በማእከላዊ ጎንደር ዞን ጭልጋና አካባቢው በጸረ-ሰላም ሃይሎች የተፈጠረውን የሰላም መደፍረስ ለማረጋጋት ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን የኮማንድ ፖስቱ አመራሮች አስታወቁ፡፡የኮማንድ ፖስቱ አመራሮች ዛሬ በጎንደር ከተማ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ ከዛሬ ጀምሮ ከጎንደር መተማ በሚወስደው ዋና መንገድ በ10 ኪሎ ሜትር ርቀት ግራና ቀኝ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ ክልከላ ተጥሏል፡፡

የኮማንድ ፖስቱ አባልና የ33ኛ ክፍለ ጦር አመራር የሆኑት ሻለቃ ከተማው ብናልፈው እንደገለጹት በጭልጋና አካባቢው ጸረ-ሰላም ሃይሎች በፈጠሩት ግጭት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡ኮማንድ ፖስቱ የአካባቢውን ሰላም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ህግ የማስከበር እርምጃዎችን ከመውሰድ ጀምሮ ተስተጓጉሎ የቆየውን የጎንደር መተማ መንገድ ለማስከፈት በዛሬው እለት እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ህግ የማስከበር ተልእኮ ከተሰጣቸው አካላት ውጪ በአካባቢው ከወረዳ ወረዳ እንዲሁም ከቀበሌ ቀበሌ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ የተከለከ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“የአካባቢውንና የህዝቡን ሰላም በማደፍረስ በዜጎች ላይ ጉዳት እንዲደርስ በትጥቅ የተደገፈ ትንኮሳ የፈጸሙትን ጸረ-ሰላም ሃይሎች ለህግ ለማቅረብም ኮማንድ ፖስቱ ተልእኮ ተሰጥቶት ወደ ስራ ገብቷል” ብለዋል፡፡

“በጭልጋና አካባቢው በአሁኑ ወቅት በህዝቡና በጸጥታ መዋቅሩ የጋራ ጥረት አንጸራዊ ሰላም ለማስፈን ተችሏል” ያሉት ሻለቃ ከተማው የህዝቡን በሰላም ወጥቶ የመግባት ደህንነት ይበልጥ ለማረጋገጥ ኮማንድ ፖስቱ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡የማእከላዊ ጎንደር ዞን ፖሊስ መምሪያ ሃላፊ ኮማንደር እንየው ዘውዴ በበኩላቸው በጸረ-ሰላም ሃይሎች ትንኮሳ በተፈጠረ ግጭት የደረሰውን ሰብአዊ ጉዳት የሚያጣራ ቡድን ከፌዴራልና ከክልል ተልኮ በዛሬው እለት ወደ አካባቢው መድረሱን ተናግረዋል፡፡

ህዝቡ የሰላሙ ባለቤት እራሱ መሆኑን በሚገባ በመገንዘብ የጥፋት ተልአኮ ተቀብለው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎችን በማጋለጥ ለህግ በማቅረብ በኩል ከኮማንድ ፖስቱ ጋር ተቀናጅቶ እንዲንቀሳቀስ አሳስበዋል፡፡በጭልጋና አካባቢው የተቋቋመው ኮማንድ ፖስት ከፌደራል መከላከያ ሰራዊት ከፌደራል ፖሊስና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ጽህፈት ቤት እንዲሁም ከአማራ ክልል ልዩ ሃይል ከዞኑ ፖሊስና የካቢኔ አባላት የተውጣጣ ነው፡፡በጭልጋና አካባቢው ከሚያዚያ 5 ቀን 2013 ዓ/ም ጀምሮ ተፈጥሮ በነበረው የሰላም መደፍረስ የሕዝቡ የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ተገድቦ እንደነበርም በኮማንድ ፖሰቱ መግለጫ ተመልክቷል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡Leave a Reply