ህክምና የሚሻው የአሜሪካ ፖሊሲ

የዓለም መንግሥታት ማኅበር (League of Nations) በኋላም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ በታሪኳ በአሜሪካና በአጋሮቿ ክህደት ሲፈጸምባት የአሁኑ የመጀመሪያዋ እንዳልሆነ ምሁራንና የሰነድ ማስረጃዎች ያሳያሉ።

ኢትዮጵያና አሜሪካ ዘመናት የተሻገረ ታሪካዊ ወዳጅነት እንዳላቸው በማሳያዎች አስደግፈው ለንባብ ያበቁት በቴክሳስ የቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ዴንተን ኮሊንስ ናቸው።

በቅርቡ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ኢትዮጵያን ላይ ተጨማሪ ማእቀብ መጣል የሚያስችል አስተዳደረዊ መመሪያ (Executive Order) መፈረም በአገራቱ መካከል የግንኙነት መሻከር እንዲያቆጠቁጥ የሚያደርግ ማሳያ ነው ብለውታል።

የባይደን አስተዳደር የኢትዮጵያን መንግሥት ጨምሮ በትግራይ ቀውስ ተሳትፈዋል በሚላቸው ላይ ማዕቀብ መጣል የሚያስችለውን መመሪያ ፕሬዝዳንቱ በፊርማቸው ማጽደቃቸው የሚታወስ ነው።

ይህ ደግሞ ከ1903 እኤአ አንስቶ የዘለቀውን የኢትዮጵያና አሜሪካ ታሪካዊ አጋርነት ላይ ቀዝቃዛ ውኃ የመቸለስ ያህል ነው ብለውታል። ለዚህም Food Aid as a Weapon in Ethiopia, the Death of US Diplomacy and the Power of Brain Washing for State Destruction በሚል ርዕስ ውሳኔውን ለመሞገት ብዕር ለማንሳት እንደተገደዱ ነው የሚገልጹት።

አሜሪካ ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ በተሳሳተ የውጭ ፖሊሲዋ ምክንያት ኢትዮጵያንና ፈረንሣይን የመሳሰሉ ቁልፍ የዘመናት አጋሮቿን ማጣቷን ፕሮፌሰር ዴንተን ኮሊንስ ያስረዳሉ። የባይደን አስተዳደር ውሳኔ ሚዛናዊነት የጎደለው ከመሆኑ ባለፈ ከአሸባሪው ህወሓት ይልቅ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ዴሞክራሲያዊ በሆነ ምርጫ በተመረጠው ኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያነጣጠር ሲሉም ተችተውታል።

ፕሮፌሰሩ ባለፉት ሁለት ቀናት ለንባብ ባበቁት ጽሁፋቸው መመሪያው  በወቅቱ የእንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰር ሣሙኤል ሆሬ እና በፈረንሣዩ አቻቸው ፔር ላቫል ኢትዮጵያን ከፋፍሎ ለፋሽስቱ ሙሶሊኒ ለእርድ አመቻችተው ካቀረቡበት ውሳኔ ጋር አመሳስለውታል። ውሳኔው በአሸባሪነት ለተፈረጀውና ዘራፊ ለሆነው የህወሓት ቡድን የሞራል ልዕልና ለመስጠት የዳዳው ከመሆኑ አልፎ ቀውሱና የዜጎች ሰቆቃ በአጭሩ እንዳይቋጭ የሚያደርግ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።

ፕሮፌሰሩ እንደሚሉት የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካን ለሚከታተል ማንኛውም ሰው ህወሓት በዘረኝነቱ ከአፓርታይድ በጭካኔው ደግሞ የዘመኑ ናዚ እንደሆነም አስረድተዋል። ጸሃፊው ራሷን የዴሞክራሲ ሥርዓት ጠበቃ አድርጋ የምታቀርበው አሜሪካ በህጋዊ መንገድ ለተመረጠው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ አስተዳደር ተገቢውን እውቅና ከመስጠት ይልቅ ከዓመታት በፊት ህወሓት አድርጌዋለሁ ያለውን ምርጫ በማድነቅ ኢትዮጵያውያን ለዴሞክራሲ ባላቸው ጉጉት ላይ በስላቅ ማፌዟን ያወሳሉ። የዚህ ስላቅ ተዋናይትም ሱዛን ራይዝ እንደሆኑ በመጥቀስ ጭምር። አሁን ደግሞ የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት ጉዳይ ያሳስበኛል በሚል ሰንካላ ምክንያት አሜሪካ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቷ ኃላፊነት የጎደለው ተግባር ነው ሲሉ ኮንነውታል። 

