4ሺ 35 ግራም ኮኬይን ይዞ የተገኘው ናይጄሪያዊ በፅኑ እስራትና በገንዘብ ተቀጣ

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትህ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ዘርፍ የተደራጁና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ጀነራል ዐቃቤ ሕግ 4ሺ 35 ግራም የሚመዝን ኮኬይን የተባለ አደገኛ እፅ ይዞ የተገኘው ናይጀሪያዊ ዜጋ በፅኑ እስራት እና በገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ አደረገ፡፡

የዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው ሚስተር ፒተር ኢመሀን የተባለው ናይጀሪያዊ ዜግነት ያለው ተከሳሽ ልዩ ፍቃድ ሳይኖረው በህግ የተከለከሉ እፆችን ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር አስቦ ከብራዚል ሀገር በመነሳት የኢትዮጵያ አየር መንገድን ተጠቅሞ ወደ ናይጄሪያ ሀገር ለመሄድ ጥቅምት 3 ቀን 2015 ዓ.ም ከምሽቱ በግምት 1፡30 ሰዓት ሲሆን በቦሌ አለም ዓቀፍ ኤርፖርት ትራንዚት እያደረገ ባለበት ወቅት በተደረገ የኤክስሬ ፍተሻ 4ሺ 35 ግራም የሚመዝን ኮኬይን የተባለ አደገኛ እፅ በወገቡ ላይ በማሰር የተገኘበት ሲሆን ሰዎችን ሱስ በማስያዝ ለተለያዩ ወንጀል ድርጊቶች መንስኤ እንዲሆኑ ስለሚገፋፋ እንዳይመረት፣ እንዳይዘዋወር፣ በጥቅም ላይ እንዳይውል የታገደውን የኮኬይን እፅ ፍቃድ ሳይኖረው ይዞ በመጓዝ ላይ የተገኘ በመሆኑ በፈፀመው አደገኛ እፆችን በማዘዋወር ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቶበታል፡፡

ተከሳሽም ክሱ ተነቦለት የወንጀል ድርጊቱን ፈፅሜያለሁ ያለ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግም ተከሳሹ የተከሰሰበትን የወንጀል ድርጊት እንደ ክሱ ሙሉ በሙሉ ያመነ በመሆኑ ባመነው መሰረት በተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ ይሰጥልኝ ሲል አቅርቧል፡፡ ፍርድ ቤቱም ተከሳሹ በተከሰሰበት ድንጋጌ ስር በዝርዝር ያመነ በመሆኑ ባመነው መሰረት ጥፋተኛ ነህ ብሎታል፡፡

ጉዳዩን የተመለከተውም የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የልደታ ምድብ 1ኛ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል ችሎትም ተከሳሽን ያርማል ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን ያስተምራል ያለውን በ10 ዓመት ፅኑ እስራት እና በ20 ሺ ብር የገንዘብ መቀጮ እንዲቀጣ ሲል ወስኖበታል፡፡

See also  የሐረሪ የምርጫ ሂደት በተመለከተ ምርጫ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውድቅ አደረገ

Leave a Reply