December 3, 2021

የቡድን 7 ጉባኤ፣ ዉጤቱና ዳራዉ

ቋሚ ፅሕፈት ቤት፣ሥራ አስኪያጅ ወይም ፀሐፊ የሌለዉ ያ የሐብታሞቹ ስብስብ፣ ብዙዎች እንደሚተቹት ከምጣኔ ሐብቱ ይልቅ ፖለቲካ የሚጫጫነዉ ከፍትሐዊነት ይልቅ የቱጃሮች ፍላጎት ማስጠበቂያ ከሆነ ዓመታት አስቆጠረ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በቀደም እንዳሉት ግን ስብስቡ ለዴሞክራሲ የቆመ፣ ለፍትሕ የሚታገል፣ አምባገነኖችን የሚቃረን ነዉ።

የጀርመኑ ዕዉቅ መፅሔት የዴር ሽፒግል የዛሬ የአምደ መረብ እትም የሽፋን ፎቶ ሁሉንም ይለዋል።በደማቅ ቀይ መደብ ላይ አንድ ትልቅ፣ሶስት ትናንሽ ቢጫ ከዋክብት ያሉበት የሕዝባዊት ቻይና ሪፐብሊክ ባንዲራ መሬት ላይ ተነጥፏል። ጂንስ ሱሪ ያጠለቀ፣ስኔከር የተጫማ አንድ ሰዉ ባንዲራዉን በአንድ እግሩ ረግጦታል።«ቻይና ቡድን ሰባትን ጠብ ጫሪና ከፋፋይ በማለት አጣጣለች» ይላል የመጣጥፉ ርዕስ።ካለፈዉ አርብ እስከ ትናንት ኮርን ዎል-ብሪታንያ የተደረገዉ የቡድን ሰባት  ጉባኤ የኮሮና ተሕዋሲን ከመዋጋት ምጣኔ ሐብትን እስከ ማሳደግ፣ ከኢትዮጵያ እስከ ምያንማር፣ከሩሲያ እስከ አዉሮጳ-ሕብረት-ብሪታንያ ያሉ ፖለቲካዊ ቀዉሶችን አንስቷል።እንደቻይና የተደጋጋመ-ጉባኤተኞችን ያለያየ ርዕስ ግን አልነበረም።የጉባኤዉ ሒደት ዉጤት መነሻ፣ የቡድን 7 ዳራ ማጣቀሻ ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።
                                        
