ከመወሰንህ በፊት ረገብ በል !

ከዚህ በፊት አንድን ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ወስነህ፣ በኋላ የተጸጸትክባቸውን ጊዜያት መለስ ብለህ ብታስባቸው ከእነዚህ ሁለት ሁኔታዎች መካከል አንዱን ታገኛለህ ብዬ እጠረጥራለሁ፡-

1) ውሳኔውን ስትወስን በከፍተኛ የስሜት ግለትና ደስታ ውስጥ ነበርክ፣ ወይም ደግሞ፣

2) ውሳኔውን ስትወስን በወረደ ስሜት (የስሜት ቀውስ) ውስጥ ነበርክ፡፡

እነዚህ ሁለት የስሜት ጥጎች በሕይወትህ “ወሳኝ የሆኑ ውሳኔዎችን” ከመወሰንህ በፊት ረገብ እስከምትል ልትጠብቅ የሚገባህን የስሜት ጥጎች ጠቋሚ ናቸው፡፡

  1. ስሜትህ ከፍ ሲል – ረገብ በል!

አንድ ሚልየን ብር ሎተሪ ደርሶት ከመደሰቱ የተነሳ በዚያው ቀን ላገኛቸው የቤተሰቦቹ አባላት ለእያንዳንዳችሁ አንድ መቶ ሺህ ብር እሰጣለሁ በማለት በጉጉት የተናገረ ጎልማሳ፣ ብሩን እጁ ካስገባና ከረገበ በኋላ ለመስጠት ቃል የገባውን ገንዘብ ሲደምረው ሁሉንም ገንዘብ እንደሚያስከፈልው ወደመገንዘብ ይመጣል – እጅግ ቀላልና ግልጽ ምሳሌ!

በአንድ ሁኔታ ምክንያት የስሜት ግለት ውስጥ ስትገባና እጅግ ስትደሰት ማንነትህ በዚያ ሁኔታ ምክንያት የምታገኘውን አመርቂ ነገር ከእውነታው ባሻገር አጉልቶ የማየት ዝንባሌ ውስጥ ይገባል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ በኋላ የማትዘልቀው ውሳኔ፣ መሃላና ቃል ኪዳን ውስጥ ራስህን ታገኘዋለህና ከመወሰንህ በፊት ረገብ በል! አየህ፣ በሕይወታችን እጅግ በጣም ደስ የሚያሰኝ ሁኔታ፣ እድል ወይም ውጤት በምናገኝበት ጊዜ የሚኖረን በደስታ የተሞላ የስሜት ግለት በተረጋጋንበት ጊዜ ለማንወስናቸው ውሳኔዎችና ለማንገባቸውን ቃል ኪዳኖች አጋልጦ ይሰጠናል፡፡ ከዚያም ያንን ውሳኔ ከወሰንን በኋላ ከስሜቱ ረገብ ስንል እውነታው ብቅ ይላል፡፡

  1. ስሜትህ ዝቅ ሲል – ረገብ በል!

አንድ ለሞት ሊያጋልጠው የሚችል ህመም ምልክት ያየ የመሰለው ወጣት ይህ በሽታ በውስጤ አለ ብሎ ከመደንገጡና ከመስጋቱ የተነሳ ያለውን ትምህርት በማቋረጥና በተስፋ መቁረጥ ሁሉንም ነገር እርግፍ አድርጎ በመተው ሁለት አመታት አባከነ፡፡ ከዚያም ከስሜቱ ረገብ ሲል የህመም ስሜቱ ከብዙ አይነት ሁኔታዎች ሊመነጭ እንደሚችል እዲያስብ የሚያስችለውን መረጃ ማግኘት በመጀመሩ ምርመራን ሲያደርግ የፈራው ነገር እንዳልሆነ ወደማወቅ መጣ – ሌላ እጅግ ቀላልና ግልጽ ምሳሌ፡፡

በአንድ ገጠመኝ ምክንያት ስሜታችን ሲወርድ ሁኔታውን ከእውነታው ባሻገር አጋንኖ የማሳየት አቅም ስላለው ትክክለኛ ውሳኔን የመወሰን አቅማችንን ይነጥቀናል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ከዚያ የስሜት ቀውስ መለስ ብለን በረገብንበት ጊዜ ለማንወስናቸው የተሳሳቱ ውሳኔዎች አሳልፎ ይሰጠናል፡፡ ከዚያም ያንን ውሳኔ ከወሰንን በኋላ ከስሜቱ ረገብ ስንል እውነታው ብቅ ይልና እንደፈራነው እንዳልሆነ ይገባናል፡፡ የውሳኔው ዘር ግን አንዴ ስለተዘራ በኋላ መብቀሉ አይቀርም፡፡

See also  የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት አማራዎች የተጨፈጨፉባቸው በርካታ የጅምላ መቃብሮች መገኘታቸውን የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ጥናት አጋለጠ

ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ሁኔታዎች ራስን ለመጠበቅ ረገብ በማለት ለሁሉም ነገር በቂ ጊዜን መስጠት አስፈላጊ ነውና – ረገብ በል !!!

Via dr Eyob Mamo

Leave a Reply