ፖሊስ አዲስ አበባን ማዕከል ያደረገ የሽብር ሴራ፣ የጦር መሳሪያና በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር የውጭና የአገር ውስጥ ገንዘብ ያዘ

ፖሊስና የተለያዩ የጸጥታ መዋቅር አካላት በህብረት ለአዲስ አበባ የተደገሰ ሴራ መበጣጠሱን፣ ለሽብር ዓላማ ሊውሉ የነበሩ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ፣ 399 ሺህ 371 የአሜሪካ ዶላር፣ 26 ሺህ 755 ዩሮ፣ 19 ሺህ 788 ፓውንድ፣ 273 ሺህ 867 የተለያዩ ሀገራት ገንዘብ መያዙንና በርካታ መሳሪያዎችን ከተጠርታሪዎቹ ጋር በቁጥጥር ስር ማዋሉን አመለከተ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ ባደረገው ብርበራ ለሽብር አገልግሎት ሊውሉ የነበሩ በርካታ የጦር መሣሪያዎች እንደተገኙ ያመለከተው። የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ እንዲሁም ደጋፊዎቻቸው አዲስ አበባን ማዕከል ያደረገ ሁከትና ብጥብጥ ለመፍጠር አቅደው ሲሠሩ እንደነበር አስታውቀዋል።

አሸባሪዎቹ ነውጥና ብጥብጥ ለመፍጠር አቅደው ቢንቀሳቀሱም የአዲስ አበባ ፖሊስ ከመላው የሀገሪቱ የፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የአሸባሪ ቡድኑን ዓላማ ማክሸፍ እንደቻለ አመልክተዋል። “አሸባሪው ህወሓት አዲስ አበባ ተከብባለች በማለት ሕዝቡን የሚያሸብር ፕሮፓጋንዳ እየነዛ ሲንቀሳቀስ ነበር” ያሉት ኮሚሽነር ጌቱ፣ በተግባር ይህንኑ ውዥንብር በማራባትና በዚህ ሂደት ውስጥ የተሳተፉና ለመሳተፍ የተዘጋጁ የጁንታው አባላት እንዳሉ ፖሊስ በሠራቸው ሥራዎች ለማረጋገጥ መቻሉን ጠቁመዋል። 

በዚሁ መነሻ በተደረገ ክትትል በርካታ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንኮሚሽነሩ ገልጸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን መሠረት በማድረግ በተደረገ ብርበራ ለሽብር አገልግሎት ሊውሉ የነበሩ 28 ቦምቦች፣ 65 ክላሽንኮቭ መሣሪያ፣ ከ5 ሺህ በላይ ጥይቶች እንዲሁም 272 ሽጉጦችን ከ3 ሺህ በላይ ጥይቶችና ካርታዎች እንደተገኙ ገልጸዋል። በተጨማሪም 2 ሺህ 889 የብሬን ጥይት፣ ተጥሎ የተገኘ 83 የዲሽቃ ጥይቶች፣ 42 የጦርሜዳ መነፅር፣ ከ50 በላይ የሬዲዮ መገናኛዎችና ፈንጂዎች እንዲሁም በርካታ ወታደራዊ አልባሳትና የደንብ ልብሶች ፖሊስ መያዙን አስታወቀዋል። 

ለሽብር ዓላማ ሊውሉ የነበሩ ከ700 ሚሊየን ብር በላይ፣ 399 ሺህ 371 የአሜሪካ ዶላር፣ 26 ሺህ 755 ዩሮ፣ 19 ሺህ 788 ፓውንድ፣ 273 ሺህ 867 የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችም በተደረገው ብርበራ እንደተያዘ መናገራቸውን ፌደራል ፖሊስን ጠቅሶ ፋና ዘግቧል። ። የተለያዩ ሕገ-ወጥ ሰነዶች እና የባንክ ደብተሮች እንዲሁም ወደ ስምንት ኪሎግራም የሚመዝን የወርቅ እና የብር ጌጣ ጌጦች በተጠርጣሪዎች መኖሪያ ቤት በተደረገ ብርበራ መያዛቸውንም ኮሚሽነሩ ጨምረው ገልጸዋል።

Leave a Reply