የአስር ዓመት ልጅን በሽተኛ በማስመሰል በሶስት ሚኒባስ ተደራጅተው ሲለምኑ የነበሩ ተያዙ

ህጻን ልጅን የኩላሊት ህመምተኛ በማስመሰል ሲለምኑ የነበሩ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የጉለሌ ክፍለ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የ10 ዓመት ህጻን ልጅን የኩላሊት ህመምተኛ በማስመሰልና በሀሰተኛ ሰነድ ገንዘብ ሲያሰባስቡ የተገኙ 11 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የጽ/ቤቱ ኃላፊ አቶ ጌታሁን አበራ ገልጸዋል፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት በ3 ክፍለ ከተሞች ስም የተዘጋጁ ሃሰተኛ ሰነድ እንዲሁም የሃኪም ማስረጃዎችን ከሚለምኑባቸው 2 ሚኒባስ መኪኖች ጋር በህብረተሰቡ በተደረገ ጥቆማና በጸጥታ አካላት ክትትል በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል ብለዋል፡፡

በተደረገው የክትትል ስራ ለህገ-ወጥ ስራው የተዘጋጁ ሃሰተኛ ሰነዶችን፣ ታርጋ ቁጥር 58456 እና 79169 ኮድ 3 ኦሮሚያ ሚኒባስ ታክሲዎችን እንዲሁም 9 ሴትና 2 ወንዶች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተጣራባቸው ይገኛል ብለዋል፡፡

በከተማዋ የተለያዩ ሃሰተኛ መረጃዎችን በማዘጋጀትና ያልታመመ ሰውን ታመመ በማለት የሚመለከተው የህክምና ተቋም ማረጋገጫ ሳይሠጥ በህገ-ወጥ መንገድ የሚካሄዱ ልመናዎች መብዛታቸውን የጠቆሙት ኃላፊው ህብረተሰቡ ከአጭበርባሪ ራሱንና ንብረቱን እንዲጠብቅ ጥሪ ማቅረባቸውን የከንቲባ ጽ/ቤትን ገልጾ ኢፕድ ዘግቧል።

Leave a Reply