፡-

“… ለወራት ያህል በመለስ ታማኞች ትዕዛዝ ሰጪነት የተከበቡት ኦጋዴኖች በረሃብ ተጠበሱ። ችግሩ ሲጠናባቸው ሽማግሌ በመላክ “በረሃብ ማለቃችን ነው። እኛ ንፁሃን ዜጎች ነን። ህፃናት እየተጎዱ፣ ከብቶቻችን እያለቁ ነው’’ በማለት ከከበባው ለመውጣት ጥያቄ ቢያቀርቡም ትእዛዝ ከተላለፈላቸው የጦር አዛዦች ያገኙት መልስ ጥይት ነበር። በተፈጥሯቸው አንድ ቀበሌ መኖር የማይችሉ ዘላኖች (አርብቶ አደሮች) ከቦታ ቦታ መዘዋወር ተከልክለው ለአራትና አምስት ዓመታት እንዴት ኖሩ? ምን ያህልስ ሰብዓዊ ቀውስ ደረሰ? ከአመታት የስቃይ ኑሮ በኋላ የመጨረሻው የፍርድ ቀን ደርሶ በኦጋዴን የጅምላ ጭፍጨፋ ተካሄደ። ንፁሃን ጉድጓድ ተምሶ በጅምላ እንዲቀበሩ ተደረገ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ መለስ ስለ ኦጋዴን ሲነሳ ያማቸው ጀመር። ከዋናው የኦጋዴን ነፃ አውጪ ግንባር ጋር የሰላም ስምምነት አድርጌያለሁ ቢሉም አካባቢውን ገለልተኛ ወገኖች ገብተው እንዲመለከቱት ፈቅደው አያውቁም። ሰሞኑን  የስዊድን ጋዜጠኞች  ላይ የተወሰደው ርምጃም የዚሁ ‹ምስጢር ይወጣብኛል› ፍርሃቻ አካል ስለመሆኑ ጥርጥር የለንም … ”

“… ኦጋዴን በሚኖሩ ዜጎቻችን ላይ የተፈጸመው ጭፍጨፋ ተድበስብሶ ቢከርምም ዛሬ በሶማሊያ የተከሰተውን አስፈሪ ርሃብ ተከትሎ ይፋ መሆን ጀምሯል። ድርጅታችን በጋምቤላ፣ በደቡብ፣ ክልል፣ በአዲስ አበባና በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች የተፈፀሙትን ጭፍጨፋዎች በመቃወም እንዳደረገው ሁሉ በኦጋዴን የተፈፀመው ጭፍጨፋ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ አስፈላጊውን ሁሉ እያደረገ ነው። የኦጋዴን ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ በመሆኑ ይህ መግለጫ የሚደርሳችሁ አካላት በሙሉ ድርጊቱን በመቃወም አግባብ ያለው ተፅዕኖ በማድረግ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ መድረክ ትግላችሁን እንድትቀጥሉ አጥብቀን እናሳስባለን” ሲል ጥሪውን አስተላልፎ ነበር። (የመግለጫው ሙሉ ቃል እዚህ ላይ ይገኛል)

በዖጋዴን የደረሰውን በተመለከተ እንዲሁም የሁለቱን ጋዜጠኞች በተመለከተ እስካሁን የዘገብናቸውን ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፡፡

ኢትዮጵያ፡ በፖለቲካ እስረኞች ላይ የማሰቃየት ድርጊት ይፈጸማል፤ ፖሊስ በጋዜጠኞች እና በተቃዋሚዎች ላይ በደሎችን ይፈጽማል።

በሚዲያ መረሳት ያስፈራል፤ “ነጻ ፕሬስ ከሌለ አገር አደጋ ላይ ነው”

“የጥቁርም የነጭም ደም ቀይ ነው” የመለስ ድራማ!! ኢህአዴግ ለመክሰስ ሲፈልግ ፊልም እንደሚደርስ ተረጋገጠ

Leave a Reply