ኦሮሚያ ዛሬ ምን አለ?

በኦሮሚያ ክልል ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ሰፊ ቁጥር ያለው ህዝብ አደባባይ በመውጣት ለጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሙሉ ድጋፍ እንደሚሰጥ በገሃድ አስታወቀ። ለውጡን ለማስቀጠል አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ” በመድመር” ስሌት እንደሚንቀሳቀሱም ይፋ አደረጉ። ሰልፉ በተለያዩ የማህበራዊ ገጾች “የጋላን መንግስት በሃይል እናስወግዳለን ” በሚል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ላይ የጥላቻ ቅስቀሳ በሚደረግበት ወቅት በመሆኑ ” ኦሮሚያ ተናገረ” አስብሏል። ሽመልስ አብዲሳ ” ነጻነት፣ እኩልነት እና ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት የኢትዮጵያ አንድነት ዋስትና ነው” ሲሉ በማህበራዊ አውዳቸው ገልጸዋል።

በተለያዩ ከተሞች የተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ በሰላም መጠናቀቁን የክልሉ ኮሙኒኬሽን ሲያስታውቅ እንዳለው ሰልፉ በሚሊዮኖች የተሳተፉበት ነው። በተለያዩ የቪዲዮ መረጃዎች እንደታየውም በትናንሽ ከተሞች ሳይቀር የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ስም በማግነን በተደረገው ሰልፍ ጎዳና የወጣው ህዝብ ቁጥሩ ከፍተኛ ነው።

በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ በስኬት መቀጠሉን በመደገፍ፣ የለውጡን መሪዎች ለበለጠ ስራ ለማነሳሳት፣ የህዝቡን አብሮነት የታየበት እንደነበር የተነገረለት ይህ የድጋፍ ሰልፍ፣ በሌሎች ክልሎችም እንደሚቀጥል ተሰምቷል።

የክልሉ መንግስት በድጋፍ ሰልፍ ለተሳተፉ በሙሉ እንዲሁም ለሰልፉ በሰላም መጠናቀቅ ሲሰሩ ለቆዩ የፀጥታ አካላት ያመሰገነው የክልሉ ኮሙኒኬሽን ጽህፈት ቤት እንዳለው መልዕክቱ ይበልጥ ሃላፊነትን የሚያሸክም፣ ለበለጠ ልማት ያለማሰለስ ለመስራት የሚያነሳሳ ነው።

ሰልፉን ካድሬዎች ያዘጋጁትና ምድር ላይ ያለውን ሃቅ የሚገልጽ እንዳልሆነ የተቹም አሉ። ሰልፉን ከደገፉት መካከል ትችቱን የተቃወሙ ” በቀጣይ ድጋፍ የሚወጡትን አክሎ መጪውን ምርጫ ከወዲሁ ውጤቱን ያመላከተ ነው። ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ይፈርደዋል” ሲሉ ተሰምተዋል።

ሮቤራ ገምቱ “ዛሬ ኦሮሚያ ለሚሰሙ ሁሉ ግልጽ መልዕክት አስተላልፏል። ይህን እያዩ የጅምላ ስድብ ላይ ጊዜ ማጥፋት ዋጋ የለውም። የሚቀይረውም ነገር የለም” ብሏል። አያይዞም ዛሬ በሰልፉ ላይ የታየውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ለማጠንከር መስራት እንደሚገባ፣ የሚያከሩትን ከሁሉም ወገን መታገል እንደሚገባ አመልክቷል።

ኦሮሚያ ላይ የድጋፍ ሰልፍ እንደሚካሄድ ሲገለጽና ሲካሄድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጎንደርና ባህር ዳር እንደሆኑ የመንግስት ዜና ማሰራጫዎች አሳይተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ዛሬ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከለውጡ ወዲህ የተመዘገቡ ለውጦችን በመደገፍ ህዝቡ ላካሔዱት የድጋፍ ሰልፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡ አቶ ሽመልስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ “ሁሉን አቀፍ ብልጽግና እናረጋግጣለን” ብለዋል፡፡ ነጻነት፣ እኩልነት እና ኅብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት የኢትዮጵያ አንድነት ዋስትና መሆናቸውን አንስተዋል፡፡

See also  በህወሃት የሽብር ቡድን አባላት ሀብቶች ላይ ተጨማሪ ጥቆማ እንዲደረግ ጥሪ ቀረበ።

የብልፅግና ፓርቲ ኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ተሰማ ለውጡን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የተደረገውን የድጋፍ ሰልፍ አስመልክተው ህዝቡን አመስግነዋል፡፡ በድጋፍ ሰልፉ በሚሊዮን የሚቆጠር የኦሮሞ ህዝብ በአንድነት በመውጣት ትላልቅ መልዕክቶችን ለአለም አስተላልፏል ብለዋል ፡፡ ህዝቡ ባካሔደው የድጋፍ ሰልፍም ለነፃነት፣ እኩልነት እና ለፍትህ የተከፈለውን መስዕዋትነት በማሰብ ከለውጡ በኃላ ለተመዘገቡ ዘርፈ ብዙ ስኬቶች እውቅና መስተቱንም አመልክተዋል።

ሰልፈኞቹ “የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል ከአመራሮቻችን ጎን ነን፣ የለውጡ መሪዎቻችን እንደ ዓይናችን እንጠብቃችኃለን፣ መጋቢት 24 የኢትዮጵያዊያን የነፃነት እና የእኩልነት ሀውልት ነው” የሚሉ መፈክሮች ሲያሰሙ ተሰምቷል።

ከበርካታ በኦነግ ስም ከሚጠሩት መካከል አንዱ ጥሪ እንዳልደረሰው ቢያስታውቅም፣ በኦሮሚያ ተወዳዳሪ ድርጅቶች አንድ የመሆን አቅጣጫ እየተከተሉ መሆኑንን ጠቅሰን መዘገባችን የሚታወስ ነው።

Leave a Reply