“አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድንና የጥፋት ኃይል ዳግም ከሞከረ የማያዳግም ቅጣት ይጠብቀዋልʺ

“አሸባሪው የትግራይ ወራሪ ቡድንና የጥፋት ኃይል ዳግም ከሞከረ የማያዳግም ቅጣት ይጠብቀዋልʺ ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ

የአማራ ክልል ጀግኖቹን እያመሰገነ ነው፡፡ ክልሉ ʺበሕግ ማስከበርና በሕልውና ዘመቻው የተከፈለ መስዋእትነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት እና አንድነት” በሚል መሪ ሃሳብ ጀግኖቹን እያመሰገነ ነው፡፡

በምስጋና ዝግጅቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ተኮላ አይፎክሩ ሀገር ላቆሙ ጀግኖች ታላቅ ክብር ይገባቸዋል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል የጸጥታ ኃይሎች ሕዝብን ከማንኛውም ስጋት የመጠበቅ ኃላፊነትና ስልጣን እንደተሰጣቸው ያነሱት ኮሚሽነሩ የትግራይ ወራሪ ቡድን ክልሉን ለማተራመስና ሀገር ለማፈራረስ የከፈተውን ጦርነት ከሌሎች የጸጥታ ኃይሎችና ከሕዝብ ጋር በመሆን ያደረገውን ወረራ በመመከትና አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት አኩሪ ጀብዱ ፈጽመዋል ብለዋል፡፡ የሠሩት አኩሪ ጀብዱ በታሪክ ዚከር እንደሚኖርም ገልጸዋል፡፡

ወራሪው ቡድን ጦርነትን እንደ ብቸኛ አማራጭ በመውሰድ፣ የጦርነት ነጋሪት በመጎሰም፣ በየአደባባዩ በፉከራ የጀመረውን እብሪት ያለ ይሉኝታ ወደ ተግባር በመቀየር በክልሉ ጭካኔ የተመላበት ቁሳዊና ሰብዓዊ ጥፋት አጥፍቷል ነው ያሉት፡፡ ተዋህዶና በባሕል ተጋምዶ የኖረውን ሕዝብ ደም አቃብቷልም ብለዋል፡፡ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት መፈጸሙንም ገልጸዋል፡፡

አሁንም ከባለፈው ችግር ሳይማር ተጨማሪ ችግር ለመፍጠር ሲወራጭ ይስተዋላል ያሉት ኮሚሽነሩ የወራሪው ቡድን ወረራ የተቀለበሰው፣ ጠላት አይቀጡ ቅጣት የተቀጣውና አሁን ያለው ሰላምና ድል የተገኘው በክፉ ቀን ደራሽ በሀገር ባለውለታና ቆራጥ ጀግኖች መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ድሉ የተገኘው ሕዝቡ በቁጣ በመነሳት ከጸጥታ ኃይሉ ጋር ባደረገው ተጋድሎ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለድሉ መገኘት በሁሉም ዘርፍ የተደረገው የተቀናጀ ሥራ ወሳኝ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡ ወራሪው ቡድን አሁንም ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሔ የጥፋት ኃይል ዳግም ከሞከረ የማያዳግም ቅጣት ይጠብቀዋልም ብለዋል፡፡

ጀግኖችና የጀግና ቤተሰቦችን ስንሸልም መላ የጸጥታ ኃይሉንና ሕዝቡን የበለጠ ለግዳጅ ዝግጁ ለማድረግ ነውም ብለዋል፡፡
በየትኛው ወራሪና ጸረ ሰላም ኃይል ላይ አጸፋዊ እርምጃ ለመውሰድ መደራጀትና ራስን ማዘጋጀት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ የጎላ አስተዋጽዖ ለነበራቸው ጀግኖች እውቅና እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡ ጀብዱ ለፈጸሙ ጀግኖች የማዕረግ እድገት መደረጉንም ገልጸዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ (አሚኮ)

You may also like...

Leave a Reply