የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ሕግ (ክፍል አንድ)

አረንጓዴ ወርቅ የሚል ስያሜ የተሰጠው እና የሀገሪቱ የውጭ ምንዛሪ የጀርባ አጥንት የሆነው የቡና ምርት ሻጭ እና ገዢ የሚገናኙበት ሂደት እና አሰራር ሕግን ያልተከተለ በመሆኑ፤ የዓመታት ልፋታቸውን ያክል ገቢ ማግኘት ያልቻሉ አርሶ አደሮች እና ነጋዴዎች የቅሬታ ምንጭ ሲሆን ይስተዋላል። ሕገ-ወጥ የቡና ግብይትን ለማስቀረት፣ የቡና አመራረት ስታንዳርዱን የጠበቀ ለማድረግና ዘመናዊ የግብይት ሥርዓት ለመዘርጋት የቡና ግብይት እና ጥራት ቁጥጥር ሕግ አዋጅ ቁጥር 1051/2009 ወጥቶ በስራ ላይ ውሏል። በመሆኑም በሚከተሉት ሁለት ክፍሎች ስለቡና ታሪካዊ አመጣጥ፣ ስለቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አዋጁ/ሕጉ አስፈላጊነት፣ የቡና ግብይት እንዴት መከናወን እንዳለበት፣ በቡና ግብይት የተሰማራ ሰው ግዴታዎች፣ ስለተከለከሉ ተግባራትና የሚያስከትሉት ተጠያቂነት እንዳስሳለን፡፡

1. ስለቡና ታሪካዊ አመጣጥ

ቡና በመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው (የታወቀው) በኢትዮጵያውያን እረኞች አማካኝነት በ800 ዓ/ም (በእርግጥ አንዳንዶች በ10ኛው ክፍለ ዘመን ሲሉ ሌሎች ደግሞ በ9ኛው ክፍለ ዘመን በማለት ስለሚገልፁ እርግጠኛ መሆን አይቻልም) አካባቢ ሲሆን እረኞቹም ያስተዋሉት ፍየሎቻቸው ቡናውን በልተው የመቅበጥበጥና የመደነስ ስሜት ሲታይባቸው ነው። በዚህም መሰረት በድሮ ጊዜ ከፋ ከሚባል አካባቢ አንድ ካልዲ የሚባል የፍየል እረኛ ከሚጠብቃቸው ፍየሎች ውስጥ አንዷ የሆነ ዛፍ ፍሬን ወይም ቅጠልን በልታ ያልተለመደ ባህርይ ማሳየት ትጀምራለች (በተለየ ሁኔታ እንደመዝለል አይነት)። በዚህ ጊዜ ካልዲ የዛን ዛፍ ቅጠል ወይም ፍሬ እቤቱ ወስዶ ሲቆላው እጅግ በጣም ደስ የሚል እና ልዩ ስሜት የሚሰጥ ሽታ ይሸተዋል። ከዛን ቀን በኋላ ካልዲ ቡናን በተለያየ መልክ መጠቀም ጀመረ፤ ለዓለምም አስፋፋው። እነሆ ዓለምም ከዛ ጊዜ ወዲህ የቡና ወዳጅ ብሎም ሱሰኛ እንደሆነች ይነገራል።

ከዚህም በተጨማሪ የተለያዩ ሀገራት የቡናን ስያሜ ሲያወጡ ቡናው ከተገኘበት አካባቢ ተቀራራቢነት ያለው ስያሜ ሰጥተውታል፡፡ (ለምሳሌ፡- በእንግሊዝኛ coffee /ኮፊ/ በፈረንሳይኛ café/ካፌ/ በደች ኮፊ/koffie/ በእብራይስጥኛ ካፈ/ka-feh/ በስዊድንኛ ካፈ(kaffe) ወዘተ በማለት የሰየሙበት ምክንያት ምናልባትም ቡናው ከተገኘበት አካባቢ ስያሜ ጋር በማመሳሰል ሊሆን ይችላል የሚል እምነትም አለ።

2. የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ሕግ አስፈላጊነት

See also  ግማሽ ሚሊየን ብር በጥሬው ሲቀበል እጅ ከፍንጅ የተያዘው ተከሳሽ በፅኑ እስራት ተቀጣ

ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬዋ ዋነኛ ምንጭ የሆነውንና የ15 ሚሊዮን ዜጎቿ ኑሮ የተመሰረተበትን ቡና ግብይቱንና የጥራት ቁጥጥሩን ለማስተዳደር የሚያስችል ህግ ከአፄ ኃ/ስላሴ ዘመን ጀምሮ ያላት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ሰለቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥርን በተመለከተ አሁን በስራ ላይ ያሉት የህግ ማዕቀፎች አዋጅ ቁጥር 1051/2009፣ ይህን አዋጅ ለማስፈፀም የወጣ ደንብ ቁጥር 433/2011 እና የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር መመሪያ ቁጥር 01/2010 ናቸው፡፡ ስለዚህ አንድ ከቡና ጋር ግንኙነት ባለው የስራ መስክ የተሰማራ ግለሰብ የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር አዋጁን ብቻ ሳይሆን ከአዋጁ ሰፋ ባለ መልኩ ዝርዝር ድንጋጌዎች የያዘውን ደንብና መመሪያውንም ጠንቅቆ ማወቅ የሚገባው ይሆናል፡፡

