ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር በተሻሻለው የፌዴራል ቤተሰብ ህግ

መግቢያ

የአንድ ህብረተሰብ እንዲሁም የሀገር መሰረት ቤተሰብ ነው፡፡ ቤተሰብ የኅብረተሰብ የተፈጥሮ መነሻ በመሆኑ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ህገ መንግስት በአንቀፅ 34/3 ስር ቤተሰብ ከህብረተሰብና ከመንግስት ጥበቃ የማግኘት መብት እንዳለው በማስቀመጥ ለቤተሰብ እውቅና ይሰጣል፡፡ ሕገ መንግስት ጥቅል ህግ በመሆኑ እና ስለ ቤተሰብ ዝርዝር ጉዳዮችን ስለማያካትት የቤተሰብ ጉዳዮችን የሚገዙ የፌደራል እንዲሁም የክልል የቤተሰብ ህጎች ወጥተው በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ በ1992 ዓ.ም በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ በወጣው በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ አዋጅ 213/1992 መሰረት ቤተሰብ በሁለት አይነት መንገዶች ሊመሰረት እንደሚችል ከህጉ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡ ይኸውም በጋብቻ እና ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ በመኖር ናቸው፡፡ በዚህ አጭር ፅሁፍ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ ስለመኖር በተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ህግ የተካተቱ መሰረታዊ ጉዳዮችን፣ በግላዊ እና በንብረት ግንኙነት ዙሪያ የሚኖረውን ውጤት ከጋብቻ ጋር በማነፃፀር እንመለከታለን፡፡

ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ ስለመኖር ትርጉም

የቤተሰብ ህጉ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ማለት አንድ ወንድና ሴት በህግ በሚፀና አኳኋን ጋብቻ ሳይፈጽሙ በትዳር መልክ አብረው የሚኖሩ ሲሆን ነው በማለት በአንቀፅ 98 ስር ትርጉም ይሰጣል፡፡ በህግ የፀና ጋብቻ በሶስት አይነት መንገድ ሊመሰረት የሚችል ሲሆን እነዚህም በክብር መዝግብ ሹም ፊት የሚፈፀሙ ጋብቻ፣ በሃይማኖት ስርዓት የሚፈፅም ጋብቻ እና በባህል ስርዓቶች የሚፈፀሙ ጋብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት ቤተሰብ ለመመስረት በማሰብ ነገር ግን ከእነዚህ ስርዓቶች አንዱን ሳይከተሉ በትዳር መልክ አብረው የሚኖሩ እንደሆነ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር በሚል በጋብቻ አብረው ከሚኖሩ ሰዎች በተወሰነ መልኩ የሚለይ የህግ ጥበቃ እና ሽፋን ተሰጥቷቸው ይገኛል፡፡ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር ከጋብቻ በተጨማሪ ህጋዊ እውቅና የተሰጠው ማህበረሰቡ ውስጥ ያለውን ነባራዊ ግንኘነት ማለትም ብዙ ሰዎች ህጋዊ ጋብቻ ሳይፈፅሙ ቤተሰብ እና ንብረት አፍርተው ስለሚኖሩ ጋብቻ ባይኖርም በዚህ ጥምረት አማካይነት የሚፈጠርን የንብረት ውህደት እና የልጆች ሁኔታ ጥበቃ ማግኘት ያለበት በመሆኑ ነው፡፡ በተለይ የሴቶች እና ህፃናትን መብት ከማስከበር አንፃር ከፍተኛ ጠቀሜታ ስለሚኖረው ነው፡፡

በቤተሰብ ህጉ ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብረው ኖሩ ለማለት ወንድየውና ሴትየዋ የሚያሳዩት ሁኔታ በህግ እንደተጋቡ ሰዎች አይነት መሆኑ አስፈላጊ እና በቂ ሲሆን ለሶስተኛ ወገኖች እንደተጋቡ ሆነው መቅረብ አስፈላጊ እንዳልሆነ በአንቀፅ 99/1 እና 2 ስር ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት የፈጠሩ ሰዎች በጋብቻ ሥርዓት የትዳር ግንኙነት እንደመሰረቱ ሰዎች የህግ ሰውነት የተሰጠው አካል ፊት ወይም በተፈጥሮ ሰው ፊት ግንኙነት መመስረታቸውን ቀርበው ማስረዳትም ሆነ ማስመስከር ወይም የተለየ ሥርዓት መፈፀም አይጠበቀባቸውም::

