ትህነግ ጦርነት እንደሚከፍት ይፋ አደረገ፤ አማራ ክልል “ለክተት ተዘጋጁ”አለ፤ መከላከያ በተጠንቀቅ ላይ ነው

“በወረራ ተይዞብኛል” ሲል ትህነግ ከሚገልጸው ወልቃይትና በሻዕቢያ ተይዞብኛል ከለው አካባቢ በቀር ከሕዝብ ጋር ውይይት በማካሄድ የሰላም አማራጭ የማይሆን ከሆን ወደ ጦርነት እንደሚገቡ ከሕዝብ ጋር ስምምነት መደረሱን የአሜሪካ ሬዲዮ የትግራይ ዘጋቢ አስታውቋል። ከወልቃይት የወቅቱ አስተዳደር በኩል ለህዝቡ “.. የአንድ ወር ስንቅ በማዘጋጀት በየቤቱና በየቀበሌው ሆኖ ለምናቀርበው የፈጥነህ ድረስ ጥሪ ዝግጁ ሆኖ እንዲጠብቅ ሲል ኮሚቴው መልዕክቱን ያስተላልፋል” ሲል፣ ክልሉ በበኩሉ ” ለሙሉ ክተት ተዘጋጅ” ሲል የውስጥ ባንዳን እንደሚመታ አዋጅ አውጇል።

የትግራይ ክልል አመራሮች በክልሉ የተለያዩ ቦታዎች ከሚገኙ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሰሞኑ ባደረጉት ውይይት፤ ነገሮች በሰላማዊ መንገድ የማይፈቱ ከሆነ ሕዝቡ ሳይወድ በግድ

የትግራይን ሕልውናና ዋስትና ለማረጋገጥ ሲባል ጦርነት ለመክፈት የክልሉ አስተዳደርና ሕዝብ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውን፣ ይህም ስምምነት በጭብጨባና በእልልታ መደገፉን በመቀለ ተደረገ በተባለው ስብሰባ መሳተፋቸውን የገለጹ ሁለት ሰዎች ሲናገሩ በዘገባው ተሰምቷል። የሰላም አማራጭ እንደሚከተሉም ሲገለጽ ሕዝብ በጭብጨባና በእልልታ ምላሽ መስጠቱን አመልክተዋል።

በሕዝባዊ ውይይቱ ላይ የተሳተፉ የመቀሌ ከተማ ነዋሪዎችን ዋቢ ያደረገው ዘገባ ሕዝብ በርካታ የዕለት ተዕለት ችግሩንና አጠቃላይ ችግሩን በማንሳት ጥያቄ አቅርቧል። ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረሚካኤል የሕዝቡን ሕልውና ለማረጋገጥ መጀመሪያ የሚወሰደው እርምጃ ሰላማዊ ድርድር መሆኑንን አመልክተዋል። በድርድሩ ምን እንደሚፈልጉ ግን አልተዘረዘረም። “አማራጭ ከታጣ ግን ወደ ጦርነት እንገባለን” ሲሉም ትህነግ ያስቀመጣቸው አማራጮች በይፋ አልተነገሩም። ሕዝቡ ጦርነት አማራጭ እንደሚሆን ሲነገረው ማጨብጨቡና ዕልልታውን ማሰማቱን ቪኦኤ ቢገለጽም ቀደም ባሉት ሳምንታት ቢቢሲ አማርኛና ሌሎች ሚዲያዎች ልጆቻቸውን ወደ ጦርነት ለመላክ ያልተስማሙ እናቶች እየታሰሩ መሆናቸውን መዘገባቸው ይታወሳል።

በትግራይ ረሃብ፣ በሽታና የመድሃኒት እጥረት መኖሩን ሕዝብ መጠየቁን፣ የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት አመልክተው ” ተኩስ ቆሟል ቢባልም በውጤት ደረጃ ለውጥ አላመጣም። ትግራይ ተከባ ነው ያለችው” ብለዋል። “ከበባ” ያሉትን ጦርነት እንደሆነ ገልጸዋል። እናም አሁን በይፋ ወደ ጦርነት ቢገባ አዲስ ነገር እንዳልሆነ ተመልክቷል።