ሕጉ የወጣበት ምክንያት በዓለምአቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ በጥሬውና እሴት የተጨመረበት የቡና ምርት በጥራትና በከፍተኛ መጠን፣ ቀጣይነት ባለውና የምርት ዱካውን በጠበቀ ሁኔታ ለማቅረብ የሚያስችል የቡና ግብይትና ጥራት ቁጥጥር ስርዓት ለመዘርጋት እና የቡና ግብይትን ዘመናዊነት፣ ህጋዊነትና ፍትሃዊነት በማሻሻል የቡና አምራቾች፣ የግብይት ተዋንያንና የሀገሪቱን ተጠቃሚነት በላቀ ደረጃ ማሳደግ የሚያስችል የተለያየ አማራጭ ያለው የግብይት ስርዓት ለመዘርጋት እንዲረዳ ታስቦ ስለመሆኑ የአዋጁ መግቢያ ላይ ሰፍሯል፡፡

3. የቡና ግብይት እንዴት ይከናወናል?

የቡና ግብይት ስርዓትን ከማየታችን በፊት የቡና ግብይት ምን ማለት እንደሆነ በአዋጁ የተሰጠውን ትርጉም ስንመለከት “የቡና ግብይት ማለት ህጋዊ የግብይት ሥርዓትን በመከተል በመጀመሪያ ደረጃ የግብይት ማዕከላት፣ በምርት ገበያው፣ በውጪ ገበያ ወይም በሌሎች የግብይት አማራጮች በአምራቾች፣ በአቅራቢዎች፣ በላኪዎች፣ እሴት በሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎችና የውጭ ቡና ገዢ ኩባንያዎች እንዲሁም በጅምላ ነጋዴና ቸርቻሪ መካከል የሚከናወን የቡና ግዢና ሽያጭ ሂደት ነው” በማለት የተረጎመው በመሆኑ የቡና ግብይት ስርዓት ደግሞ ይህ መስተጋብር የሚመራበት ሰንሰለት ነው፡፡ በመሆኑም አዋጁ አንቀፅ 5 ስር የቡና ግብይት የሚከተሉትን አሰራሮች በመከተል መከናወን እንደሚገባው ይደነግጋል፡-

1. ቀይ እሸት ወይም የጀንፈል ቡና ግብይት አነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች ወይም አልሚ ባለሀብቶች ወይም በአቅራቢዎች ወይም በህብረት ሥራ ማህበራት ወይም በልማትና ግብይት ትስስር በፈጠሩ አልሚ ባለሃብቶች ወይም እሴት በሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎች መካከል፤

See also  በሚሊዮን ብር ማባበያ ቤተመንግስት ቦምብ ለማስወርወር ሲሰሩ ነበሩ በተባሉ ላይ ክስ እንዲሻሻል ብይን ተሰጠ

2. የአቅርቦት ቡና ለውጭ ገበያ ለማዘጋጀት የሚውል ከሆነ በአቅራቢና በላኪ መካከል ወይም በአቅራቢ እና በኤክስፖርት ቡና ቆዪ መካከል፤

3. የአቅርቦት ቡና ሆኖ የውጭ ገበያ ደረጃ ካላሟላ በአቅራቢና በጅምላ ነጋዴ ወይም በሀገር ውስጥ ቡና ቆዪ መካከል፤

4. ከወጪ ገበያ ምርት ዝግጅት የሚወጣ ተረፈ ምርት ቡና ከሆነ በላኪ እና በሀገር ውስጥ ፍጆታ ቡና ጅምላ ነጋዴ ወይም በሃገር ውስጥ ቡና ቆዪ መካከል፤

5. በኢትዮጵያ ምርት ገበያ የሚፈጸም የአቅርቦት ቡና ግብይት በምርት ገበያ ወይም በባለስልጣኑ በተፈቀደላቸው የግል የቡና ጥራት ምርመራና ደረጃ ምደባ ማዕከላት በተሰጠው የጥራት ደረጃና ባለቤትነትን ገላጭ የሆነ በተሟላ መረጃ መሰረት፤