See also  የወሲብ ምስሎች (ፖርኖግራፊ) ሥርጭት ከኢትዮጵያ እንዲታገድ ዘመቻ ተጀመረ

ይህ ግንኙነት በህግ በተፈቀደው አግባብ ጋብቻ ሳይፈጸሙ በራሳቸው አነሳሽነት ከጋብቻ ስርዓት ውጪ የባልና ሚስት ግንኙነት የመሰለ ትስስር መፈጠርን የሚያመለክት ሲሆን ‹‹ በትዳር መልክ አብሮ መኖር ›› ማለት ደግሞ በቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 96 ውስጥ በግልፅ ሰፍሮ እንደሚገኘው አንድ ወንድና አንዲት ሴት ራሳቸውን እንደ ባልና ሚስት የሚቆጥሩና የሚኖሩ ከመሆናቸውም በላይ ቤተሰቦቻቸው ወይም ቤተዘመዶቻቸውና ማህበረሰቡ እንደ ባልና ሚስት የሚቀበላቸው አልያም የሚቆጥራቸው ሆኖ ሲገኝ የትዳር ሁኔታ በመካከላቸው እንዳለ መረዳት እንደሚቻል ያስገነዝባል፡፡ ለምሳሌም የተለያዩ ጥሪዎችን ፣ ሀዘን እና ደስታ ከማህበረሰቡ ጋር ሲካፈሉ ባልና ሚስት እንደሚያደርጉት አንድ ላይ በመሆን የሚከውኑ ሲሆን ማህበረሰቡ እንደተጋቡ ሊቆጥሯቸው ይችላሉ፡፡ እንዲሁም የጋብቻ ምስክር ወረቀት ባይኖራቸውም የተለያዩ ሰነዶች ላይ ባል ወይም ሚስት የሚል ስፍራ ላይ ለምሳሌ እድር ላይ ስማቸውን ያሰፈሩ እንደሆነ እራሳቸውን እንደባል እና ሚስት ቆጥረዋል ሊያስብላቸው ይችላል፡፡

ጋብቻ እና ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት ውጤት በህግ ያላቸው ተመሳሳይነት

 ተጋቢዎች የግል ግንኙነታቸውንና ንብረታቸውን በሚመለከት ‹‹የጋብቻ ውል›› ሊዋዋሉ ሲችሉ ምንም እንኳን በመካከላቸው የተፈፀመ ጋብቻ ባለመኖሩ ‹‹የጋብቻ ውል›› የሚል ስያሜ ሊሰጠው ባይችልም እንደ ባልና ሚስት የመኖር ግንኙነት የፈጠሩ ሰዎች ንብረታቸውን በሚመለከት የውል ስምምነት ሊያደርጉ የሚችሉ መሆኑ በአንቀፅ 42 እና 102 (1) መሰረት ያመሳስላቸዋል፡፡
 ምንም እንኳን በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 73 (የትዳር ወጪዎችን መሸፈን) እና አንቀፅ 101 (የጋራ የኑሮ ወጪዎችን መሸፍን) በሚል የተሰጠው ስያሜ የተለያየ ቢሆንም የተጋቡ ሰዎችም ሆነ እንደ ባልና ሚስት በትዳር መልክ የሚኖሩ ሰዎች የጋራ ወጪያቸውን እያንዳንዳቸው አቅማቸውና ችሎታቸው በፈቀደ መጠን አስተዋጾ ማድረግ የሚጠበቅባቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡
 በጋብቻ ውስጥ የተፈራው የባልና ሚስት የጋራ ንብረት የሚተዳደርበት፣ የሶስተኛ ወገን እዳ የሚከፈልበት እና ንብረት የሚጣራበት እንዲሁም ጋብቻው ሲፈርስ የጋራ ንብረት ክፍፍል የሚከናወንበት ሁኔታ እንደ ባልና ሚስት የመኖር ትስስር ውስጥ ለተፈራው የጋራ ንብረት አንድ አይነት ውጤት ወይም ተፈፃሚነት ያለው መሆኑ በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 103 ተደንግጓል፡፡
 ከጋብቻ ለሚወለዱ ልጆች እና እንደ ባልና ሚስት ከመኖር ግንኙነት ለሚወለዱ ልጆች የአባትነት፣ የእናትነትና የልጅነት እንዲሁም ከዚህ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች አፈፃፃም በአንድ አይነት ስርዓት የሚመሩ መሆናቸው በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 104 እና አንቀፅ 124 እና ተከታዮቹ አንቀፆች ውስጥ በግልፅ ተደንግጓል፡፡
 ጋብቻ ሲፈርስ ሊከፈል የሚገባውን ካሳ አስመልክቶ በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 84 መሰረት ጥፋት የፈፀመ አካል መኖሩ ሲረጋገጥ ለተጋቢው ሌላኛው ጥፋት ፈፃሚው አካል ካሳ ሊከፍል እንደሚገባ የተደነገገ ሲሆን እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት ቀሪ በሆኑ ጊዜ ጥፋት የፈፀመ ወገን አለ ተብሎ ሲታመን ወይም ሲረጋገጥ አጥፊው ለሌላኛው ወገን ካሳ ሊከፍል እንደሚገባ በአንቀፅ 105 (2) ስር መደንገጉ በዚህ ረገድ ሁለቱ ግንኙነቶች ማለትም ጋብቻ እና እንደ ባልና ሚስት መኖር ተመሳሳይ ውጤት ያላቸው መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡
 ጋብቻን እና ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት መኖርን የተመለከቱ ክርክሮች ሲነሱ በተመሳሳይ ስርዓት የሚመሩ መሆናቸው ሁለቱን ግንኙነቶች የሚያመሳስል አንድ ውጤት መኖሩን የቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 108፣ 115 እና 116 ድንጋጌዎች በማየት መገንዘብ ይቻላል፡፡
 ምንም እንኳን ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት መኖር የጋብቻ ዝምድና የማያስከትል ቢሆንም በቤተሰብ ህጉ ጋብቻ እንዳይፈፀም በአንቀፅ 9 መሰረት ክልከላ የተደረገበት የጋብቻ ዝምድና ውጤት እንደ ባልና ሚስት አብሮ ለመኖር ግንኙነትም የሚሰራ መሆኑን በአንቀፅ 100 (2) ሥር መደንገጉ ሁለቱ ግንኙነቶች ተፈጥሮአዊ የቤተሰብና የህብረተሰብ መገኛ ምንጮች መሆናቸውን የማስጠበቅ እውቅና እና ውጤት ያላቸው መሆኑ እንደሚያስገነዝብ መረዳት ይቻላል፡፡

