ሚኤሶ -ከሴፍትኔት እርዳታ ጠባቂነት ወደ ስንዴ አምራችነት

ይህ በምዕራብ ሀረርጌ ሚኤሶ ወረዳ ተንጣሎ የሚታይ በኩታ ገጠም የለማ የስንዴ ማሳ ነው።

የአካባቢው አርብቶ አደሮች ከዚህ ቀደም መሬታቸው ስንዴን ማብቀል እንደማይችል በተጫነባቸው የተሳሳተ ምልከታ እነዚህ ሰፋፊ መሬቶች ላይ ዘጠኝ ወራትን ጠብቆ የሚደርስ የማሽላ ዘር ብቻ እየዘሩ ተጠቃሚ መሆን ሳይችሉ በድህነት እና በተረጂነት ቆይተዋል።

መንግስት ለግብርናው ዘርፍ በተለይም በራስ አቅም አምርቶ ከራስ አልፎ ኢትዮጵያን በችግር እና በረሃብ እንዲሁም በተረጂነት ስያሜ ያውቋት ለነበሩትም ለመትረፍ በያዘው ቁርጠኝነት በየአካካቢው ያለው የመልማት አቅም በተግባር እየታየ ነው።

ካልተለመዱት እይታዎች እና ይሆናል ተብለው የማይታሰቡ የነበሩ ነገር ግን ለለውጥ በቆረጡት እጆች ትጋት እውን ሆነው ከታዩት ውጤቶች መካከል ይህ በምዕራብ ሃረርጌ ዞን ሚኤሶ ወረዳ የሚታየው ሰፊው በኩታ ገጠም የለማው የስንዴ ማሳ ነው።
ለከፍተኛ ድርቅ የተጋለጠ እና በሴፍትኔት እርዳታ ላይ ተመስርቶ የድህነት ህይወትን ሲመራ ቆይቷል።
የድርቁ ግዜ ሲመጣም እንስሳቶቹም ተጎጂዎች እና ከፍተኛ ሰለባዎች ናቸው።

በዚህም አካባቢው ማብቀል አይችልም ተብሎ ከመቆየቱ የተነሳ የአካባቢው አርብቶ አደር ማህበረሰብ ስንዴን ዘርቶ ማብቀል ይቅር እና በማሳ ላይ ተዘርቶ የሚኖረውን ቁመና እንኳን አይቶ አያውቅም ነበር።

ማህበረሰቡን አሳምኖ ስንዴን በስፍራው ማብቀል መቻሉ የአመራሩን እና የግብርና ባለሞያዎችን ከፍተኛ ጥረት የሚጠይቅ ስራ ነበር፣

ተከታታይነት ባለው ጥረት እና ክትትልም የዝናብ ግዜን ጠብቆ ዘጠኝ ወራትን በሚፈጅ እድሜ ማሽላ ብቻ እያመረተ እጆቹን ለእርዳታ ይዘረጋ የነበረው ማህበረሰብ ያልታመነው እና ያልተጠበቀው ውጤት ባለቤት ወደ መሆን ተሸጋገረ።

መንግስት በግብርናው ዘርፍ ላይ በካሄደው ኢኒሼቲቭ አርብቶ አደሩ ያላመነው እና የማይሆን ይመስለው የነበረውን የስንዴ ዘለላ በማሳው ላይ ማየት ቻለ።

በተደጋጋሚ ድርቅ ስትጠቃ የኖረችው እና የሴፍትኔት ጠባቂ የነበረችው ሚኤሶ ወረዳ የመቻል፣ የማሸነፍ እና ተግቶ የመስራት ውጤት ማሳያ ሆነት።
በዚህም ይህ መሬት አሁን በሶስት ወራት ጥረት እና ክትትል ብቻ በስንዴ ዘር ተሸፍኖ ምርት ወደ መስጠት ተሸጋግሯል።

አሁን ወረዳው ከ17 ሺህ ሄክታር መሬት ስንዴተሸፍኗል።ከዚህም ከ500 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል፡፡

See also  ኢትዮጵያና ፈረንሳይ የ32 ሚሊየን ዩሮ የድጋፍ ስምምነት ተፈራረሙ

“ስንዴን በእርዳታ እህል ብቻ ነው የምናውቅ የነበረው” የሚሉት የአካባቢው አርሶ አደሮች “አሁን ግን ዘርተን ሲበቅል ማየታችን ከዚህ ቀደም መሬቱን ሳንጠቀምበት መቆየታችችን በቁጭት የሚያሳይ ነው” ይላሉ።

በተገኘው የዘርፉ መነቃቃትም በወረዳው ከዚህ በፊት ያልተለመዱ የማንጎ፣ አቮካዶ እና ማሾ ምርቶች ስራ እንቅስቃሴም እየተስተዋለ ነው።

አርብቶ አደር ተብሎ ግዜን አስልቶ እርዳታ እንዲጠብቅ የተደረገው ማህበረሰብም ከእንስሳቶቹ በተጓዳኝ ማሳውን በዘመነ ምልኩ እያለማ ነው።
ለዚህ የማይቻል ይመስል ለነበረው ውጤት የወረዳው የግብርና ባለሞያዎች ከአርሶ አደሩ ጋር በመጣመር በማሳዎቹ ላይ ውለው እና አድረው ያከናወኑት ስራ የማይዘነጋ ቁርጠኝነታቸው ነው።

ሚኤሶ ታሪኳን በመቀየር ላይ ነች። በዚህም የማሸነፍ ማሳያ ወደመሆን ተሸጋግራለች።

Leave a Reply