አማራ ክልል ትህነግ ዳግም ጦርነት ስላወጀ የ”ዝግጁነትን” አዋጅ አወጣ

በመሆኑም በአንድ በኩል ከፌደራል የጸጥታ መዋቅር ጋር በመቀናጀት ከወያኔ የሚሰነዘርብንን ጥቃት ለመከላከል በተጠንቀቅና በዝግጁነት መቆም፤ በሌላ በኩል ደግሞ በውስጣችን ለወያኔ ሴራ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩትን ህገ-ወጦችንና ስርዓት አልበኞችን በመቆጣጠር የክልላችን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ ግንባር ቀደም የትኩረት አቅጣጫ እንዲሆኑ ወስኗል፡፡


እሳቸው ይህን ቢሉም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በቀልቃይትና በአፋር ትንኮሳ እየካሄደ መሆኑንን፣ በዚህም ሳቢያ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና በኢትዮጵያ የአሜሪካን አምባሳደር የትህነግን የጦርነት ትንኮሳ እንዲያስቆሙ ወይም ምክር እንዲሰጡ መንግስት ማስታወቁን አመልክተዋል።

ሰሞኑንን አስደንጋጭ የተባለ አሃዝ ይፋ ከሆነባት ወልቃይት የክተት አዋጅ ተሰምቷል። በወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ አየለ ስም ይፋ የሆነው አዋጅ “ይህን የሰማህ ሁሉ” ሲል ጥሪውን ያሰማል። “ይህን የሰማህ ሁሉ … የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ጥሪ ተቀብያለሁ የሚል ሁሉ የአንድ ወር ስንቅ በማዘጋጀት በየቤቱና በየቀበሌው ሆኖ ለምናቀርበው የፈጥነህ ድረስ ጥሪ ዝግጁ ሆኖ እንዲጠብቅ ሲል ኮሚቴው መልዕክቱን ያስተላልፋል።” ይላል። ይህ አዋጅ የታወጀው ” ወራሪዉ የትግራይ አሸባሪ መንጋ ኃይል ወልቃይት ጠገዴንና አከባቢውን ከ16 ዓመት ታዳጊ ጀምሮ እስከ 70 ዓመት አዛውንት የሆነ ማንኛውንም ትግራዋይ፤ የወልቃይት ጠገዴ አማራ ህዝብን እንዲወር የክተት አዋጅ አውጇል” በሚል አስቀድሞ ክተት በማለቱ እንደሆነ ተመልክቷል።


ወልቃይት “የወር ስንቅህን አዘጋጅተህ ለክትተ ጥሪ ተዘጋጅ”

ይህንን የወልቃይት ጠገዴ አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ ጥሪ ተቀብያለሁ የሚል ሁሉ የአንድ ወር ስንቅ በማዘጋጀት በየቤቱና በየቀበሌው ሆኖ ለምናቀርበው የፈጥነህ ድረስ ጥሪ ዝግጁ ሆኖ እንዲጠብቅ ሲል ኮሚቴው መልዕክቱን ያስተላልፋል።


“ትግራይ ከከበባ ለመውጣት ትዋጋለች፤ ህዝብም በደስታና እልልታ ተስማምቷል” የሚለው ዘገባ ቅድሚያ የሰላም አማራጭ እንደሚታይ ቢያስታውቅም ቅድሚያ ሃያ ከመቶ ልጆቻቸው የት እንደደረሱ አያውቅም የተባሉት ወልቃይቶችና አማራ ክልልም “የወልቃይትን ጥያቄ የማይታሰብ” ሲሉ ዘግተዋል። ” በጉልበት የተወሰደ፣ በጉልበት ተመልሷል” በሚል የትህነግን የሃይል እርምጃ እንደ አግባቡ ለመመለስ መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።