See also  የዓለም የጤና ድርጅት የጤና ተቋማት ሲወድሙ " አላየሁም" ማለቱ አስገርሟል

ጋብቻ እና ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ የመኖር ግንኙነት ውጤት በህግ ያላቸው ልዩነት

 ጋብቻ በህግ ከተደነገጉት ሶስት የጋብቻ አፈፃፀም ስርዓቶች ቢያንስ በአንደኛው መንገድ መፈፀም እና ህጋዊ ውጤት እንዲኖረው ስለ ስርዓቱ መከናወን ወይም ጋብቻ ስለመፈፀሙ ማረጋገጫ በዋናነት በሰነድ ማስረጃ መረጋገጥ ያለበት መሆኑ (በአንቀፅ 1 – 4 እና ከአንቀፅ 22-27) እንዲሁም በአንቀፅ 28 ጋብቻን ስለማስመዝግብ የተመለከተ ሲሆን እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር ለጋብቻ አፈፃፀም የተቀመጡ ስርዓቶችን መፈፀምን ሳይጠብቅ በግለሰቦች ስምምነት ብቻ ያለተጨማሪ ስነ- ስርዓትና ማረጋገጫ የሚመሰረት ግንኙነት መሆኑ (በአንቀፅ 98፣ 99(1)ና (2) እና 106/(1-3) በቤተሰብ ህጉ ውስጥ ተደንግጓል፡፡
 በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 9 መሰረት ‹‹ጋብቻ›› በተጋቢዎች ዘመዶች መካከል የጋብቻ ዝምድና የመፍጠር ውጤት ያለው ሲሆን እንደ ባልና ሚስት መኖር ግን የጋብቻ ዝምድና የሚያስከትል ውጤት የሌለው መሆኑ በአንቀፅ 100(1) ስር ተደንግጓል፡፡
 ጋብቻ የሚፈርሰው በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 75 እና 76 በተቀመጠው ስርዓት በባለጉዳዮች አነሳሽነት በፍርድ ቤት ውሳኔ ሲሆን እንደ ባልና ሚስት የመኖር ግንኙነት ግን ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ከሁለቱ በአንዳቸው አነሳሽነት በማንኛውም ጊዜ ቀሪ ሊሆን የሚችል መሆኑ (አንቀፅ 105/1) ተመልክቷል፡፡
 ጋብቻ በተጋቢዎቹ ወይም በባልና ሚስቱ የግላዊ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ውጤት በቤተሰብ ህጉ ከአንቀፅ 49-56 ( የመከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ፤ የቤተሰብ የጋራ አመራር፤ አብሮ የመኖር፣ የመኖሪያ ስፍራ ስለመወሰን እና የመተማመን ግዴታ) በግልፅ ሲደነግግ ይህ አይነቱ አስገዳጅ የግል ግንኙነት ውጤት እንደ ባልና ሚስት ለመኖር ግንኙነት በግልፅ በህጉ ያልተደነገገ መሆኑ፡፡
 የጋራ ሀብትን አስመልክቶ የተጋቡ ሰዎች ከተጋቡ በኃላ ያፈሯቸው ንብረቶች በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 62 መሰረት የጋራ ባለቤትነት መብት ሲኖራቸው እንደ ባልና ሚስት በመኖር ግንኙነት ውስጥ ላሉ ሰዎች የጋራ ባለቤትነት መብት ቢያንስ የሶስት ዓመት የአብሮነት ቆይታን የሚጠይቅ መሆኑ (የቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 102(1))፡፡
 እንደ ባልና ሚስት የመኖር ትስስር የጋበቻ ዝምድና በአንቀፅ 100(1) የማያስከትል በመሆኑ በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 198 (1) መሰረት ቀለብ የመቁረጥ ግዴታ የማያስክትል ሲሆን በተቃራኒው ጋብቻ በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 9 መሰረት የጋብቻ ዝምድና የሚያስከትል በመሆኑ ቀለብ የመቁረጥ ግዴታን ያስከትላል፡፡

