የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ በድል የቋጨችውን የሻዕቢያ ወረራ በስምምነት ሲቋጩ አብዛኛውን በወረራ ተያዘው የነበሩትን አካባቢዎች ለኤርትራ አሳልፎ የሚሰጥ ስምምነት አልጀርስ ላይ መፈረማቸው አይዘነጋም። ይህ ይግባኝ የሌለው ስምምነት ተጋብራዊ ሳይሆን ቢቆይም፣ የኢህአዴ ስራ አስፈጻሚ ከለውጡ በፊት ስምምነቱ ተግባራዊ እንዲሆን መስማማቱ፣ ስምምነቱንም በገሃድ ለህዝብ ማስታወቁ የሚታወስ ነው።
ከለውጡ በሁዋላ የትህነግ ታጣቂ ሃይሎች በመከላከያ ሰራዊት ላይ በፈጸሙት ጥቃት ሳቢያ የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ሻዕቢያ ሰራዊቱን አሰማርቶ ተሸንፎ የለቀቀውን አካባቢ በሙሉና እላፊ ይዟል።
በትህነግና በመንግስት በኩል ሲካሄድ የቆየውና ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ያስከተለው ጦርነት በሰላም መቋጨቱን ተከትሎ ያኮረፈርው ሻዕቢያ “ይገባኛል” ከሚለው አካባቢ አልፎ ሰፊ የኢትዮጵያን መሬት መያዙ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው። በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከትግራይ ተወካትዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ይኸው ጥያቄ ቀርቦላቸው ” ተወረረ የተባለው ቦታ በደንብ ተመርመሮ በውይይት መፍትሄ እንዲፈለግ የጋራ አጥጪ ይቋቋማል” የሚል ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።
ይህ በንዲህ እንዳለ ነው የኤርትራ ሰራዊት ከሶስት የኢትዮጵያ የትግራይ ምስራቃዊ ዞን ወረዳዎች 93 ወጣቶች አግቶ መሰወሩን የአካባቢው አስተዳዳሪዎች መናገራቸው የተሰማው። ይህም ብቻ ሳይሆን ቀደም ባሉ አካባቢዎች ወሮ ይዟል በተባለበት የኢሮብ አካባቢ መታወቂያ ማደሉንና የቀድሞውን መዋቅር ማፍረሱም ተመልክቷል።
እገታው የተፈፀመው ኢትዮጵያ በትግራይ በኩል ከኤርትራ ከምትዋሰንባቸው የዛላንበሳ ከተማ የጉሎመኻዳ እና የኢሮብ ወረዳዎች መሆኑንን የቲክቫኽ ዜና ያስረዳል።
ይህን የተገለፀው የከተማ እና የወረዳዎቹ አስተዳዳሪዎች ከኤርትራ ድንበር በ35 ኪሎ ሜትር ርቀት በምትገኘው የዓዲግራት ከተማ መጋቢት 25 ቀን 2016 ዓ.ም ከአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች (AU military attaches) ባካሄዱት ውይይት ነው።
የዛላአንበሳ ከንቲባ መምህር ብርሀነ በርሀና ፣ የጉሎመኻዳ ዋና አስተዳዳሪ ሃፍቶም ባራኺ በጋራ ከአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች በነበራቸው ቆይታ እንደገለፁት ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በኃላ :-
- – በአከባቢያቸው የተለወጠ የፀጥታ ሁኔታ አለመኖሩ ፤
– ጦርነቱ ተከትሎ የተፈጠረው ችግር እንዳልተፈታ፤
– የኤርትራ ሰራዊት የዛላአንበሳ ከተማ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ እንደሚገኝ፤
