የሚኒስትሮች ምክር ቤት “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ ባቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ምክር ቤቱ በዛሬው መደበኛ ስብሰባው ከተወያየ በኋላ ውሳኔውን አሳልፏል።

ሁለቱ ቡድኖች በአገር እና በህዝብ ላይ የሽብር ተግባራትን በመፈፀም ላይ በመሆናቸው በሽብርተኝነት መፈረጃቸው አግባብ መሆኑን በመጠቅስ ነበር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳቡን እንዲያፀድቀው አቅርቦ የነበረው።

የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣው ዐዋጅ ቁጥር 1176/2012 አንቀጽ 18 እና 19 መሠረት “ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት)” እና “ሸኔ” የሽብር ወንጀልን ዓላማቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱ በመሆኑና የድርጅቶቹ የሥራ አመራር ወይም ወሳኔ ሰጭ አካላት ወንጀሉን አምነው የተቀበሉት ወይም አፈጻጸሙን እየመሩት በመሆኑ፤ የሽብር ተግባር መፈጸምም የድርጅቶቹ ጠቅላላ መገለጫ በመሆኑ፤ ድርጅቶቹ በሽብርተኛ ድርጅትነት እንዲሰየሙም ሲል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የውሳኔ ሐሳቡን ማቅረቡ ይታወሳል።

በመሆኑም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ውሎው “ህወሓት” እና “ሸኔ” በሽብርተኝነት እንዲፈረጁ በቀረበለት የውሳኔ ሀሳብ ከተወያየ በኋላ በሙሉ ድምፅ ውሳኔውን አሳልፏል።

EBC

Leave a Reply