የመርዛማ ጋዝ ጦር መሳሪያን መጠቀም እልቂቱንና ጉዳቱን ወራሪ ቅኝ ገዥዎች በጀግኖች አያት ቅደመ አያቶቻችን ላይ በፈፀሙት ጥቃት አሳምረን እናውቀዋለን፤ ሲሉ የመከላከያ ህዝብ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮ/ል ጌትነት አዳነ አስታወቁ።

ግንቦት 15/2013 ዓ.ም በእንግሊዝ እየታተመ በሚወጣ “ቴሌግራፍ” ጋዜጣ ላይ “ዊል ብራውን” እና “ሉሲ ካሳ” የተባሉ በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከወር በፊት ሚያዚያ 12/2013 ዓ.ም ተፈፀመ ብለው የዘገቡት የመርዛማ ጋዝ ጥቃት ሊሆን ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል ነው ብለዋል ኮ/ል ጌትነት ፡፡

ውሸት የማያልቅበት አሸባሪው ህወሃት አሁንም በሃሰት ማደናገሩን ቢቀጥልም ፣ ከወር በፊት ግን በተለየ ውሸት ይፈበረክ እንደነበር ብዙ ማሳያዋች እንዳሉ አስረድተዋል። ጥቂቶቹን ለማስታወስ ያህል “ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የትግራይ ህዝብን እየጨፈጨፈ ነው ፣ ሴቶች ተደፈሩ ፣ ሬሳ ገደል አስገቡ ፣ እርዳታ ተከለከለ ፣ ገበሬው እርሻ እንዳያርስ ተደረገ ፣ ንብረቱ ወደመና ተዘረፈ አልፎም የእርዳታ ድርጅት ሰራተኞች ታገቱና ተገደሉ ” እያሉ ራሳቸው የፈፅሙትን ድርጊት አስመስለው በመቅረፅ ጭምር ሲያሰራጩ ቆይተዋል ብለዋል።

“ጅብ ከማያውቁት ሃገር ሄዶ አጎዛ አጥፉልኝ” አለ እንደተባለው ፣ 27 ዓመት የኢትዮጵያ ህዝብን ሲያታልሉበት የነበረው ፕሮፖጋንዳ በሃገር ውስጥ ሲጋለጥና ሲከሽፍ ፤ ለማያውቁት ፣ ቢያውቁትም በጥልቀት ላልተረዱት ወይም ለተገዙት “ጅቡ የተነጠፈለትን አጎዛ እስኪበላ ድረስ” እንግዳ ብለው እነሱ ያስተናግዱት እንጂ እኛ ከበቂ በላይ እናውቀዋለን ብለዋል።

ይህን አይነት የበሬ ወለደ ውሸት የሚያስተናግዱ ሚዲያዎችና ግለሰቦች አንድም ለቆየ ዓላማቸው ፤ በሌላም ኢትዮጵያ በተዘረፈችው ዶላር የተገዙ ነጭ ሸብር ፈጣሪዎች እንደሆኑ አስረድተዋል ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ግን ፣ የውጭ ወራሪዎች በቀደምት አያት ቅድመ አያቶቻችን ላይ ያውም በትግራይ የሃገራችን ክፍል የተፈፀመውን ግፍና መከራ ጠንቅቀን ስለምናውቅ ፣ እንኳን በዜጎቻችን በማንኛውም ፍጡር ላይ መጠቀም እንደማንችል ህጉ ብቻ ሳይሆን ሞራላችን እንደማይፈቅድ ሊታወቅ ይገባል ብለዋል ።

ኢትዮጵያ ሃገራችን የጅምላ ጨራሽ ጦር መሳሪያዎችን ያለመጠቀምና ያለማስተላለፍ አለም አቀፍ ስምምነትን የፈረመች እና ያፀደቀች ቀዳሚ ሃገር ነች ። በወራሪዎችም የጥቃቱ ሰለባ እንደነበርን የወጋ ቢረሳ… የተወጋ እንዲህ ሲነካካ ያስታውሳል ነው ያሉት ።

የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ እንደተናገሩት ፣ በአያት ቅደመ አያቶቻችሁ መርዛማ ጋዝ ያልተንበረከኩ ወላጆቻችን ተተኪ ልጆች ነን። አሁንም በመርዛማ ወሬያችሁ ልታንበረክኩን አትችሉም። ይህንንም ታሪክ እንደ አደዋው ድል ዳግም አደዋ ተብሎ እንደሚወሳ እርግጠኞች ነን።

የአሁኑ መርዛማ ጋዝ ፣ የውጭው ወሬና ጫና መሆኑ ታውቆ ፤ በአንዳንድ ቅጥረኛ ሚዲያ የሚሰራጭ ዘመቻን በተገቢው ልክ ስለምንረዳ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንደ ቀደሙት አያት ቅደመ አያቶቻችን ጠብቀን እኛም ለመጭው ትውልድ ጀግንነትን እናወርሳለን ብለዋል ኮ/ል ጌትነት አዳነ።

ፎቶግራፍ ተሰማ ኡርጌሳ

Leave a Reply