እስራኤል እንደ ሐገረ-መንግስት ከተመሰረተች ከ1948 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) ጀምሮ ከአረቦች ጋር ባደረገቻቸዉ ጦርነቶች ሁሉ አሜሪካ መራሹ ምዕራብ ዓለም ከእስራኤል ጎን ቆሞ በየጦርነቱ ያልተሳተፈበት፣በየዉጊያዉ ሥልት፣ ድል-ሽንፈት ያልሰጋ-ያልደነገጠ ያልተደሰበት ጊዜ በርግጥ የለም።
የዮም ኩፑር ወይም የረመዳን  ተብሎ በሚጠራዉ በ1973ቱ ጦርነት ግብፅ መራሹ  የአረብ ጦር መጀመሪያ የባር ሌቭ ምሽግን ደርምሶ መግባቱና  አረቦች በነዳጅ ዘይት ሽያጭ ላይ የጣሉት ማዕቀብtnን ያክል ምዕራቦችን ያስፈራ፣ ባንድ ያሳበረ፣ ለምፍትሔ ያራወጠም አልነበረም።
አረቦች ለአዲስ ጦርነት መዶለት፣ ማዕቀብ ለመጣል ማሴራቸዉን ቀድመዉ ያወቁት የዩናይትድ ስቴትሱ የገንዘብ ሚንስትር ጆርጅ ሹልትስ የምዕራብ ጀርመን፣የፈረንሳይና የብሪታንያ አቻዎቻቸዉን  ለአጭር ጊዜ ምክክር ወደ ዋሽግተን ጠሩ።መጋቢት 23፣ 1973። የገንዘብ ሚንስትሮቹ የአረቦች የነዳጅ ዘይት ሽያጭ ማዕቀብ በምዕራባዉያን ላይ ሊያስከትል የሚችለዉን ኪሳራ የሚቋቋሙበትን ስልት የቀየሰዉን ዉይይት ያደረጉት  ዋይት ሐዉስ ቤተ-መፅሐፍ ዉስጥ በመሆኑ ጋዜጠኞች ሲሻቸዉ ቡድን አራት ሲፈልጋቸዉ ደግሞ «የቤተ-መፅሐፍቱ» ቡድን እያሉ ይጠሩት ገቡ።
የአራቱ ሐገራት የገንዘብ ሚንስትሮች በ1973 አጋማሽ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሰበሰቡ የጃፓኑን አቻቸዉን አምስተኛ ጨመሩ። ያኔ የፈረንሳይ የገንዘብ ሚንስትር የነበሩት ቫለሪ ዢስካር ዲስታንግ በ1974 የፕሬዝደንትነቱን ሥልጣን ሲይዙ በገንዘብ ጉዳይ ላይ የሚመክረዉ የገንዘብ ሚንስትሮች ስብሰባ ወደ መሪዎች ጉባኤ እንዲያድግ፤ርዕሱም ምጣኔ ጠለቅ አድርጎ እንዲነጋርበት፣ ኢጣሊያም ክለቡን እንድትቀየጥ ሐሳብ አቀረቡ።የተቃወመ የለም።አራቶቹ-ስድት ሆኑ።
ሕዳር 1975። በፕሬዝደንት ቫለሪ ዢስካር ዲስታንግ አስተናጋጅነት ራምቡዮ ለሶስት ቀን የተሰበሰቡት የስድስቱ ሐገራት መሪዎች የፈረንሳይን ምርጥ የባሕር ዉስጥ ምግብ በምርጡ ዋይን እያወራረዱ የዓለምን ምጣኔ ሐብት የጉዞ አቅጣጫ ለሶስት ቀን ገርድፈዉ ሰለቁት።ብዙም ሳይቆይ ካናዳ የምርጦቹን ክለብ ተቀላቀለች።ቡድን ሰባት ተባለም።
በ190ዎቹ ማብቂያ ሩሲያን ጨምረዉ ቡድን 7 ሲደመር አንድ ያስብሉ ጀምረዉ ነበር።አሁን ግን በሰባቱ ከፀኑ ቆዩ። የ7ቱ ሐገራት ሕዝብ ቁጥር ከዓለም ሕዝብ 10 ከመቶ እንኳን አይሞላም።ከዓለም ምጣኔ ሐብት ግን ከ60 ከመቶ የሚበልጠዉን ወይም ከ320 ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋዉን ሐብት ይቆጣጠራሉ።የዓለምን ሁለንተናዊ ሒደት ባሻቸዉ ይዘዉራሉ።ከ7ቱ ሐገራት 3ቱ ኑክሌር የታጠቁ፣ የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ቋሚ አባላትም ናቸዉ።
ሁሉም ሐገራት የምዕራቡ ዴሞክራሲ ተከታዮች፣ በሕዝብ ድምፅ በተመረጡ ፖለቲከኞች የሚመሩ ናቸዉ። 

ቋሚ ፅሕፈት ቤት፣ሥራ አስኪያጅ ወይም ፀሐፊ የሌለዉ ያ የሐብታሞቹ ስብስብ፣ ብዙዎች እንደሚተቹት ከምጣኔ ሐብቱ ይልቅ ፖለቲካ የሚጫጫነዉ ከፍትሐዊነት ይልቅ የቱጃሮች ፍላጎት ማስጠበቂያ ከሆነ ዓመታት አስቆጠረ።የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን በቀደም እንዳሉት ግን ስብስቡ ለዴሞክራሲ የቆመ፣ ለፍትሕ የሚታገል፣ አምባገነኖችን የሚቃረን ነዉ።
                           