6. በዚህ አንቀጽ ንኡስ አንቀጽ (2)፤ (3) እና (4) የተደነገገው እንደተጠበቀ ሆኖ በሌሎች የግብይት አማራጮች የሚፈጸም የአቅርቦት ቡና ግብይት ይህን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣው ደንብ ዝርዝር በሚወሰነው መሠረት በባለስልጣኑ እየተመዘገበ ይከናወናል፤

7. በኢትዮጵያ ምርት ገበያም ሆነ በሌሎች የግብይት አማራጮች የተሸጠ የአቅርቦት ቡና ለውጪ ገበያ ዝግጅት ከዝርዝር መረጃው ጋር ወደ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪ ይሸኛል፤

8. የአቅርቦት ቡና ደረጃ ከወጣለት ቀን ጀምሮ በኢትዮጵያ ምርት ገበያው አሰራር በሚፈቀደው የጊዜ ገደብ በመኪና ላይ ወይም ባለቤትነትን ገላጭ በሆነ መንገድ ተከማችቶ ይሸጣል፤

9. በመኪና ላይ በጊዜ ገደቡ ያልተሸጠ የአቅርቦት ቡና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወይም የመጋዘን አገልግሎት ለመስጠት በተፈቀደላቸው ድርጅቶች መጋዘን ብቻ ባለቤትነትን ገላጭ በሆነ አግባብ በማቆየት ለገበያ ይቀርባል፤

10. የሀገር ውስጥ ፍጆታ ቡና በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ ለጅምላ ነጋዴዎች ወይም ለሀገር ውስጥ ቡና ቆዪዎች በጨረታ ይሸጣል፤

11. ቡና ላኪዎች በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ወይም በሌሎች የግብይት አማራጮች የገዙትን ወይም በማሳቸውና በትስስር ያመረቱትን እንዲሁም ቆልተው ወይም ቆልተውና ፈጭተው ያዘጋጁትን ቡና ለውጭ ሀገር ቡና ገዢዎች በመሸጥ የሽያጭ ውል ሰነድ በብሔራዊ ባንክ ያስመዘግባሉ፤ ለባለሥልጣኑ ያሳውቃሉ፤

12. የወጪ ንግድ ደረጃ ያለው እሴት የተጨመረበት ቡና ተፈጥሯዊ ጣዕምና ባህሪውን ለማስተዋወቅ ሲባል በደንብ በሚፈቀደው ቦታና ጊዜ መሠረት በሀገር ውስጥ በውጭ ምንዛሪ ብቻ ለሽያጭ ሊቀርብ ይችላል፡ ፡

See also  ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት መኖር እና የሚያስከትለው ውጤት

13. የቡና እሴት የሚጨምሩ ኢንዱስትሪዎች ይህንን አዋጅ ተከትሎ በሚወጣ ደንብ መሠረት ከውጭ ሀገር ጥሬ ቡና ማስገባት ይችላሉ፡፡

አዋጁ በነዚህ ድንጋጌዎቹ የቡና ግብይቱን በነማን መካከል ሊፈፀም እንደሚገባ በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን ደንቡ ደግሞ ግብይቱ የት መከናወን እንዳለበት በአንቀፅ 4 ስር በመዘርዘር ደንግጓል፡፡ በዚህም መሰረት የቡና አምራች አርሶ አደሮች ከግል ቡና አቅራቢዎች ወይም ከመሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት ጋር የሚደረግ ግብይት በተፈቀደ የታጠበ እና ያልታጠበ ቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ላይ መከናወን የሚገባው ሲሆን የቡና ማዘጋጃ ኢንዱስትሪዎች ተደራሽ ባልሆኑባቸው ወይም በሌሉባቸው አካባቢዎች ደግሞ በሚቋቋሙ በመጀመሪያ ደረጃ ቡና ግብይት ማዕከላት ግብይቱ መካሄድ አለበት ይላል (የመጀመሪያ ደረጃ ቡና ግብይት ማዕከላት የሚባሉት በቡና አምራች አካባቢዎች አግባብ ባለው የክልል አካል የተፈቀደ ቀይ የእሸት ወይም የጀንፈል ቡና መገበያያ ሥፍራ ናቸው)፡፡ ግብይቱ የቡና ልማትና ግብይት ትስስር በፈጠሩ ቡና አምራች አርሶ አደሮችና አልሚ ባለሃብቶች መካከል ሲሆን እንዲሁም የወጪ ቡና ቆዪ ኢንዱስትሪዎች ከቡና አምራች አርሶ አደሮች ጋር ሲሆን በውል ስምምነቱ በተገለፀ ቦታ መሆን እንዳለበት ይደነግጋል፡፡

በክፍል ሁለት ስለግዴታዎች፣ የተከለከሉ ተግባራትና የወንጀል ተጠያቂነትን አስመልክቶ ያዘጋጀነውን ማብራሪያ በቀጣይ ሳምንት ይዘን እንቀርባለን፡፡

ፍትህ ሚኒስቴር

Leave a Reply