 የከሱና የተጎሳቆሉ ህፃናትና ሴቶችን ምስል ለዓለም በማሳየት “እርዳታ” በሚል ስም የምትለግሰው ምግብ እነማን እንደሚጠቀሙበት አሜሪካ አሳምራ ታውቃለች ያሉት ጸሃፊው ህወሃት መንግሥት እያለ ጭምር እርዳታውን ምን ሲያደርገው እንደነበር ከአሜሪካ ያልተሰወረ የአደባባይ ምስጢር ነው ብለውታል።

እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መጀመሪያ ላይ የምግብ እርዳታ ሥርጭትን ሰበብ ያደረገ የበርካታ ቢሊዮን ዶላር ጥናት በሚችጋን ዩኒቨርሲቲ በግብርና ምጣኔ ሃብት ትምህርት ክፍል፣ በወቅቱ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ልማትና ትብብር ሚኒስቴርና በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት አማካይነት መካሄዱን ፕሮፌሰሩ ያነሳሉ። ወደ ኢትዮጵያ ከሚላከው እርዳታ በአብዛኛው ምናልባትም በብዙ እጥፍ የሚበልጠው ወደ ትግራይ ክልል ይላክ እንደነበር የጥናቱን ግኝት ዋቢ አድርገው ያስረዳሉ።

እንዲያም ሆኖ የእርዳታው መዳረሻዎችን ለማወቅ የሚደረጉ ጥናቶች ህወሓትንም ሆነ ለጋሽ ተቋማትን የሚያስቆጣ እንደነበርም ጠቅሰዋል።

አጥኚዎቹም ከኢትዮጵያ እንዲባረሩና የአሜሪካውያን ግብር ከፋዮች በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ገንዘብም የውሃ ሽታ ሆኖ እንዲቀር ሲደረግ መቆየቱን በማጣቀሻ አሳይተዋል። አንዳንድ ጥናቶች ላይ አጠያያቂ ውጤት ሲገኝም መረጃው እንዲሰረዝ ተደርጎ በዚህ ጥናት ያልተካተቱ ጉዳዮች በሚል ሃረግ እውነታውን ማድበስበስ የተለመደ ተግባር እንደሆነም ገልጸዋል።

የአሸባሪውን ህወሓት ድብቅ ባህሪ ካለመረዳት አሊያም ለመረዳት ካለመፈለግ የተነሳ የዘር ማጥፋት እያለ የሚያላዝነውን ጩኸት ያለጥያቄ ወስዶ በተገኙት የሚዲያ አውታሮች ሁሉ ማስተጋባትና አብሮ መጮህ በአንዳንድ የትግራይ ዳያስፖራ አባላት ዘንድ የተለመደ የማደናገሪያ ስልት መሆኑን ግልጽ አድርገዋል።

 “ሁለት የአሃዝ መረጃዎች ጉዳዩን በግልጽ ይናገራሉ፣ የመጀመሪያው ህወሓት ሲመራው የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት ከአሜሪካ የተቀበለው የገንዘብ ድጋፍ 30 ቢሊዮን ዶላር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ህወሓት የሚመራት የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከሚመሯት አገር ያሸሹት ገንዘብ 30 ቢሊየን ዶላር ነው”ሲል ታዋቂው የሃብት ጉዳዮች መጽሄት ፎርብስ Ethiopia’s Cruel Con Game በሚል ርዕስ ከዓመታት በፊት ማስነበቡን ያወሳሉ።

