የዲጂታል መታወቂያ ምንነት እና የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1284/2015 ዋና ዋና ገጽታዎች

ዘመናዊ የመታወቂያ ስርዓት በአንድ ሀገር ውስጥ ተግባራዊ ሲደረግ መሰረታዊ የሚባሉ ጠቀሜታዎች ያሉት ሲሆን፣ ከነዚህ ጠቀሜታዎች መካከልም ሃገራዊ ልማትን በአግባቡ ለማቀድ፣ ምጣኔ ሃብታዊ ሽግግር ለመፍጠር፣ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን፣ የሀብት ብክነትን ለመቀነስ፣ ወንጀልን ለመከላከል፣ ፖሊሲዎች ሲቀረጹ እና የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ድግግሞሽን ለመቅረፍ እና አካታችነትን ለማጎልበት የሚረዳ መሆኑ የተረጋገጠ ነው፡፡ በኢትዮጵያም በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የበለፀገ፣ ዘርፍ ተሻጋሪ፣ መሠረታዊ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መዘርጋት አሰፈላጊ መሆኑ ታምኖበት የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ተቋቁሞ ላለፉት ሁለት ዓመታት በግንባታና በሙከራ ሂደት ላይ ቆይቷል። በዚህ ሂደት ውስጥ ከተለያዩ የአገልግሎት ዘርፎች ጋር ለማስተሳሰር የሙከራ ትግበራ ስራዎችን በማከናወን ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎችን መዝግቦ አብዛኞቹን የዲጂታል መታወቂያ ባለቤት ለማድረግ ተችሏል።

በዚህ የሙከራ ትግበራ ወቅት ከተከናወኑ ተግባራት ውስጥ ሌላው የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ማዘጋጀት ሲሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መጋቢት 21 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው መደበኛ ስብሰባ “የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1284/2015” አድርጎ አፅድቆታል፡፡ አዋጁ ከሌሎች ሀገሮች የመታወቂያ አዋጆች አንፃር ዘግየት ብሎ የወጣ በመሆኑ በሌሎች ሀገሮች የታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን በሚያስችል መልኩ የተዘጋጀ ሲሆን፣ ዘመኑ የደረሰበትን የዲጂታል መታወቂያ በዘመናዊ መልኩ ለነዋሪዎች ለመስጠት እና ለማስተዳደር በማለም የወጣ ነው፡፡ አዋጁ በርካታ ጉዳዮችን የያዘ ሲሆን፣ በዝርዝር በሌላ ፅሁፍ የምንመለስበት ሲሆን፣ በዚህ ክፍል የአዋጁን ዋናዋና ድንጋጌዎች በተለይም ከዓላማዉ ጋር በማገናኘት ለማየት እንሞክራለን፡፡

  1. የዲጂታል መታወቂያ ምንነት እና አገልግሎት

በየትኛውም ሀገር የሚገኝ የመታወቂያ ሥርዓት በሁለት የሚከፈል ሲሆን እነሱም አገልግሎት ተኮር መታወቂያ (Functional ID) እና መሰረታዊ መታወቂያ (Foundational ID) ናቸው፡፡ አገልግሎት ተኮር የመታወቂያ (Functional ID) ማለት የተወሰነ አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል መታወቂያ ነው። እንዲህ አይነት መታወቂያ፣ ከተሰጠበት አገልግሎት ውጭ ለሌሎች ነዋሪነትን እና ማንነትን በማረጋገጥ ለሚሰጡ አገልግሎቶች ተቀባይነት ላይኖራቸው ይችላል፡፡ መሰረታዊ መታወቂያ (Foundational ID) ማለት በተሰጠበት ሀገር ውስጥ በየትኛውም ቦታ ተቀባይነት ያለው እና ማንነትን በማረጋገጥ ለሚሰጡ የትኛውም አገልግሎቶች ተቀባይነት ያለው የመታወቂያ አይነት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ መሰረታዊ መታወቂያ (Foundational ID) ለአገልግሎት ተኮር መታወቂያዎች (Functional ID) እንደመረጃ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል፡፡

መሰረታዊ መታወቂያ በተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ስያሜዎች ሊኖሩት የሚችሉ ሲሆን ብሄራዊ መታወቂያ ወይም የዲጂታል መታወቂያ በብዛት መሰረታዊ መታወቂያ የሚጠራባቸው ስያሜዎች ናቸው፡፡

