አሸባሪው ህወሃት ከህዳር ወር ጀምሮ በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል አገልግሎት መሰረተ ልማቶች ላይ በፈጸመው ጥቃት 11 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ጉዳት ማድረሱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል ማስታወቁን ፕሪንሳ ላቲና ዘገበ፡፡
አሸባሪው ህወሃት በኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ ኢንሱሌተሮች፣ ኮንዳክተሮች፣ ምሰሶዎችና ሌሎች የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ በትግራይ ክልልና በሌሎች ቦታዎች ጉዳት አድርሷል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ሞገስ መኮንን እንደገለጹት፤ በትግራይ ክልል በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የደረሰውን ጉዳት ወዲያው መጠገን ቢቻልም አሸባሪው ህወሃት መልሶ አውድሟቸዋል፡፡
“ጉዳቶችንም አከታትሎ ፈፅሟል” ያሉት አቶ ሞገስ፤ አሸባሪው ህወሃት የትግራይን ክልል ህዝብን ከፌዴራል መንግስት ለመነጠል ባለው ፍላጎት ትላልቅ መሰረተ ልማቶች ላይ ጉዳት አድርሷል።
ከኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች በተጨማሪ በቴሌኮሙኒኬሽን፣ በመንገዶች፣ በአየር መንገድና በውሃ መሰረተ ልማቶች ላይም አሸባሪው ህወሃት ጉዳት እንዳደረሰ አቶ ሞገስ ጠቅሰዋል።
በጦርነት መሃል ጥገና እንዲደረግ አለምአቀፍ ድንጋጌዎች ባያስገድዱም የሰላም ሁኔታው ሲሻሻል ተቋሙ የኤሌትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮችን ለመጠገን ዝግጁ መሆኑን ገልፀዋል ፡፡ (ኢዜአ)