ህውሓት መራሹ መንግሥት በእርዳታ ስም ያገኘውን ከፍተኛ ገንዘብ አሁን ላይ የአሜሪካ ፖሊሲ ላይ ጫና ለመፍጠር እያዋለው እንደሚገኝ አመልክተዋል። ገንዘቡ በትክል ስራ ላይ ቢውል የሚሊዮኖችን ህይወት ሊለውጥ ይችል እንደነበርም በቁጭት ተናግረዋል። እናም ግብር ከፋዩ የአሜሪካ ህዝብ በእርዳታ ስም የሚለገሰውን አንጡራ ሃብቱን የት እንደደረሰ የመጠየቂያው ጊዜ አሁን ነው ይላሉ።

በአፍሪካ አገራት ባልተለመደ መልኩ የወርቅ መሸጫ ሱቆች የተለየ ጥበቃ በማይደረግባት ኢትዮጵያ ለ27 ዓመታት የዘለቀው የህወሓት አገዛዝ ሌብነትን ነውር አልባ የእለት ተእለት ተግባር እንዲሆን አድርጎታል ሲሉም ህወሓትን ይከሳሉ። በእርዳታ እህል የጀመረው ሌብነት ወደ ካፒታል ፕሮጀክቶችና የመሰረተ ልማት አውታሮች በመሻገር አገሪቱ ወደለየላት የዘራፊ ባለስልጣናትና ኮንትራክተሮች መፈንጫ አገር ቀይሯታል ባይ ናቸው ፕሮፌሰሩ።

በህወሓት አገዛዝ ስር “የልማታዊ መንግስት” አስተዳደር መርህን በመከተል ከአፍሪካ ከፍ ያለ አገራዊ ጠቅላላ የምርት ዕድገትን አምጥታለች የምትባለው ኢትዮጵያ ተገኘ በተባለው ዕድገትና የሃብት ክፍፍል ረገድ ሚዛናዊነት የጎደለው እንደነበር ብዙዎቹ የሚያነሱት ጉዳይ ነው። የትግራይ ክልል አጎራባች የሆነው የአማራ ክልል ለዚህ ጥሩ ማሳያ እንደሆነም ፕሮፌሰር ዴልተን ኮሊንስ ያነሳሉ። ክልሉ ካለው ስፋትና የህዝብ ብዛት ጋር የማይጣጣም የመሰረተ ልማት እንደሚታይበት በመግለጽ ጭምር።  

ህሓሃት የምግብ እርዳታዎችን አቅጣጫ አስቀይሮ መቸበቸብና ረብጣ ገንዘብ ማጋበስ ጥርሱን የነቀለበት ተግባር መሆኑን አረጋዊ በርሄና ገብረመድህን አርአያን የመሳሰሉ የድርጅቱ ቀደምት መሪዎችና የህወሓት ተከፋዩ ጋዜጠኛ ማርቲን ፕላውት ህያው ምስክሮች ናቸው ይላሉ።

ህወሓት የጦር መሳሪያን ከሱዳን ለማሾለክ ያቋቋመው የትግራይ ተራድኦ ድርጅት የተረጂዎችን ቁጥር በማብዛት፣ ጦርነቱን ያልደገፉትን እርዳታ ከልክሎ በማስራብ የተገኘውን እርዳታም ገበያ አፈላልጎ በመሸጥ የምግብ እርዳታን ለጦር መሣሪያ መሸመቻነት በማዋል ይቅር የማይባል ወንጀል መፈጸሙን ምሁሩ አስረድተዋል።