See also  ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ መንግስትን ዘርፈዋል የተባሉት ወደ ማረሚያ ቤት ተዛወሩ

በኢትዮጵያ በአሁኑ ሰአት ተግባራዊ ለማድረግ በሙከራ ላይ የሚገኘው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት (Foundational ID) መሰረታዊ መታወቂያ የሚሰጥበት ስርዓት ነው፡፡ የዲጂታል መታወቂ ማለት ማንኛውም በሀገሪቱ ውስጥ የሚኖር ሰው ተቋሙ ወይም በተቋሙ ውክልና የተሰጠው አካል በሚያደርገው የምዝገባ ሂደት የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃዎችን በመስጠት ከተመዘገበ በኋላ ማንነቱን ለማረጋገጥ የሚሰጥ ልዩ ቁጥር(Unique Number) ነው፡፡ ይህ ልዩ ቁጥር ወይም ዲጂታል መታወቂ የሚመነጨው ከግለሰቡ የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ ዳታ በመሆኑ፣ ግለሰብን በልዩ ሁኔታ ለመለየት የሚስያስችል አስተማማኝ የመታወቂ ስርዓት ነው፡፡

ይህን የመታወቂያ ስርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እና የህግ ድጋፍ እንዲኖረው ለማስቻል በብሄራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ከተዘጋጀ በኋላ ረቂቁን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ ቁጥር 1284/2015 አድርጎ አፅድቆታል፡፡ በአዋጁ አንቀፅ 14 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው የዲጂታል መታወቂያ የአንድን ነዋሪ ማንነትን ለማስረዳት ወይም ለማረጋገጥ እንደ ህጋዊ እና በቂ ማስረጃ ተደርጎ እንደሚወሰድ እና ማንኛውም ተጠቃሚ አካል ለነዋሪው ለሚሰጠው አገልግሎት የዲጂታል መታወቂያ እንደ አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ የሚያደርግ አሠራር በሚመለከተው ተቆጣጣሪ አካል ፍቃድ መዘርጋት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም አሁን በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚደረገው ዲጂታል መታወቂያ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ተቀባይነት ያለው እና ማንነትን በማረጋገጥ ለሚሰጡ አገልግሎቶች እንደ አስገዳጅ የመታወቂያ አይነት የሚወሰድ ሲሆን፣ በዚህ መታወቂያ አገልግሎት ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው በወንጀል እንደሚጠየቅ አዋጁ አንቀፅ 21/1/ በሚከተለው መልኩ ደንግጓል፡፡

“በዚህ አዋጅ እና ይህን አዋጅ ተከትለው በሚወጡ ደንቦች እና መመሪያዎች መሠረት ስልጣን ባለው አካል የተሰጠን ዲጂታል መታወቂያን እንደ ህጋዊ መታወቂያ ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነ ወይም ማንነትን ብቻ በማረጋገጥ የሚሰጡ አገልግሎቶችን በዲጂታል መታወቂያ ለመስጠት ፍቃደኛ ያልሆነ ወይም በዚህ አዋጅ አንቀፀ 19 ላይ የተመለከተውን የመተባበር ግዴታ የተላለፈ ማንኛውም ሰው ከአስር ሺህ እስከ አንድ መቶ ሺህ ብር በሚደርስ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል”
ከላይ እንደተገለጸው ዲጂታል መታወቂያ የሚባሉው ልዩ ቁጥሩ ሲሆን፣ ይህንን መታወቂያ በካርድ መልኩ መያዝ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ተገቢውም ክፍያ በመፈፀም ከተቋሙ ወይም ተቋሙ ውክልና ከሰጠው ማንኛውም አታሚ ድርጅት የመታወቂያ ካርዱን ማግኘት የሚቻልበት ስርዓት ተዘርግቷል፡፡

