ከ40 ሺህ በላይ የጸጥታ አካላት በአዲስ አበባ መሰማራታቸው ታወቀ

“የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ሰላማዊ ሂደቱን ጠብቆ እየተካሄደ ነው” -የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል

የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባስቀመጠው አቅድ መሰረት የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ሰላማዊ ሂደቱን ጠብቆ እየተካሄደ መሆኑን የጋራ ግብረ ኃይሉ እሰተባባሪ ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለጉባኤው ሰላማዊነት እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ አስተዋጽኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ የጋራ ግብረ-ኃይሉ ጥሪ አቅርቧል።

የአፍሪካ ህብረት 40ኛው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ ባለፉት ሁለት ቀናት ሲካሂድ የቆየ ሲሆን፤ በነገው እለት ደግሞ 35ኛው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ ይጀመራል፡፡

በጉባኤው የሚሳተፉ በርካታ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ወደ አዲስ አበባ ገብተዋል፤ ቀሪዎቹም በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡

መንግስት ጉባኤውን በሰላም ለማካሄድ ቀደም ብሎ ከኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት፣ የሪፐብሊካን ጥበቃ፣ ፌዴራል ፖሊስ፣ ብሔራዊ የመረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ የአዲስ አበባ ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስን ያካተተ ብሔራዊ የጸጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ-ኃይል አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ይታወቃል።

የግብረ-ኃይሉ አስተባባሪና የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ እስካሁን ባለው ሂደት ጉባኤው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ያለምንም እንከን በሰላም እየተካሄደ ነው፡፡

የህብረቱ 40ኛው የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ጉባኤ በሰላም መጠናቀቁን ያነሱት የጋራ ግብረ ኃይሉ አስተባባሪ፤ የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች በ35ኛው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ በሰላም ወደ አዲስ አበባ እየገቡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ለጉባኤው ሰላማዊነት ከ40 ሺህ በላይ የጸጥታ አካላት በአዲስ አበባ መሰማራታቸውንም ነው የተናገሩት፡፡

የጋራ ግብረ-ኃይሉ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ አገልግሎት ላይ ያልዋሉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ጉባኤው በሰላም እንዲካሄድ ቀን ከሌት እየሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡

የጋራ ግብረ ኃይሉ በቦሌ ዓለም ዓቀፍ አየር ማረፊያና በአፍሪካ ህብረት ቅጥር ግቢ ውስጥ ጊዜያዊ ቢሮ ከፍቶ የጸጥታና ደህንነት ስራዎችን እያከናወነ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

መሪዎቹ ባረፉባቸውና በሚያርፉባቸው አካባቢዎችም የተጠናከረ ጥበቃ እየተከናወነ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

ጉባኤው በሰላም እንዲጠናቀቅ የሚያስችሉ ሁሉም የጸጥታ ጉዳዮች በጋራ ግብረ-ኃይሉ እቅድ መሰረት በጥሩ ሁኔታ እየሄዱ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ከጸጥታ መዋቅሩ ጎን በመቆም ለጉባኤው ሰለማዊነት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ጠቅሰው፤ ነዋሪዎቹ ይህንኑ ተግባር አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡

Ena

You may also like...

Leave a Reply