 ኢትዮጵያውያን ተሰባጥረውና በጋብቻም ተሳስረው መኖራቸው ነውርና ወንጀል ሲያደርግ የቆየው ህወሓት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ ዘላቂ ጥቅሙን ለማስከበርና ሁሉንም ከጫማው ስር ለማድረግ በአገሪቱ ባሉ ከ80 በላይ ብሄሮች መካከል ያሉ ጥቃቅን ልዩነቶች እንዲከፉና እንዲሰፉ ያለመታከት በመስራቱ በድርጅቱ አስተምህሮ ተቀርጾ ያደገው ትውልድ ለማስተካከል ከባድ ትግልና ረጅም ጊዜ እንደሚጠይቅም ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት ከዓመት በፊት ባዘጋጀው ድብቅ ሰነድ ከቻለ ኢትዮጵያን ራሱ በሚፈልገው መንገድ መግዛት፣ ካልተቻለ በራሱ አምሳል ያዘጋጃቸውን ምስለኔዎች ማስቀመጥ ያም ካልሆነ ጦርነት በመክፈት ድርድር በማስጀመር ስልጣን የመጋራት እቅድ እንደነበረው በመረጃ አስደግፈው አብራርተዋል።

 ከሶስቱ ሃሳቦች አንዱም ካልተሳካ ኢትዮጵያን ከዓለም ካርታ ላይ ማጥፋት የሚያስችል ተግባራትን ከአገር ውስጥና ከውጭ ጠላቶች ጋር ተባብሮ እየተገበረ መሆኑን የአሁኑ ቀውስ ማረጋገጫ ነው ብለውታል።

ህወሓት ባለፈው ዓመት ጥቅምት ላይ በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው የክህደት ጥቃትና ብዙዎችን የፈጀበትን ድርጊት ለአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት መነሻ ከሆነው የፎርት ሳምተር የአየርና የመድፍ ድብደባ ጋር የሚመሳሰል ነው ብለውታል። የፎርት ሳምተር ጥቃት እ.ኤ.አ በ1861 በደቡብ ካሮላይና ቻርልስተን አቅራቢያ የተፈጸምና በኋላም ለዓመታት ለዘለቀው የአሜሪካ የእርስ በርስ ጦርነት መነሻ ሆኗል።

ልክ እንደ ፎርት ሳምተር ጥቃት ሁሉ ህውሓት በለኮሰው ጥፋት ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበት የሕግ ማስገበር ኦፕሬሽን እንደ ኒው ዮርክ ታይምስ የመሳሰሉ የአሜሪካ ግዙፍ የሚዲያ አውታሮች ሀቁን አዛብተው ሲዘግቡት መስተዋሉ ሙያዊ ሃላፊነት የጎደለው ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል። የሀሰት ትርክቶች ለጊዜው ዕውነታውን ሊያንሻፍፉ ይችሉ እንደሆን ነው እንጂ ታሪክን ሊቀይሩ ግን እንደማይችሉ መገንዘብ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ በአፍሪካውያን የተጠላው ህወሓትና ፖሊሲዎቹ ምናልባት ጥቂቶቹን ካልሆነ በቀር ዳግም የበዛውን ህዝብ ማደናገር እንደማይቻለው ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል፤ እናም አሜሪካም ሆነች አውሮፓውያን በህወሓት የሀሰት ትርክት ተደናግረው ከኢትዮጵያ ጋር  ያላቸውን ታሪካዊ ወዳጅነት እንዳያጨልሙት መሥራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

 በተለይ የአሜሪካ ግብር ከፋዮች ገንዘብ ጥቅም ላይ እንዲውልና የአሜሪካ መልካም ወዳጅነት ዘላቂነት እንዲኖረው የባይደን አስተዳደርና አሜሪካውያን የመገናኛ አውታሮች ለህወሓት የሚያደርጉትን ድጋፍ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በማቆም ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያላቸውን አጋርነት በተጨባጭ የማሳያ ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ ጠቃሚ እርምጃ በመውሰድ ግንኙነቱ ዳግም ማከምና ህዝብ ከመረጠው መንግሥት ጋር ሚዛናዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በመፈጠር ለዘላቂ የህዝቦች ጥቅም መስራት ብሎም ጨለማውን ወደ ብርሃንና ተስፋ መቀየር ከአሜሪካ የሚጠበቅ ነው ሲሉ ፕሮፌሰር ዴንተን ኮሊንስ ጽሁፋቸውን ደምድመዋል።    

ከኢዜአ የተወሰደ

Leave a Reply