  1. የአዋጁ ዓላማ

የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1284/2015 ዋና ዓላማው የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት መዘርጋት ነው፡፡ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ምንድን ነው የሚለው ሰፊ ትንታኔ የሚፈልግ ሲሆን፣ ጠቅላላ የሆነ ትርጓሜውን ግን ከዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ዓላማ ከሚለው ድንጋጌ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በመሆኑም በአዋጁ አንቀፅ 5 ላይ እንደተመለከተው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ዓላማ ነዋሪዎች በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ሲንቀሳቀሱ በቀላሉ የመታወቅ መብታቸው እንዲረጋገጥ በማድረግ ለሰብአዊ መብቶቸ አከባበር እና ለመልካም አስተዳደር መሻሻል አስተዋፅኦ ማድረግ፣ አገልግሎት ማግኘት የሚፈልጉ ግለሰቦችን በቀላሉ ለመለየት የሚያስችል የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት በመዘርጋት በአገልግሎት ሰጪ እና አገልግሎት ተቀባይ መካከል እምነት እንዲጎለብት ማድረግ፣ ሕገ-ወጥ ተግባራትን መከላከል፣ ሀገር አቀፍ የዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት በማደራጀት ሀገራዊ ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎች እና እቅዶች ሲቀረጹ እና የልማት ሥራዎች ሲከናወኑ ድግግሞሽን መቅረፍ፣ በዚህም የሀብት ብክነትን መቀነስ እና አካታችነትን ማጎልበት፣ የነዋሪዎችን የዲሞግራፊክ እና ባዮሜትሪክ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችል ሥርዓት በመዘርጋት፣ ለሌሎች መንግስታዊ እና መንግስታዊ ላልሆኑ አካላት የመታወቂያ ሥርዓት መረጃ ምንጭ ሆኖ ማገልገል እና አገልግሎት ተኮር የሆኑ የመታወቂያ ሥርዓቶች ወደ ዲጂታል መታወቂያ ሥርዓት እንዲሸጋገሩ ማጠናከር መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

  1. የዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት እና ዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት ስለሚሰበሰቡ መረጃዎች
See also  ፍርድ ቤቱ ፌዴራል ፖሊስ በሽብር ወንጀል የተከሰሱትን እነ ሌ/ጀ ፃድቃንን ይዞ እንዲያቀርብ ትእዘዝ ሰጠ

በአዋጁ አንቀፅ 7 ላይ በግልፅ እንደተመለከተው ማንኛውም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖር ሰው የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃዎችን በመስጠትና በመመዝገብ የዲጂታል መታወቂያ የማግኘት መብት አለው፡፡ ነዋሪው የዲጂታል መታወቂያ ለመውሰድ እሱነቱን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ የመታወቂያ ሰነዶች እና ሌሎች በተቋሙ ተቀባይነት ያላቸውን ሰነዶች ወይም የሰው ምስክር ማስረጃዎችን በመጠቀም በማረጋገጥ መመዝገብ ይችላል፡፡ ከላይ እንደተመለከተው ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት የሚገባ የግል መረጃ የእያንዳንዱን ተመዝጋቢ የዲሞግራፊክ መረጃ እና ባዮሜትሪክ መረጃን ያካተተ መሆን ያለበት ሲሆን፣ የዲሞግራክ መረጃ የሚባሉትም ስም ፣ የአባት ስም ፣ የአያት ስም ፣ ወይም በዚህ መልክ የተደራጀ ህጋዊ ስም ለሌለው ተመዝጋቢ ተቋሙ ህጋዊ የሆነውን ስያሜ ወይም ተመዝጋቢው በአካባቢው ማህበረሰብ የሚጠራበትን ስም፣ ዜግነት፣ የትውልድ ቀን፣ ወር እና ዓመት፣ ፆታ፣ መኖሪያ አድራሻ ሲሆኑ እንደአስፈላጊነቱ ስልክ ቁጥር፣ የኢሜይል አድራሻ እና ፖስታ አድራሻንም ሊያካትት ይችላል፡፡ የሚሰበሰቡት የባዮሜትሪክ መረጃዎች ድግሞ የአስር ጣት አሻራ፣ የሁለቱም አይኖች ብሌን እና የፊት ገፅታ ናቸው፡፡ እነዚህን የባዮሜትሪክ እና ዲሞግራፊክ መረጃዎች የሰጠ ማንኛውም ሰው የዲጂታል መታወቂያ ማግኘት ይችላል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የባዮሜትሪክ መረጃዎችን ለመስጠት የሚቸገሩ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ጣት የሌለው ሰው፣ በእርጅና እና በተለያዩ ምክንያቶች አሻራቸው የማይነበብ ሰዎች በሚኖሩበት ጊዜ እና መሰል ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ፣ በዲሞግራፊክ መረጃ ብቻ መታወቂያውን መስጠት የሚገባ ስለመሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡

