“የትግራይ ክልልን መልሶ በማደራጀት ሂደት ውስጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር ያስፈልጋል”-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

የትግራይን ክልልን መልሶ በማደራጀት ሂደት ውስጥ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ትብብር እንደሚያስፈልግ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡ ፕሬዚዳንቷ ዛሬ በትግራይ ክልል መቐለ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎችን ጎብኝተዋል፡፡ በጉብኝታቸውም በመቐለ ከተማ የሚገኙትን የዓይደር ስፔሻላይዥድ ሆስፒታል፣ የፌደራል መንግስት እህል ማከማቻ ማዕከላዊ መጋዘን እና በትግራይ ክልል በተካሄደው የህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው በከተማዋ የሚገኙ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል፡፡

ፕሬዘዳንት ሳህለወርቅ ከመቐለ ከተማ አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች ጋርም ውይይት አካሂደዋል፡፡ በውይይቱም የአገር ሽማግሌዎች በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል የተንሰራፋው የሥራ አጥነት ችግር እንዲፈታ፣ ከመንግስት ቢሮዎች የተዘረፉ ቁሳቁሶች ተሟልተው በተጠናከረ መልኩ ስራ እንዲጀምሩ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

በትግራይ በአሁኑ ወቅት በዋናነት ለሰላም እና ለጤና ቅድሚያ ተሰጥቶ መሰራት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡ በተጨማሪም መንግስት እያቀረበ ያለውን የሰብዓዊ ድጋፍ አቅርቦት አጠናክሮ እንዲቀጥል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በሰጡት ምላሽም ትግራይን ወደቀደመው ሰላም ለመመለስ መንግስት በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል፡፡

የትግራይ ክልልን መልሶ በማደራጀት ሂደት ውስጥ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከመንግስት ጎን በመሆን ሊደግፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ በትግራይ ክልል መንግስት ህዝብ አብሮ የሚኖርበትንና የሚደጋገፍበትን ስርዓት በመገንባት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ያሉ የሕዝብ ጥቄዎች በአፋጣኝ እንዲፈቱ እየተሰራ መሆኑንም ፕሬዝዳንቷ ጠቁመዋል፡፡ በተጨማሪም ትግራይን መልሶ ለማደራጀት ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ያስረልጋል ብለዋል።

ፕሬዚዳንቷ በመቐለ ከተማ ያደረጉትን ጉብኝት በማጠናቀቅ ወደ አዲስ አበባ መመለሳቸውን ኢዜአ ዘግቧል። በትናትናው ዕለት የሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል እና የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዳይሬክተር በትግራይ ክልል እየተሰጠ የሚገኘውን የሰብዓዊ ድጋፍ ለመመልከት በመቀሌ ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

See also  ተ.መ.ድና ኢሰመኮ፤ በትግራይ ክልል በጋራ ሲያከናውኑት የነበረው ምርመራ ተጠናቀቀ

Leave a Reply