የአማራ ክልል ባወጣው መግለጫ በግልጽ ቋንቋ ዝግጁ መሆኑንን፣ ይህን የሚያስተጓጉሉ የውስጥ ለውስጥ ባንዶችን ለመልቀም መወሰኑንን አስታውቋል። መከላከያን ወልቃይት፣ ወልደያና በተለያዩ ግንባሮች ተዟዙረው ያነቃቁት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የወታደር መለዮ ከለበሱ ከራርመዋል። አቶ ደመቀ መኮንን ከትናንት በስቲያ “ከነካን የምያዳግም እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።

ወደ ትግራይ የሚገባው መድሃኒትና የምግብ እርዳታ በቂ እንዳልሆነ የክልሉ ሃላፊዎች አስታውቀዋል። በዚህም ሳቢያ በሱዳን ያለውን ኮሪዶር አጽድቶ ያለ ከልካይ እንዳሻቸው ለመጠቀም በሚል ወደ ጦርነት እንደሚገቡ ማመልከታቸው ፍጹም እብደት እንደሆነ የሚናገሩ አሉ።

ምክትል ኤታማዦር ሹም ጀነራል አበባው አርባ ሺህ የማይሞላ ሰራዊት በመቶ ሺዎች ከሚቆጠረው የትህነግ ሃይል ጋር እንዴት እንደገጠመና የውጊያ ሂደቱና ሰራዊቱን መልሶ የማደራጀቱ ስራ እንዴት እንደተሰራ ባስታወቁበት ቃለ ምልልሳቸው፣ ይፋ እንዳደረጉት ሳይሆን ዛሬ መከላከያ ሌላ ቁመና፣ ሌላ አደረጃጀት፣ ሌላ ስብዕናና ሌላ መልክ፣ እንዲሁም በትጥቁ የዘመነ በመሆኑ ትህነግ ወደ ጦርነት ከገባ እልቂቱ እጅግ እንደሚከፋ በርካቶች እየገለጹ ነው።

ትህነግም መሬት ላይ ያለን ሃቅ፣ ወቅታዊ ሁኔታና አቅሙን በማገናዘብ፣ የትግራይን ወጣቶች ለመቆጠብ ሲባል የጦርነት አማራጭን መንገድን እንዲተው የሚመክሩ፣ መንግስትም እንደ አገር መሪ ለሰላም በሚያመቹ መንገዶች ሁሉ እጁን አስፍቶ፣ ትዕግስቱን አብዝቶ ለትግራይ ሕዝብ ሲባል የጀመረውን የሰላም ጅማሮ እንዲያሰፋ ይጠይቃሉ።

ከኤርትራ ጋር ውዝግብ ያለባቸው አካባቢዎችን በተመለከተ ራሱ ትህነግ “አያዋጣህም” ሲባል አልሰማም ብሎ በማይሆን መረጃ ሄግ ላይ ይግባኝ በማይባልበት ፍርድ እንዲያስረክብ በትፈረደበት መሰረት ጉዳዩን በሰላም መቸረስ ሳይችል ሁለት አስርት ዓመታት ማሰለፉ ድክመቱ እንደሆነ በተደጋጋሚ ተመልክቷል። ውሳኔው ምንም እንኳን እንደ አገር ኪሳራ ቢሆንም መቀበል የግድ መሆኑንን ባለሙያዎች ቢመክሩም ትህነግ ሊስማማ አልቻለም።