  1. የዲጂታል መታወቂያ ከሌሎች መታወቂያዎች፣ የባንክ አካውንቶች እና መሰል ማንነትን ለማረጋገጥ ከሚያገለግሉ ሰነዶች ጋር የሚኖረው ግንኙነት
    የዲጂታል መታወቂያ ራሱን የቻለ መታወቂያ ቢሆንም፣ ሌሎች መታወቂያዎችን የሚያጠናክር የመታወቂያ አይነት ነው፡፡ ሁሉም ከላይ በርዕሱ ላይ የተመለከቱን ማንነትን ለማረጋገጥ የሚያገለግሉ ሰነዶች ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት እንዲገቡ የሚደርግ አሰራር ተዘርግቷል፡፡ ለምሳሌ ፕሮጀክት ፅህፈት ቤቱ ከብሄራዊ ባንክ ጋር በመተባበር ከሁሉም በሀገሪቱ ውስጥ ከሚገኙ ባንኮች ጋር ስምምነት ላይ በመድረስ፣ ሁሉም ባንኮች ደንበኞቻቸውን ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ለማስገባት ስራ ጀምረዋል፡፡ እንዲሁም ፅህፈት ቤቱ እና ገቢዎች ሚኒስቴር የመግባቢያ ስምምነት በመፈራረም ሁሉንም ግብር ከፋይ የታክስ ከፋይነት መለያ ቁጥሩን መሰረት በማድረግ ወደ ዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ለማስገባት የሚስችል ስራ ተጀምሯል፡፡ ከዚህ መገንዘብ የምንችለው የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ሌሎች መታወቂያ ስርዓቶችን እያጠናከረ የሚሄድ የመታወቂያ አይነት መሆኑን እና ራሱንም ችሎ ማናቸውንም አገልግሎት ለማግኘት የሚያስችል የመታወቂያ አይነት መሆኑን ነው፡፡
  2. የመረጃ አጠባበቅ ስርዓት
See also  የሽብር ወንጀል ተግባር በኢትዮጵያ ህግ

የዲጂታል መታወቂያ ለማግኘት የሚሰበሰቡ መረጃዎች በተለይም የባዮሜትሪክ መረጃዎች በጥንቃቄ ካልተያዙ ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ሊያጋልጡ ይችላሉ፡ ስለዚህ ለዲጂታል መታወቂያ የተሰበሰቡ መረጃዎች በጥንቃቄ መያዝ ያለባቸው በመሆኑ አዋጁ ተቋሙ የዲጂታል መታወቂያ ስርዓት የግል መረጃን በአስተማማኝነት የሚይዝ ጠንካራ የመረጃ አስተዳደር ስርዓት መዘርጋት አለበት፤ በሚል የደነገገ ሲሆን፣ አሰራርና ህግን ጠብቆ በዲጂታል መታወቂያ ስርዓት ለተሰበሰበ የማንኛውም ተመዝጋቢ ግላዊ መረጃ ያለ ተመዝጋቢው ፈቃድ ለሌላ ሰው መግለጽ ፣ ማስተላለፍም ሆነ እንዲለወጥ መፍቀድ የተከለከለ መሆኑን ህጉ በግልፅ አስቀምጧል፡፡ ይህን ክልከላ መተላለፍም በወንጀል የሚስጠይቅ ስለመሆኑ በአዋጁ አንቀጥፅ 25 ላይ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ለፍትህ ስራ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በህግ ስልጣን ለተሰጠው ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሠረት የግል መረጃው ለሚመለከተው ህጋዊ አካል ሊገለጽ ወይም ሊተላለፍ እንደሚችል የዲጂታል መታወቂያ አዋጅ ቁጥር 1284/2015 አንቀፅ 16 ተደንግጓል፡፡

በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት የተዘጋጀ

1 Comment

  1. እውነት ከውስጤ ነው ያስደሰተኝ ይህ አይነት ስርአት መዘርጋቱ!

Leave a Reply