- – ከዛላኣንበሳ ከተማ መግብያ በቅርብ ርቀት ዝባን ሑፃ ተብሎ በሚጠራ አከባቢ ኬላ አቋቁሞ ፍተሻ እንደሚያካሂድ ፤
– የኤርትራ ሰራዊት ከዛላኣንበሳ ከተማ 15 ፣ በቁጥጥሩ ስር ከሚገኙ የጉሎመኻዳና የኢሮብ ወረዳዎች የተለያዩ ቀበሌዎች 78 ባጠቃላይ 93 ወጣቶች አግቶ የወሰዳቸው ወጣቶች ያሉበት ሁኔታ እንደማይታወቅ ተመልክቷል።
ከዚህ በተጨማሪ በኤርትራ ሰራዊት ቁጥጥር ስር በሚገኙ የጉሎመኻዳ እና የኢሮብ ወረዳዎች 10 ቀበሌዎች የሚኖር ህዝብ እርዳታ ጨምሮ የጤና የትምህርት እንዲሁም ሌሎች የመንግስት አገልግሎቶች እንደማያገኝ አስተዳዳሪዎቹ ለአፍሪካ ህብረት ወታደራዊ ታዛቢዎች በዝርዝር አስረድተዋል።
በስብሰባው ወቅት የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ተወካዮች መሳተፋቸውን ኢትዮጵያ ከትግራይ ምስራቃዊ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ፅህፈት ቤት አመልክቷል።
የሀገር መከላከያ ሚንስትሩ ዶክተር አብራሃም በላይ በየካቲት 2016 ዓ.ም የመጨረሻው ሳምንት ላይ በትግርኛ ቋንቋ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለመጠይቅ ፥ ” የሻብዕያ ሰራዊት ” ብለው የገለፁት የኤርትራ ጦር ከኢትዮጵያ መሬት ስለመውጣት ጉዳይ ፤
” ከፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በፊት በበርካታ የትግራይ አከባቢዎች የሻዕብያ ሃይል ገብቶ ነበር ፣ ከስምምነቱ በኋላ እንዲወጣ ተደርጓል ፣ አሁንም የተቀሩ ቦታዎች ካሉ ቦታዎቹ እና ቀበሌዎች ከፌደራልና ከትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር የተውጣጣ ቡድን በዝርዝር አጥንቶ እንዲያቀርብና መፍትሄ እንዲሰጠው እየሰራን ነው ሁሉም ልክና መስመር ይይዛል ” ማለታቸውን ቲክቫህ በዘገባው አስታውሷል።
በኢትዮጵያ ላይ በተዘዋዋሪና በግልጽ ሴራ እያደራ ያለው የፕሬዚዳንት ኢሳያስ አስተዳደር እጁን እንዲሰበስብ ለመንግስት ቅርብ ናቸው የሚባሉ እየወተወቱ ነው። እነዚህ ክፍሎች እንደሚሉት ከሆነ ኢትዮጵያ የታጋሽነት ፖለቲካ አቋሟን በሻዕቢያ አማካይነት ልትቀይር እንደምትችልና ጠላቶቿ እንደሚያደርጉት ” እሾህን በሾህ” የሚል አካሄድ ልተከተል እንደምትችል ጥቆማ እየሰጡ ነው።
የኢትዮጵያን ውድቀትና መበታተን እያስለ ከሚሰራው የግብጽ መንግስት ጋር በይፋ ያበሩት ኢሳያስ አፉወርቂ ይህ ተግባራቸው ኢትዮጵያ ላይ በይፋ ጦርነት እንደማውጅ እንደሚቆጠር የሚገልጹ እየበዙ ነው። ሻዕቢያ እስካለ ድረስ ኢትዮጵያ ስለሟ ሊጠበቅ እንደማይችል ከድምዳሜ የደረሱ አካላት በግልጽ ኢትዮጵያ ለህልውናዋ ስትል አንድ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባት እየጠየቁ ነው። መንግስት ዝምታን ቢመርጥም የሻዕቢያ ጉዳይ ላይ በጥንቃቄ እየሰራ መሆኑንን የሚጠቁሙ ” ሻዕቢያ የአማራ ክልልን ጦርነት የሚያቀጣጥለውና ድጋፍ የሚያደርገው ኢትዮጵያ ሰላም ከሆነች አትለቀኝም ከሚል ስጋት በመነሳት ነው” ሲሉ አማራ ክልል ላይ የሚደረገውን የውክልና ጦርነት ምክንያት ያብራራሉ።