በዚሁ ጥቃት ሳቢያ ዕቃዎችን ከአፍሪካ ወደ እስያ እና አውሮፓ ለማጓጓዝ እስከ 20 ቀን እንደሚፈጅ እና ይህም የዓለም የንግድ ልውውጥ ማስተጓጎሉ ማስተጓጎሉ ተመልክቷል።
በዚሁ የቀይ ባሕር የፀጥታ ችግር ምክንያት የአውሮፓ ሕብረት ሀገራት የወጪ እና ገቢ ንግዳቸው በ2 በመቶ እና በ3 ነጥብ 1 በመቶ መቀነሱን ተመልክቷል። በጥናቱ ባይካተትም አውሮፓ የሸቀጦች ዋጋ አሻቅቧል። አቅርቦቱም ያነስበትና እጥረት የተፈጠረባቸው አገራት አሉ። ምሬቱም ከየአቅጣጫው እየተሰማ ነው።
በተመሳሳይ የአሜሪካ የወጪ ንግድ በ1 ነጥብ 5 በመቶ እንዲሁም የገቢ ንግዷ በ1 በመቶ መቀኑሱን ጠቅሶ አርቲ ዘግቧል፡፡
የሁቲ አማፂያን ባለፈው ወር በቀይ ባሕር ሲጓዙ በነበሩ ንብረትነታቸው የአሜሪካ እና ሌሎች ሀገራት በሆኑ መርከቦች ላይ ጥቃት መፈጸማቸው ይታወሳል፡፡ በአንጻሩ የቀይ ባሕርን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚል አሜሪካ እና ብሪታኒያ በየመን የሁቲ አማፂያን ይዞታዎች ናቸው ባሏቸው 16 ዒላማዎች ላይ ድብደባ መፈፀማቸው ይታወቃል፡፡
ይህ በንዲህ እንዳለ እንደ አዲስ አሁን ብቅ ያሉ መረጃዎች አሉ። በስደት አውሮፓ የሚኖሩ የሶማሌ ዜጎች እንደሚሉት ኢትዮጵያ ወታደሮቿን ከሶማሊያ ልታስወጣ ትችላለች። ከኤርትራ ጋር በመሻረክ የግብጽን አጀንዳ እያስፈጸመ ያለው የሶማሊያ መንግስት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ያደረገችውን አዲስ ስምምነት ተከትሎ የያዘው አቋም ለአልሸባብ መልካም አጋጣሚ ሊሆንለት እንደሚችል ነው ስጋታቸውን የሚገልጹት ክፍሎች የሚናገሩት።
ከሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ጋር የሚሰራ አራት ሺህ፣ ለብቻው ያለ ሃያ ሺህ ሰራዊት ያሰማራችው ኢትዮጵያ ሃይሏን ከሳበች አልሸባብ ሶማሊያን ለመቆጣጠር ብዙም እንደማይቸገር የሚገልጹት ወገኖች ስጋት እውን ከሆነ የቀይ ባህር መግቢያ ጉሮሮ በአልሸባብና ሁቱ እጅ ወደቀ እንደማለት ነው።
ኢትዮጵያ ጦሯን ከሶማሊያ ስለማስወጣቷ በገሃድ የተባለ ነገር የለም። ኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤት ለመሆን የጀመረችውን ፍትሃዊና በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሰረተ እንቅስቃሴ ስለመግፋቷ፣ ስምምነቱን ማወቅ ያለባቸው ተቋማትና አገራት አስቀድመው እንዲረዱት መደረጉ ከመግለጽ ውጭ ወታደር ስለማንቀሳቀስ የተሰማ ዜና የለም። ኢትዮጵያ ለሶማሌ ሰላም የልጆቿን ህይወት የገበረችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሶማሌያ ተወላጆችን ያለ አንዳች ስጋት አቅፋ የምታኖር አገር እንደሆነች የሚረዱ ጉዳዩ በሰላማዊ ውይይት ሊታይ እንደሚገባው እየወተወቱ ነው።
“አንድም የሶማሊያ ስደተኛ የማታስተናግድ፣ ድጋፍ የማታደርግና አልሸባብን ሲያደራጅና ሲያስታጥቅ ከኖረው ኢሳያስ አፉወርቂ ጋር አብሮ ኢትዮጵያን ማስቀየም ከሶማሌ መሪ አይጠበቅም” ሲሉ ስጋት የገባቸውን ነገሮችን በእርጋታ የሚያዩት ወገኖች ገልጸዋል። “አንድ ሶማሊያን እንፈልጋለን። ያ ደግሞ በሶማሌ ላንድም ስምምነት ሊሆን የሚችል ነው። አሁን የተያዘው መነገድ እነሱንም የበለጠ ስለመለየት እንዲያስቡ የሚያደርግ ነው” ሲሉ የተናገሩ የሞቃዲሾ ነዋሪ የነበሩና አሁን በስደት አውሮፓ የሚገኙ ናቸው። እሳቸው እንዳሉት ስደት፣ ረሃብ፣ ጦርነት የተፈራረቀበት ህዝብ የሚመሩ መሪዎች ፉከራ አቁመው በጠረጲዛ ዙሪያ ሊወይዩ ይገባል። ከዚያ ውጭ ያለው አካሄድ ሌሎችን ከማስደሰት ውጭ ለሶማሌያ ህዝብ አንዳችም ጥቅም እንደሌለው፣ ይልቁኑም በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚሆን ነው ያመለከቱት።