በዚህ መልኩ ጦርነትም፣ ሰላምም በሌለበት መልኩ ለሁለት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ድንበር አፍጥቶ ሲጠብቅ በድንገት ” መብረቃዊ ጥቃት” የተባለው የክህደት በትር ካርፈበት በሁዋላ አጋጣሚውን በመጠቀም ኤርትራ “ይገባናል” የምትለውን ቦታ መያዟ ታውቋም። ዛሬ ትህነግ ከህዝብ ጋር ስብሰባ አድርጎ ሻዕቢያንና የኢትዮጵያን መከላከያ አንድ ላይ ለመደምሰስና “የህልውና ጉዳይ” ያለውን ጦርነት በድል ለማጠናቀቅ ከስምምነት የመድረሱ ዜና ቀና አሳቢዎችን አስደንግጧል። የማይቀረው ውጊያ በክረምት እንደሚጀመር ነገሩ ከስጋትም በላይ ሆኗል።

“ሂሳብ እናወራርዳለን” በሚል ስሌት አማራና አፋር ክልልን ወሮ የነበረው ትህነግ በቆየባቸው አካባቢዎች ሁሉ ፈጸሟቸዋል የተባሉት ግፎች ገና ሳያሽሩ ዳግም ወደ አማራና አፋር ክልል ለመግባት መሞከር ብዙም እንደማይሳካ የሚጠቁሙ ” ለድርድር የማያመቸውን የአገሪቱን አከላለልና ፖለቲካዊ መዋቅር እስከ መቀየር የሚያደርስ ውሳኔ ተወስኖ ጉዳዩ በሰላም ቢፈታ፣ የአማራና የትግራይ ሕዝብ የሚጋደለበት መሰረታዊ ምክንያት ስለሌለ አብሮ እንዲኖር ባህላዊ እሴቶቻችንን ልንጠቀም ይገባል” ይላሉ። የተጀመረው አገራዊ ውይይት ይበልጥ ውጤቱ የተሳካ እንዲሆን በማገዝና በቀናነት በውይይቱ በመሳተፍ ለዘላቂ ስለም ቅድሚያ መስጠቱ እንደሚጠቅምም አመልክተዋል።

“ለፖለቲከኞች ከርስና ለስልታን ጥማት ህዝብ ማለቅ የለበትም” ሲሉ የሚከራከሩ ሕዝብ ከሁሉም ወገን ሚዛኑንን ጠብቆ ፖለቲከኞች ላይ ጫና እንዲያደርግ፣ ምሁራንም የነገውን በማየት እርምት እንዲወሰድ እንዲመክሩ፣ ከሁሉም በላይ አሁን ጦርነት ከተጀመረ ውጤቱ እጅግ የከፋ ስለሚሆን የትግራይ ህዝብም ረጋ ብሎ እንዲያስብ በስፋት ሃሳብ እየተሰጠ ነው።

ትግራይ ከአማራና ኤርትራ እንዲሁም ከአፋር ጋር የከፋ ጸብና በቀላሉ ሊረሳ የማችል ቂም ውስጥ ወድቃለች። ይህ አላንስ ብሎ ዳግም ወደ ጦርነት ማምራት ፍጹ አዋጪ እንዳልሆነ የሚናገሩ የትግራይ ተወላጆችም ከመቼውም በላይ ድምጻቸው እያሰሙ ነው። ጀነራል አበበ ተክለሃይማኖት “እርስ በርስ እናተራምሳቸዋለን” ሲሉ እንደተሰማው ብቻ ሳይሆን ነገሮች ገልብጦ ማሰብም አግባብ እንደሆነ የሚመክሩ የትግራይ አንቂዎችና ምሁራን ከጦርነት የሚገኝ ነገር እንደሌለ በማስታወቅ ትህነግ ወደ ሰላማዊ ንግግር እንዲያተኩር ጅምሩን በመደገፍ ጫናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ መክረዋል።

በቅርቡ ከትግራይ ተፈናቅለው ወደ አማራ ክልል በአስር ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎች መግባታቸው ይታወሳል። የትህነግ አመራሮችም ” አማራ ወንድማችን” እያሉ “ሂሳብ እናወራርዳለን” ባሉት ምትክ ሲያሞካሹ እየተሰማ ነው።

You may also like...

Leave a Reply