«እንደሚመስለኝ በፍጥነት በሚቀያየረዉ በ21ኛዉ ክፍለ ዘመን፣ ከቻይና ጋር ሳይሆን፣ ከፈላጭ ቆራጮች፣ በመላዉ ዓለም ከሚገኙ ፈላጭ ቆራጭ መንግስታት ጋር እየተናነቅን ነዉ።የልጅ ልጆቻችን ከ15 ዓመታት በኋላ ወደ ኋላ ዞረዉ ሲመለከቱ »ርምጃ ወስደዉ ነበር?» ብለዉ ሲጠይቁ

England | G7 Gipfel 2021

ተገቢዉን መልስ ማግኘት አለማግኘታቸዉ የሚወሰነዉ፣እኛ ዴሞክራቶች በጋራ ቆመን ዕርምጃ ስንወስድ ነዉ።»
መሪዎቹ 1 ቢሊዮን ብልቃጥ የኮሮና ተሕዋሲ መከላከያን ክትባት ለደሐ ሐገራት ለመስጠት ተስማምተዋል።ሌላ ተመሳሳይ ወረርሺኝ ቢከሰት የሚከላከሉበትን ሥልት ለመቀየስ፣ የተፈጥሮ ሐብትን ለመጠበቅ፣የትላልቅ ኩባንያ ግብርን ለማሻሻል፣ የዓለምን የመሰረተ ልማት አዉታርን ለመጠገን፣ የልጃገረዶች ትምሕርን ለማስፋፋት ቃል ገብተዋል።
ግጭት፣ ጦርነትና የፖለቲካ ቀዉስ ያሉባቸዉን ሐገራት ወይም አካባቢዎች ከየቀዉሱ እንዲወጡ ለመርዳትም ቃል ገብተዋል።እንደ ቻይና ግን የጨከኑበት ሐገር የለም።ይሁንና በጉባኤዉ እንደ ፕሬዝደንት ለመጀመሪያ ጊዜ የተካፈሉት ጆ ባይደን ጉባኤዉ በቤጄንግ ላይ ጠንካራ አቋም እንዲይዝ ባደረጉት ግፊት ልክ ከሌሎቹ ድጋፍ አላገኙም።
በተለይ ከጉባኤተኞቹ ሁሉ ለረጅም ጊዜ በስልጣን ላይ የቆዩት የጀርመንዋ መራሒተ መንግስት አንጌላ ሜርክል ላዲሱ ግን ለትልቂቱ ሐገር መሪ፣ ትልቅ ግፊት በቀላሉ እጅ አልሰጡም።ሜርክል ባስተርጓሚ እንዳሉት ካለ ቻይና ትብብር በተለይ የዓለም የዓየር ንብረትን ማስጠበቅ አይቻልም።
                                   
«የዓየር ንብረትንና ብዙሐ ሕይወትን ለመጠበቅ ዓለም በጋራ እንዲጥር እንፈልጋለን።ቻይና ካልተሳተፈች መፍትሔ አናገኝም።»
በነገራችን ላይ የዘንድሮዉ ጉባኤ ለባይደን እንደ ፕሬዝደንት የጀመሪያዉ እንደሆነ ሆነ ሁሉ ለሜርክል እንደ መርሒተ መንግስት የመጨረሻዉ ነዉ።ከዉይይት ክርክሩ በኋላ የወጣዉ የጋራ መግለጫ በቻይና ላይ የያዘዉ አቋም ለዘብ ያለ ነዉ።መግለጫዉ በሆንግ ኮንግና በዑይጉሕሩ ሕዝብ ላይ የቻይና መንግስት ይፈፅመዋል ያለዉን ጭቆና አዉግዟል።ጉቤተኞች የገበያ ሕግን የጣሰ ያሉትን የቻይናን የንግድ ተፅዕኖ በጋራ ለመቋቋም ቃል ገብተዋልም።
የቻይናን፣ የሩሲያንና የሌሎች ሐገራት መንግሥታትን ሞቅ ቀዝ-ቀዝ ባሉ ቃላት በጋራ ያወገዙት ጉባኤተኞች እርስ በራሳቸዉ ከመነታረክ አላማምለጣቸዉ እንቆቅልሹ።በተለይ በቅርቡ ከአዉሮጳ ሕብረት አባልነት የወጣችዉ የብሪታንያና ሕብረቱን በበላይነት የሚመሩት የፍራንኮ-ጀርመን  መሪዎች የቃላት ልዉዉጥ መረር-ከረር ጠንከር ያለ ነበር።
የልዩነታቸዉ መሰረት የአዉሮጳ ሕብረትና የብሪታንያ ድንበር የሚባለዉ የሰሜን አየርላንድና የአየርላንድ ሪፐብሊክ ወሰን አጠቃቀም ነዉ።ጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን ዳርድንበራችን