See also  ተመድ በትግራይ ያሉ የረድኤት ሠራተኞች ማስወጣቱን እንደሚቀጥል አስታወቀ

ጋብቻ ሳይፈፅሙ እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር አለ የማያስብሉ ሁኔታዎች

አንድ ወንድና አንዲት ሴት በታወቀና በተደጋገመ ሁኔታ የሩካቤ ሥጋ ግንኙነት መፈፀማቸው ብቻ፣ በሁለቱ መካከል ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት የመኖር ግንኙነት አላቸው ለማለት በቂ ምክንያት እንዳልሆነ የቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 99/3 ያስቀምጣል፡፡ የቤተሰብ ህጉ ሽፋን ስር ለመውደቅ ጋብቻ ሳይፈፅሙ አብረው የሚሆኑ ሰዎች ልክ እንደተጋቡ ሰዎች የትዳር ሁኔታ ማሳየት እንዳለባቸው እና ከተራ ግንኙነት በዘለለ ከፍ ያለ ሃላፊነትና ግዴታ የሚጠበቅበት ግንኙነት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡
ጋብቻ ሳይፈፀም የሚደረጉ ሌሎች ግንኙነቶች
ከጋብቻ ስርዓት ወይም ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት አብሮ ከመኖር ውጪ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የሚደረጉ ሌሎች ግንኙነቶች በህግ ፊት ምንም ውጤት እንደማይኖራቸው የቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 107/1 ይደነግጋል፡፡ ይህ ማለት ለምሳሌ አንድ ወንድ እና እንዲት ሴት ሰው በሚያውቀው ሁኔታ በጓደኝነት አብረው መሆናቸው ምንም አይነት የህግ እውቅና የለውም ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ ጋብቻ እና ጋብቻ ሳይፈፀም እንደ ባልና ሚስት አብሮ መኖር በተሻሻለው የቤተሰብ ህግ እንደ ቤተሰብ መመስረቻ መንገዶች እውቅና ተሰጥቷቸው ይገኛሉ፡፡ በተጣማሪዎቹ የንብረት እና የግላዊ ግንኙነት ላይ የሚኖራቸው ውጤትም በህጉ ሽፋን ያገኘ ሲሆን በህግ ደረጃ የተለያዩ የሚመሳሰሉባቸዉ እና የሚለያዩባቸው ነጥቦች እንዳሉ ከቤተሰብ ህጉ ድንጋጌዎች መገንዘብ ይቻላል፡፡

በንቃተ ህግ፣ ትምህርትና ስልጠና ዳይሬክቶሬት ministry of justice

Leave a Reply