ከቀናት በፊት የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የሁቲ አማጺያን በቀይ ባህር የሚፈፅሙትን ጥቃት እንዲያቆሙ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ አፅድቋል፡፡ ይሁን እንጂ አማጽያኑ የሚሰሙ አልሆነም።
በዩክሬን ስም ዓለም ከሩሲያን ጋር በገባው ጦርነት ሳቢያ የዓለም የንግድ ስርዓትንና መሰረታዊ ፍጆታ ማዛባቱ የፈጠረው ቀውስ እንዴት እንደሚገታ መላው በጠፋበት ወቅት ላይ ሃማስ የጀመረው ጦርነት መዘዙ እየሰፋ ነው። እስራኤል በሃማስ ላይ እየወሰደች ያለውን እጅግ የከፋ የተባለ፣ መላው የጋዛን ነዋሪዎች መኖሪያ አልባ ያደረገና ሜዳ ላይ ያስቀረ፣ ለብዙ ሺዎች ሞትና ጉዳት ምክንያት የሆነውን ይህ ጦርነት ተከትሎ የሁቲ አማጺያን ጥቃት መጀመራቸው ይታወሳል።
እስራኤል ” በምንም ዓይነት” ስትል ድብደባዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል ማሳሰቧን ተከትሎ ዓለም ላይ ጫና ለመፍጠር ሁቱዎች ሮኬት በማስወንጨፍ የንግድ መርከቦች ላይ ጉዳት በማድረሳቸው የቀይ ባህር የንግድ እንቅስቃሴ ላይ እክል ፈጥሯል። ንግድንም አዛብቷል። ጭራሹኑ ወደ ቀይ ባህር ድርሽ አንልም ያሉም አሉ።
በዚሁ ሁሉ ስጋት ለታጀበው የጸጥታው ምክር ቤት አማፂያኑ ጥቃት እንዲያቆሙ የሚጠይቀው የውሳኔ ሃሳብ በጃፓን እና አሜሪካ ቀርቦ በ11 ድምፅ ያለምንም ተቃውሞ፣ በአራት ድምፅ ተዓቅቦ ፀድቋል፡፡
በተጨማሪም በፀጥታው ምክር ቤት የሁቲ አማጽያንን ትደግፋለች የተባለችው ኢራን በምክር ቤቱ እንድትወገዝ ተጠይቋል፡፡የውሳኔ ሃሳቡ የሁቲ አማጺያን ከውሳኔው ቀን በፊት በአሜሪካ መርከቦች ላይ የፈፀሙትን ከበድ ያለ ጥቃት ተከትሎ የቀረበ ሲሆን ምክር ቤቱ ጥቃቱ የዓለም የንግድና የመርከቦችን እንቅስቃሴን የሚያደናቅፍና የሚገታ ነው ሲል አውግዞታል፡፡
በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው የሁቲ አማፂያን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እውቅና ከነበረው የየመን መንግስት ጋር የእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ የገቡ ሲሆን ሰሜናዊ የመንን ተቆጣጥረው ይገኛሉ፡፡
አማፂያኑ እስራኤል በጋዛ ላይ የምትፈፅመውን የአየር ጥቃት ተከትሎ በቀይ ባህር ለእስራኤል ድጋፍ ሰጭ ናቸው ባሏቸው የአሜሪካ እና የሌሎች ሀገራት መርከቦች ላይ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈፀሙ ይገኛሉ፡፡
ጥቃቱን ለመከላከል እና የቀይ ባህር ደህንነትን ለመጠበቅ አሜሪካ መራሽ ጥምረት ሀይል የተቋቋመ ቢሆንም የአማፂያኑ ጥቃት ተባብሶ መቀጠሉን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
ዘገባው ከተለያዩ ሚዲያዎች የተሰባሰበ ነው