England | G7 Gipfel 2021 | Joe Biden, Emmanuel Macron und Ursula von der Leyen

አይደፈርም ይላሉ።«እኔ፣ እኔ የምለዉ የብሪታንያን የግዛት አንድነት ለማስከበር አስፈላጊዉን ሁሉ እናደርጋለን ነዉ።»
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮ በጆንሰን አባባል የተናደዱ ይመስላል።ከሕብረቱ የተነጠላችሁ እናንተዉ፣ የብሪታንያን የግዛት አንድነት ማንተጋፍቶ ያዉቅና ዓይነት ይላሉ።
«ለጠቅላይ ሚንስትር ቦሪስ ጆንሰን የምነግረዉን እነግራቸዋለሁ፣ ለናንተም አሁን እነግራችኋለሁ።ፈረንይ፣ በብሪታንያ የግዛት አንድነት ላይ ጥያቄ እንዲነሳ ፈፅሞ ፈቅዳ አታዉቅም።የብሪታንያን የግዛት አንድነትና ሉዐላዊነትን ያላከበረችበት ጊዜ የለም።አንድ ነገር ግን ሐቅ ነዉ።ብሪግዚት የዚሕ የብሪታንያ ሉዑላዊነት ዉጤት ነዉ።ለአዉሮጳ መሪዎች ደግሞ የብዙ ሺሕ ሰዓታት ድካም ነዉ።ስለዚሕ እኛ አዉሮጳዉያን የብሪታንያን ሉዐላዊነት ምን ማለት እንደሆነ እናዉቃለን።»
የጀርመንዋ መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል እንደ ሐገር መሪ ለ16 ዓመታት የኖሩበትን ፖለቲካ ለመሰናበት ምናልባት ሰነድ፣ ዶሴያቸዉን በሚሸክፉበት ባሁኑ ወቅት የመሪነትን ወንበር ገና ከሚለማመዱት ከነቦሪስ ጆንሰን ጋር መነታረኩን የፈለጉ አይመስሉም።ሜርክል ከሁለት ዓመት የሩቅ ለሩቅ ጉባኤ በኋላ፣ አክራሪዉ ነዉጠኛ ቱጃር ፖለቲከኛ ዶናልድ ትራምፕ በተሸነፉ ማግሥት በተደረገዉ ጉባኤ የረኩ መስለዋል።በመሪነቱ የሚቀጥሉ ባልደረቦቻቸዉ ብዙ መስራት እንዳለባቸዉ ማሳሰባቸዉ ግን አልቀረም።
                                              
«የዚሕ የኮርን ዎሉ ስብሰባ  ዋና መልዕክት የተሻለች ዓለምን ለመፍጠር መጣር እንደምንፈልግ ማሳየታችን ነዉ።ወረርሺኙ ሲወገድ ደግሞ ይሕ ጥረታችን ይበልጥ አስፈላጊ ይሆናል።ጥረቱ ቀላል እንዳልሆነ እናዉቃለን።ለዚሕም ነዉ ለደሐ ሐገራት ልማት 100 ቢሊዮን ዩሮ ለመመደብ ያደረግነዉ ስምምነት ገቢራዊ እንዲሆን የተሻለ እንቅስሴ ማድረግ በጣም አስፈላጊ የሚሆነዉ።የዘላቂ ዕድገት አጀንዳ 2030ን በታሰበዉ መንገድ ገቢራዊ እንዳናደርግ ወረርሺኙ በማደናቀፉ የባከነዉን ጊዜ ለማካካስ  መጣርም አለብን።»
ጉባኤዉ ባለፉት አራት ዓመታት በፊትለፊትም በርቀትም ከተደረጉት ጉባኤዎች ሁሉ የተሻለ መግባባት የተያበት፣የአትላንቲካ ባሕር ማዶ=ለማዶ ግንኙነት ወደነበረበት የመመለሱ ምልክት የተንፀባረቀበት እንደነበር ብዙዎች መስክረዉለታል።በየዓመቱ እንደሚሆነዉ ሁሉ የድሆች፣ የመብት፣ የእኩልነትና የተፈጥሮ ሐብት ተቆርቋሪዎች ተቃዉሞ ግን አልተለየም።ሰልፉን ካደራጁት አንዱ የብሪታንያዉ  ግብረሰናይ ድርጅት የኦክስፋም ኃላፊ ማክስ ሎዉሰን የጉባኤዉን ዉሳኔ መራርና «ተስፋ አስቆራጭ» ብለዉታል።
«አስፈላጊዉ ድርጊት (እርምጃ) አለመወሰዱ በጣም ተስፋ አስቆራጭ ነዉ።እነዚሕ ከዓለም እጅግ ከፍተኛ ኃይል ያላቸዉ ሰባት ሐገራት ናቸዉ።ታዉቃለሕ።የሚያደርጉት በጣም ትርጉም አለዉ።ምንም ወይም በጣም ትንሽ ለማድረግ ሲወስኑ ስታይ፣ ከድርጊት ይልቅ ዝም ብለዉ ሲያወሩና

Großbritannien | Protest während G7 Gipfel in Cornwall

ዙሪያ ጥምዝ ሲጓዙ ስታይ ጥሩ ዓይደለም።ብዙ መስራት ነበረባቸዉ።አለማድረጋቸዉን ስታይ ተስፋ አስቆራጭ ነዉ ማለት ሲያንስ ነዉ።»
የብሪታንያ ንግስት ኤልሳቤጥ ዳግማዊት ለግብዣ፣ድግስ፣ ገራገሩ ዉይይት ጉባኝት ልዩ ድንመቀት ሰጥተዉታል።የ95 ዓመቷ ባልቴት ሁሉንም ጉባኤተኞች እኩል ከማስተናገዳቸዉ በተቸማሪ የ78 ዓመቱን አዛዉንት ጆ ባይደንና ባለቤታቸዉን ትናንት ሻይ ቡና ብለዋቸዋል።ንግስት ኤልሳቤጥ የብሪታንያን ዙፋን ከወረሱ ዘንድሮ 69 ዓመታቸዉ ነዉ።በዚሕ ዘመን ከተፈራረቁት 14 የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ንግስቲቱን ያልጎበኙት ሊንደን ጆንሰን ብቻ ናቸዉ።ንግስቲቱ ባለቤታቸዉ በሌሉበት የአሜሪካ ፕሬዝደንትን ሲያስተናግዱ ደግሞ ባይደን የመጀመሪያዉ ናቸዉ።ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ  ሸዋዬ ለገሰ DWLeave a Reply

Previous post NATO leaders see rising threats from China, but not eye to eye with each other
Next post በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫን ተከትለው የሚነሱ ክርክሮች ካሉ ለማስተናገድ ፍርድ ቤቶች ዝግጁ መሆናቸው ተገለጸ
Close
%d bloggers like this: